የጥቅምት 02 /2018 ዓ. ም ሰንበት ዘጽጌ 1ኛ ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የዕለቱ ምንባባት፡-
1. ሮሜ 7፡ 1-13 ፣
2. 1ጴጥ 1፡ 21-25 ፣
3. ሐዋ 22፡ 1-5 ፣
4. ማቴ 6፡ 25-34
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
መጨነቅ እንደማይገባ
ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ስለ ነፍሳችሁ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ ነፍስ ከምግብ ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም፥ ወይም አያጭዱም፥ ወደ ጎተራም አይሰበስቡም፤ ነገር ግን የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል፤ ታዲያ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል እስቲ ማን ነው? ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። ነገር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እግዚአብሔር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? ስለዚህ “ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?” ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብም እነዚህን ሁሉ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃል። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፥ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። “ስለዚህ ስለነገ አትጨነቁ፥ ነገ ስለ ራሱ ይጨነቃልና፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
“የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቁን ፈልጉ ፤ የቀረው ሁሉ ይጨመርላችኋል!”
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ላላችሁ ሁሉ!
እንደ ቤተክርስትያናችን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሠረት የዛሬው ሰንበት ዘጽጌ 1ኛ በመባል ይታወቃል።
በምንኖርበት ዘመን ብዙ የሚያስጨንቁን ነገሮች ይኖራሉ። ጊዜያዊ እና አላፊ የሆነው በምድር የምንኖረው ሕይወታችን በብዙ ሲያንከራትተን ይስተዋላል። የሰማዩን ችላ ብለን በምድሩ ብቻ እየታጠርን መሆናችንን ማወቅ ይኖርብናል። በክርስቶስ ያገኘነውን የመንግሥተ-ሰማያት ዜግነትን ምድራዊ በሆኑ ነግሮች ለመተካት እየቃጣን ነው።ከክርስቶስ ያገኘንውን ጸጋም በመዘንጋት ከሕግ በታች አለመሆናችንን ዘንግተናል። አሮጌውን ከአዲሱ የመቀላቀል አባዜ የያዘን መሆኑን ማየት ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ "እንግዲህ ወንድሞች ሆይ እናንተ ደግሞ በክርስቶስ ሥጋ ለሕግ ተገድላችኋል ፤ ለእግዚአብሔር ፍሬ እንድናፈራ እናንተ ለሌላው ከሙታን ለተነሣው ለእርሱ ትሆኑ ዘንድ (ሮሜ᎐ 7:4)" በማለት ከሙታን የተነሣውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘን ፍሬ ማፍራት እንዳለብን ያስተምራል። አሮጌው ሕይወታችን በክርስቶስ ትንሣኤ ወደ አዲስ ስለመቀየሩ በሚገባ ያወሳል። ስለ ምድራዊው ሳይሆን ለሰማዩ እርስታችን መጨነቅ እንዳለብን ይናገራል። ለሥጋ ብቻ መሮጥ ትርፍ እንደሌለው ይመሰክራል። ከሕግ በታች አለመሆናችንን ያስተምራል።
ሞቶ መቅረት ያለበትን አሮጌው ሰውነታችንን በመቀስቀስ መድከም የለብንም። ምድራዊ ለሆነ ነገር ብቻ ያለ ልክ መልፋት ኪሳራ የበዛበት ነው። በክርስቶስ የተረጋገጠልንን የብርሃን ሕይወት አጥብቀን በመያዝ መመላለስ የክርስትናችን መሠረት ነው። ትዛዛቱን በመጠበቅ ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት የመንግሥተ-ሰማያት መግቢያ ነው።ሐዋሪያው ጳውሎስ "ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው ፤ ትእዛዛቱም ቅድስትና ጻድቅ በጎም ናት (ሮሜ᎐ 7፡12)" በማለት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ የጽድቅ መንገድ እንደሆነ በድጋሚ ያስተምራል። ሕጉን መጠበቅ የክርስትናችን መሠረት እንደሆነ በሚገባ ያስተምራል። ክርስቶስን መከተል ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመግቢያ መንገድ ነው።
ክርስቶስ ያስተማረን ትልቁ ምሥጢር ፍቅር ነው። መዋደድ ዋነኛው የክርስትናችን እውነት እንደሆነ አሳይቶናል።በመኖር መመስከር ይጠበቅብናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ "ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ እርስ በእርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ (1ጴ᎐1፡22)" በማለት ስለ እውነት መንገድ ያስተምራል።የእግዚአብሔርን መንግሥት መፈለግ የምንችለው በመዋደድ ነው። የጽድቅ ጉዞ ፤ የፍቅር ጉዞ ያለበት ነው።" ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋው ዘር አይደለም ሕያውና ዘለዓለም በሚኖር በእግዚኣአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ (1ጴ᎐ 1፡23)" እያለም በክርስቶስ በፍቅር የተወለድን መሆኑን በሚገባ ያስተምራል።