የመስከረም 25/2018 ዓ. ም ዘመስቀል 2ኛ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የዕለቱ ምንባባ
1. 1ቆሮ 2፡ 1-11
2. 1ጴጥ 2፡ 20-25
3. ሐዋ 4፡ 19-30
4. ሉቃ 9፡ 18-27
የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል
ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ጴጥሮስ መመስከሩ
ለብቻውም ሲጸልይ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፦ “ሕዝቡ እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም መልሰው፦ “ ‘መጥምቁ ዮሐንስ፥’ ሌሎችም ‘ኤልያስ፥’ ሌሎችም ‘ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል፤’ ይላሉ፤” አሉት። እርሱም፦ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ “የእግዚአብሔር መሢሕ ነህ፤” አለ።
ኢየሱስ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው አስቀድሞ መናገሩ
እርሱ ግን ይህንን ለማንም እንዳይናገሩ እነርሱን አስጠንቅቆ በማዘዝ፦ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ በሽማግሌዎችና በካህናት አለቆች፥ በጻፎችም ይናቃል፥ እንዲሁም ይገደላል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤” አለ። ለሁሉም እንዲህ አላቸው፦ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር፥ ራሱን ይካድ፤ በየዕለቱም መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? በእኔና በቃሎቼ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩና በአባቱ ክብር እንዲሁም በቅዱሳን መላእክቱ ክብር በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል። እውነት እላችኋለሁ፤ በዚህ ከቆሙት አንዳንዶች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አሉ።”
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር መሠረት የዛሬው ሰንበት ዘመስቀል 2ኛ በመባል ይታወቃል።
የዛሬው የወንጌል ክፍል ከባለፈው ሳምንት ካስተነተንበት የወንጌል ሐሳብ፣ እሱም የማቴ.ወን.ም.16፡ ከ13-20 ካለው ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ያለው ነው፡፡ሐዋሪያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሎቹን ሐወዋሪያት ወክሎ የክርስቶስን መሲህነት እና የሕያው የእግዚአብሔር ልጅነትን ከመሠከረ በኋላ፣ክርስቶስ ስለ መስቀል ጉዞው ይነግራቸው ጀመረ፡፡ወደ ኢየሩሳሌም በሚጓዝበት ጊዜም ለሐዋሪያቱ በቅድስቷ ከተማ እየሩሳሌም በስተ መጨረሻ ስለሚጠብቀው መከራ፣ሞት እንዲሁም ስለትንሳዔው ክብር አስቀድሞ በግልጥ ነገራቸው፡፡ከሽማግሌዎች እና ከካህናት አለቆች፤ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ እንዲሁም በሶስተኛውም ቀን ይነሳ ዘንድ እንዲገባው ፤ለደቀመዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር፡፡ነገር ግን ሐዋሪያቱ እምነታቸው የጠነከረ ስላልነበር እና እንዲሁም አስተሳሰባቸው ከዚህዓለም ጋር የተቆራኘ ስለነበር ሊረዱት አልቻሉም፡፡
ሐዋሪያው ጴጥሮስም የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ስለከበደው እና ስላልተዋጠለት "አይሁንብህ ጌታ ሆይ!ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገስጸው ጀመር፡፡" ሐዋሪያው ጴጥሮስ በክርስቶስ ያምናል፣ሊከተለውም ወዷል ነገር ግን ክርስቶስ ስለሁላችን በመስቀል ሞት ስቃይ እንዲያልፍ ሐዋሪያው ጴጥሮስ አልፈለገም፡፡ለጴጥሮስ፣ለሌሎች ሐዋሪያቶች እና እንዲሁም ለእኛም የክርስቶስ የመስቀል ሞት የሚያሳዝን እና መከራ የበዛት ነው፡፡ነገር ግን እኛን ለማዳን እና የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም የተከፈለ መሥዋትነት በመሆኑ ክርስቶስ ከመጣበት ዓላማ ፈቀቅ ሊል አልሆነም፡፡ለዚህም ነው ክርስቶስ ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው፡፡
ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንንም በሚመለከት መልኩ እንዲህ አለ፤ይኸውም፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ አለ፡፡በዚህም መንገድ ሁለት እውነተኛ ሐዋሪያ የመሆኛ መንገዶችን አስታወቀ፡፡የመጀመሪያው ራስን መካድ ነው፤ይህም የሚሆነው ደግሞ በማስመሰል አይደለም፤በእውነተኛ መለወጥ የሚሆን ነው፡፡ሁለተኛው እውነተኛ ሐዋሪያ የመሆኛ መንገድ ደግሞ መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ እንዳለው ማድረግ ነው፡፡ይህም ማለት የየለት ተለት የሕይወት ጥቄዎቻችንን በትግስት መመለስን ብቻ ሳይሆን በእምነት እና በሃላፊነት ድካምን እና መከራን መሻገር ነው፡፡
ስለዚህም መስቀላችንን ተሸክመን ክርስቶስን የመከተል መሰጠታችን በክርስቶስ የዓለም አዳኝነት ተሳታፊ ያደርገናል፡፡ይህንን በምናስብበት ጊዜ እርግጠኛ መሆን ያለብን፥በየቤታችን ግርግዳ እና አንገታችንም ላይ የምናደርገው መስቀል፤ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን በፍቅር በማገልገል ከክርስቶስ ጋር ሕብረትን የምንፈጥርበት የአንድነት ምልክት ነው፡፡መስቀል የእግዚአብሐር ፍቅር እና የክርስቶስ መሥዋትነት የታየበት የተቀደሰ የድነታችን መሳሪያ ነው፡፡በመሆኑም እንደ ጌጥ በማድረግ ፋይዳውን ማሳነስ አይገባም፡፡ሁል ጊዜም የተሰቀለውን የክርስቶስን ምስል በምንመለከትበት ወቅት፤እርሱ እንደ እውነተኛው የእግዚአብሔር አገልጋይ፣እራሱን ስለሌሎች አሳልፎ በመስጠት ዓላማውን እንደፈጸመ እና ሐጥያታችንን በደሙ ያጠበ ስለመሆኑ እናስባለን፡፡በመሆኑም የክርስቶስ ተከታይ መሆን ከፈለግን፥እርሱን እንድንመስል እና ያለምንም ማንገራገርም ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር እንዲሁም ለሌሎች እንድንሰጥ ተጠርተናል፡፡
እስከ መስቀል ሞቱ ድረስ የተጓዘችው ድንግል ማሪያም የክርስቶስን አዳኝነት ከመመስከር የሚመጣ መከራ እንዳናሸነፍ እርሷ በአምልጅነቷ ትርዳን።