የክርስቶስ ብርሃን አገልጋዮች ማኅበር በቤኒን ማየት የተሳናቸውን ሰዎች እየረዳ እንደሚገኝ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከቤኒን የንግድ ከተማ ኮቶኑ 83 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በጃንግላንሜይ የሚገኘውን የሲሎኤ ማዕከልን የሚመሩ እህት አዴላይድ ቶኚዚን ሲሆኑ፥ በማዕከሉ የሚታገዝ የአሥራ አምስት ዓመት አዳጊ ሕጻን ማክስሜ በቤኒን ከክሎዌካንሜ ወረዳ የመጣ እና በአምስት ዓመቱ ወደ ማዕከሉ ሲመጣ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንደ ነበር አስታውሷል።
ዓይነ ስውር ሆኖ መወለዱን በከፍተኛ ሐዘን የሚናገረው ማክስሜ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. ወደ ሲሎዬ ማዕከል ከመምጣቱ በፊት በዓይነ ስውርነቱ ምክንያት ሕይወቱ ያለቀ ይመስለው እንደ ነበር ገልጾ፥ ነገር ግን የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ እህቶች መመሪያ እና እገዛ ማክስሜ የመለስተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ ያለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ዲፕሎማውን መቀበሉ ታውቋል።
በክርስቶስ ብርሃን አገልጋዮች ማኅበር ትምህርት ቤት ከተመዘገበ በኋላ ስለ ኮምፒውተር፣ የፈረንሳይኛ ቋንቋ መናገር እና ማንበብ መቻሉን የተናገረው ማክስሜ፥ “ማዕከሉ በሕይወቴ ላይ አዲስ ዕድል ሰጠኝ” ሲል በደስታ ገልጾ፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሕግ ማሻሻያዎች ቢደረጉም ቤኒን ውስጥ የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች ሁኔታ ያልተለወጥ መሆኑ ተነግሯል።
የክርስቶስ ብርሃን አገልጋዮች ገዳማውያት ማኅበር የበላይ አለቃ እና የማዕከሉ ዋና አስተዳዳሪ እህት ናዲን አድጃግባ ቤኒን ውስጥ ማየት የተሳናቸውን ሕጻናት በማስመልከት ሲገሩት፥ ሕጻናቱ ወደኋላ የሚቀሩት በቤተሰቦቻቸው ቸልተኝነት እንደሆነ እና “ጎደሎ ሰው” ተደርገው ስለሚወሰዱ እንደሆነ አስረድተዋል።
እህት ናዲን አድጃግባ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር 3/1983 ዓ. ም. ማዕከሉን የመሠረቱት በጊዜው የሎኮሳ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በነበሩት አቡነ ሮበርት ሳስትሬ በተደረገላቸው ዕርዳታ እና የቅዱስ ልበ ኢየሱስ በጎ አድራጎት ገዳማውያት ማኅበር አባል እህት ማርያ አግቦቮን ባደረጉላቸው ዕርዳታ መሆኑ ይታወሳል።
ማየት ለተሳናቸው ራስን በራስ የማስተዳደር ችሎታ ማዳበር
አቡነ ሳስትሬ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1993 ዓ. ም. የሲሎኤ ማዕከልን ለክርስቶስ ብርሃን አገልጋዮች ገዳማውያት ማኅበር በአደራ ሲሰጡ ዓላማው ማየት የተሳናቸው ዓይነ ስውራን በቂ ትምህርት የሚያገኙበት እና ራሳቸውን በራሳቸው የሚመሩበትን ቦታ ለመፍጠር እንደ ነበር እና በዚህም ማዕከሉ የማየት ችግር ያለባቸውን ቢያንስ ስድስት ዓመት የሞላቸው ሕፃናትን መቀበል ጀመረ።
በማዕከሉ ውስጥ ሁለት አማራጮች እንዳሉ የሚገልጹት እህት ናዲን፥ በለጋ ዕድሜያቸው ትምህርት ቤት የሚገቡት ብሬይል እንደሚማሩ እና በዕድሜ መግፋት መማር የማይችሉ ግን ሙያን እንደሚማሩ አስረድተዋል።
ማዕከሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በውስጡ ከ300 በላይ ዓይነ ስውራን በእንግድነት መኖራቸውን እህት አደላይድ ቶኚዚን ተናግረው፥ ከቀድሞ ነዋሪዎች መካከል የእጅ ጥበብ አውደ ጥናቶች መምህራን እና አስተማሪዎች እንደሚገኙ በማስረዳት፥ ከዚህም በተጨማሪም በፈረንሳይ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የማዕከሉ የቀድሞ ተማሪዎች እንደሚገኙ አክለዋል።
መጽናኛችን እነዚህ ማየት የተሳናቸው ልጆች ሲያብቡ ማየት ነው
ምንም እንኳን እነዚህ የደስታ እና የተስፋ ምክንያቶች ቢኖሩም የክርስቶስ ብርሃን አገልጋዮች ማኅበር እህቶችን ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሟቸው የሚናገሩት እህት አደላይድ ቶኚዚን፥ ማየት የተሳናቸው ሕጻናት በአጠገባቸው ያለውን ነገር ማየት ካለመቻላቸው በተጨማሪ አብዛኛው ነዋሪ ስለወደፊት ሕይወቱ እጅግ የሚጨነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕከሉ ነዋሪ የሆኑት ዣን “እጅግ የሚከብደኝ በትምህርቴ ሩቅ የምሄድበትን ዕድል ማግኘት እና ከአካል ጉዳተኛነቴ ጋር የሚስማማ ሥራ ማግኘት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
እህት አድጃግባ ዋናው ችግራቸው ሆኖ የቀጠለው ሙያዊ ትምህርቶችን መካተት እንደሆነ ተናግረው፥በአገሪቱ ውስጥ ዓይነ-ሥውራን ሥራ ማግኘት ቀላል አይደለም” ሲሉ ገልጸው፥ ከዚህም በላይ የክርስቶስ ብርሃን አገልጋዮች ማኅበር ማዕከል አንዳንድ ጊዜ ልጆቹ ኃላፊነትን በራሳቸው እንዲወስዱ ለማድረግ እንደሚገደድ አስረድተዋል።
እህት አደላይድ ቶኚዚን ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ማዕከል ካመጡ በኋላ የማይጠይቋቸው መሆኑን በሐዘን ገልጸው፥ ማዕከሉ ልጆችን ለዕረፍት ወደ ቤታቸው ሲልካቸው ወላጆች ብዙውን ጊዜ ሊቀበሏቸው ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
“አንዳንድ ጊዜ የምግብ፣ የጤና እና የልብስ ፍላጎቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ ለማሟላት በቂ አቅም አለመኖሩ ትልቅ ሸክም በመሆኑ ሸክሙ እየጨመረ ይሄዳል” ብለው፥ ሆኖም ትልቁ ደስታቸው እና መጽናኛቸው እነዚህ ልጆች በወደፊት ብሩህ ተስፋ ሲያድጉ እና ሲያብቡ ማየት ነው” ሲሉ በቤኒን የክርስቶስ ብርሃን አገልጋዮች ማኅበር አባል እህት ቶኚዚን ገለጻቸውን ደምድመዋል።