ይሕንን እውነት በተግባር በመኖር በሕይወት ምስክርነት መግለጥ እንዳለብንም ያስገነዝበናል። የክርስትና ጉዞ የመንግሥተ-ሰማያት ጉዞ ነው። የጽድቅ ጉዞ የድኅነት መንገድ በመሆኑ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በሚገባ በመውደድ የምንኖረው ነው።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሚጠፋ ነገር ብዙ መሯሯጥ እንደሌለብን ያስተምራል። ሰማያዊው ነገር የተሻለ እና የሚበልጥ ስለመሆኑ ከልብ ያስተምራል። በመሆኑም "ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ዱር አበባ ነውና ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል ፤ የጌታ ቃል ግን ለዘለዓለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይሕ ነው (1ጴ᎐1፡24-25)" በማለት ስለ እግዚአብሔር ቃል ኃያልነት ይመሰክራል። እያንዳንዳችን በክርስቶስ ቃል እንድንኖር ተጠርተናል።በዘለዓለማዊ ቃሉ መመራት የጽድቅ መንገድ ነው። በክርስቶስ ፍቅር መሠራት የመንግሥቱ ሕይወት ነው። እምነታችን እና ተስፋችን በእግዚአብሔር ዘነድ ሊሆን ይገባል። በጊዜያዊ ነገር የምንመካ መሆን የለብንም።ምክንያቱም ዘለዓለማዊ በሆነው እግዚአብሔር የተሠራን በመሆናችን የዚሕ ዓለም ጉዳይ በብዙ ሊያስጨንቀን አይገባም።
የምንበላው ነገር ያስፈልገናል። በምድር ለመኖር በቂ የሆኑ ነገሮች ሊኖሩን የተገባ ነው። ይሁን እንጂ ከልክ አልፈው ሊያስጨንቁን አይገባም። እግዚአብሔር አስቀድሞ የሚያስፈልገንን ያውቃል። በልካችንም በጊዜው ይሰጠናል።በመታገስ መኖር እንደሚኖርብን መረዳት ያሻናል። መጨነቅ ግን የሚያመጣብን ቀውስ ይኖራልና መጠንቀቅ ይኖርብናል። ዘለዓለማዊው የሆነው ሕይወታችን ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅብናል።" ስለዚህ እላችኋለሁ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉት እና በምትጠጡት ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? (ማቴ᎐ 6፡25)" በማለት የሚበልጠው ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚኖርብን ክርስቶስ በሚገባ ያስተምራል። ይሕንን ጥያቄ እያንዳንዳችንን የሚመለከት እንደሆነ ከልብ መረዳት ይጠበቅብናል። መልሳችን በተግባር የተደገፈ መሆን አለበት። ክርስትና በተግባር የሚኖር ነው። የሚበልጠው ላይ ቀልባችንን ማሳረፍ ያሻናል።
"ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ አይዘሩም አያጭዱም በጎተራም አይከቱም የሰማዩ አባታቸውም ይመግባቸዋል።እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? (ማቴ᎐ 6፡26)" በማለት በድጋሚ ለሕይወታችን አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ይጠይቀናል። እኛ በብዙ የተሻልን ሰዎች ስንሆን እንዴት ምድራዊ የሆኑ ነገሮች ያስጨንቁናል እያልን ራሳችንን በሚገባ መጠየቅ ይጠበቅብናል። ምክንያቱም አኗኗራችንን የሚመለከት ጥያቄ ስለሆን በጥንቃቄ መመለስ ያሻናል። ክርስቶስ የሞተልን የተከበርን መሆናችንን በሚገባ መረዳት አለብን። ጊዜያዊ የሆኑ ቁስ ነገሮች ሊያሰናክሉን አይገባም።ከመብላት እና ከመጠጣት መውጣት ተገቢ ነው። ምክንያቱም እኛ ከሥጋ ብቻ የተሠራን አይደለንም። ተጨንቀን እና ተጠበን የምናመጣው ምንም ነገር የለም። በእድሜያችን አንዲት ደቂቃ መጨመር አንችልም። በመሆኑም መጨነቅ በማይገባን ጉዳይ ላይ ጊዜያችንን ማባከን አይገባም።
"እንግዲህ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ ፤ ይሕንን ሁሉ አሕዛብም ይፈልጋሉ ይሕ ሁሉ እንዳሚያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና (ማቴ᎐ 6፡31-32)" በማለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብዙ ያስተምራል። እያንዳንዳችን በሚገባ መማር ያለብን ቁም ነገር ነው የሚያስተምረን።እግዚአብሔርን በማምለክ እና በማክበር መኖር ይኖርብናል። እርሱ ስለእኛ ከእኛ በላይ ያውቃል። ተጨንቀን የምናመጣው ነገር እንደሌለም ያውቃል። እርሱ ሁሉን አዋቂ በመሆኑ በፊቱ የተደበቀ ምንም ነገር የለም።
"ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቁን ፈልጉ ይሕም ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋልና (ማቴ᎐ 6፡33-34)" በማለት ነገ በእኛ ቁጥጥር ስር እንዳልሆነ ክርስቶስ በሚገባ ያስተምረናል። በክርስቶስ ካመንን በፍቅር ሥራ ተባባሪ በመሆን ክርስትናችን ማበብ አለበት። በስም ብቻ ክርስትያን መባል ምንም ፋይዳ የለውም። በተግባር መኖር የሚጠበቅብን ዘመን ላይ ነው ያለነው። እምነት ፣ ፍቅር እና ተስፋ ጸንተው የሚኖሩ መሆናቸውን በተግባር ገልጠን ማለፍ ያለብን ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። በመሆኑም ዘለዓለማዊውን ነገር በሚገባ የምንፈልግበት ወቅት መሆኑን በመረዳት ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን በሕይወት በመኖር በተግባር ማሳየት ያሻናል።
በቅዱስ ቃሉ “የእግዚአብሔርን መንግሥት እና ጽድቁን ፈልጉ ፤ የቀረው ሁሉ ይጨመርላችኋል!” እንዳለን ይህንን ለመፈፀም እና ለመኖር የሚያስችለንን ጸጋ እንዲበዛልን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ታማልደን።
ምንጭ፡- ቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ ስርጭት ክፍል