የጸሎት አስፈላጊነት
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ጸሎትም ያደርግ የነበረው ስለ እኛ ነበር እንጂ ስለራሱ አልነበረም። ምክንያቱም እርሱ የጸሎት ግዴታ አልነበረውም፣ በአብነቱ ብቻ ሳይሆን በቃሉም «እንግዲህ እናንተስ እንዲህ በማለት ጸልዩ፣ በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፣ መንግሰትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን፣ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን እኛ የበደሉንም ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፣ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፣ መንግስት ያንተ ናትና፣ ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን» (ማቴ 6፣9-13) እያለ አስተማራቸው። ቀጥሎም ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ (ማቴ. 26፣41)፣ ለምኑ ይሰጣችሁማል፣ ፈልጉ ታገኙታላችሁ፣ መዝጊያውንም አንኳኩ ይከፈትላችኋል፣ … (ማቴ. 7፣7-8) አላቸው።
ሐዋርያቱ የመምህራቸውን አብነትና ምክር ተከትለው ጸሎት ያደርጉ ነበር። ዘወትር በአንድነት ተሰብስበውና በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት ይተጉ ነበር (የሐዋ. 1፣10)። «ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው» (የሐዋ. 6፡6) እያለ የሐዋርያት ሥራ ይነግረናል። ሐዋርያትም በተራቸው ለምእመናን እንዲጸልዩ ይመክሩባቸው ነበር።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፣ በዚህም ሐሳብ ስለቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ትጉ ….» (ኤፌ. 6፣18)፣ «ሁል ጊዜ ደስ ይበላችሁ፣ ሳታቋርጡ ጸልዩ፣»(1ኛ ተሰ.5፣17-18) እያለ ይጽፍላቸው ነበር።
ቅዱስ ያዕቆብም «ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፣ ደስ የሚለውንም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። ከእናንተ ማንም የታመመ ቢኖር፣…. በጌታ ስም ይጸልዩለት፣ የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፣ …. ኃጢአትም ሰርቶ እንደሆነም ይሰረይለታል፣ እርስ በርሳችሁ ኃጢአታችሁን ተናዘዙ፣ ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለሌላው ይጸልይ፣ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች» (ያዕ. 5፣13-16) እያለ ጽፎአል። የተጻፈላቸውም ሰዎች ጸሎት አድርጉ» የሚለውን የኢየሱስን አደራ በትጋት ይፈጽሙት ነበር።ቅዱሳንም በእውነት የጸሎት ሰዎች ነበሩ፣ ጸሎት የዕለት ምግባቸው ነበር። ከእነርሱም ብዙዎች ቀኑ እያጠረባቸው ሌሊቱንም ጭምር ጸሎት ያደርጉ ነበር። ቅዱስ አንጦንዮስ አበምኔት ሌሊት ጸሎት ሲያደርግ አድሮ፣ ይህንን ረጅም ጊዜ እንደ አጭር ገምቶ ፀሐይ ስትወጣ ባየ ጊዜ «ሌሊቱ እንዴት አጭር ነው» እያለ ያዝን ነበር።
ቅዱሳን ስለ ፀሎት ትልቅነት ሲመሰክሩ «ከጸሎት የሚበልጥ ምግብ ምን አለ? ከእርሱ ሌላ ለሕይወታችን የሚጠቅም ምን አለን? ምንስ ይገኛል?» ይሉ ነበር። ቅዱስ አውጉስጡኖስም «በሃይማኖታችን ውስጥ ከጸሎት የላቀ ነገር ምን አለ? ይላል። ቀጥሎም «ሳትጸልዩ መዋል ቀኑን በከንቱ ማሳለፍ ነው» ይላል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ደግሞ «በሕይወታችን ዘመን ከምናደርገው ሥራ ሁሉ ከጸሎት የሚበልጥ የለም» እያለ ያስረዳል። የሊጎሪው ቅዱስ አልፎንሶስ በበኩሉ «የሚጸልይ ይድናል፣ የማይጸልይ ግን ይኰነናል» እያለ ይናገራል። ቅዱስ ቦናቨንቱራም «ያለ ጸሎት በቅድስና መንገድ መራመድ አይቻልም» ይላል።
ቅዱሳን ሁሉ ጸሎት ለደኀንነታችን አስፈላጊ መሆኑን ያሳስቡናል። በጸሎት በኩል ለእግዚአብሔር ስግደትና ምስጋና እናቀርባለን፣ ፍቅራችን እንገልጽለታለን። ራሳችንም የሚያስፈልገንን የኃጢአት ሥርየትና ጸጋን እንቀበላለን። የልባችንን ምኞት፣ መከራና ሐዘናችንን ለእግዚአብሔር እንገልጽለታለን። በጸሎት ሰማያዊ መጽናናት፣ ደስታ፣ የልብ ብርሃን፣ የትሕትና መንፈስ፣ ፍቅር፣ ተጋድሎ፣ ንጽሕና፣ ትዕግስትና ሌሎችን መንፈሳዊያን ፍሬዎችን ሁሉ እናፈራለን። በእነዚህም ፍሬዎች አማካይነት ፈተናን ለማሸነፍ ኃይል እናገኛለን።
ጸሎት በመንፈሳዊ መንገድ በጥሩ ሁኔታ ያራምደናል፣ መንግሥተ ሰማያትንም ይከፍትልናል። ነገር ግን እኛ በቀዝቃዛነታችን ብዙ ጊዜ ከጸሎት ስንሸሽ እንገኛለን። እግዚአብሔርን በማያስደሰት ሁኔታ እንፈጽመዋለን፣ እናሳጥረዋልን፣ ጥረታችን ይህ ብቻ ነው። በጣም ያሳዝናል። የጥልቅ ጸሎት ጥቅም አለመረዳታችን ለእኛ ትልቅ ጉዳት ነው፣ ሞኞች አንሁን። ቀዝቃዛ መንፈሳችንን አግልለን ትኩስ የሆነውን የቅዱሳንን መንፈስ እንልበስ። እንደ እነርሱ የጸሎት ወዳጆች እንሁን፣ እንደነርሱ ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ሰውነት በጥሞናና በተመስጥኦ እንጸልይ።