የዶን ቦስኮ ሳሌዝያን ገዳም በኢትዮጵያ የተመሰረተበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤሊዩ ተከበረ
አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. በ 1859 ዓ.ም. በሰሜናዊ ጣሊያን በምትገኘው ቱሪን ከተማ በትሁቱ ጣሊያናዊ ካህን ቅዱስ ዮሃንስ ቦስኮ የተመሰረተው የዶን ቦስኮ ሳሌዝያን ገዳም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ አገልግሎት ከጀመረ ሃምሳ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፥ ይሄንን አስመልክቶ የገዳሙ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ ክብረ በዓል ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እና ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመቂ ሃገረ ስብከት ጳጳስ አዲስ አበባ በሚገኘው የክርስቲያኖች ረዳት ማሪያም ቁምስና ውስጥ በጋራ በመሩት የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ በደማቅ ሥነ ስርዓት ተከብሯል።
በዕለቱ በተካሄደው የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የሳሌዝያን ገዳም የበላይ አለቃ አባ እግናሲዮ ላቬንቱሬ፣ አባ ሃይለማሪያም መድህን በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የሳሌዝያን ገዳም አለቃ፣ ከገዳሙ የመጀመሪያዎቹ ልኡካን ውስጥ አንዱ የሆኑት ወንድም ቼዛሬ ቡሎ፥ በርካታ የሳሌዝያን ካህናት እና ወንድሞች፣ የተለያዩ ገዳማዊያት እና ገዳማዊያን፣ ምዕመናን እና ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ በዕለቱ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን “የቀድሞ አባቶቻችን ከቅዱስ ዮሀንስ ቦስኮ የተቀበሉትን እምነት እና መንፈሳዊነት አውርሰውናል” ያሉ ሲሆን፥ በቁጥር ለመግለጽ በሚያዳግት ደረጃ በርካቶች በተለይም ወጣቶች እና ህፃናት በዶን ቦስኮ ጥላ ስር ማደጋቸውን አስታውሰው፥ ብፁዕነታቸው ከዛሬ 50 ዓመት ጀምሮ ያለመታከት ያገለገሉትን አባቶች እና አገልጋዮችን አመስግነዋል።
ዶን ቦስኮ በቅዱስ ፍራንሲስ ደ ሳሌስ በጎነት እና መልካምነት በመነሳሳት በወቅቱ በነበረው የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ምክንያት ወደ ከተሞች የሚሰደዱትን ወጣቶች ችግር ለመፍታት በማሰብ ጉባኤውን ያቋቋመ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት ገዳሙ እና ተከታዮቹ በቅዱስ ደ ሳሌስ (ሳሌዝያን) እንዲጠሩ አድርጓል።
በዶን ቦስኮ ሳሌዝያን ገዳም በኢትዮጵያ የሃምሳ ዓመታት አገልግሎት ውስጥ በተለይ በትግራይ ክልል ከሚገኙ የሳሌዝያን ገዳማት፣ አቢያተ ክርስቲያናት፣ መለስተኛና ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች እና የገዳሙ ተቋማት ኪነ ህንፃዎች ጀርባ፥ እንዲሁም ከበርካታ ሰብአዊ እርዳታዎች እና ማህበራዊ አገልግሎቶች በዋናነትም ከአርባ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ወቅት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል እርዳታ በማስተባበር የሚታወቁት እና ገዳሙ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከመጀመሪያዎቹ ልኡካን ውስጥ አንዱ የነበሩት ወንድም ቼዛሬ ቡሎ በህይወት ቆይተው ለበዓሉ ድምቀት የሆኑ ሲሆን፥ ከመጀመሪያዎቹ ሚሲዮናውያን አንዱ የሆኑት ወንድም ቼዛሬ አሁንም ድረስ ጎተራ በሚገኘው የዶን ቦስኮ ሳሌዚያን ገዳም በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በወቅቱ የነበሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጋፍጠው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የሳሌዝያን ገዳምን የመሰረቱት የመጀመሪያዎቹ ገዳማውያን ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ትልቅ መሰረት መጣላቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ፥ አሁን ያለው ትውልድ የእነሱን ፈለግ ተከትሎ መበርታት እንደሚገባው እና ይህም የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ለዚህ ብርታት ጥሪውን ያቀርባል በማለት አሳስበዋል።
የቅዱስ ዮሀንስ ቦስኮ ገዳም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓል ከአዲስ አበባም በተጨማሪ ገዳሙ የመጀመሪያውን የገዳማዊያን ቤት በከፈተበት መቀሌ በሚገኘው ልደታ ለማርያም ቁምስና ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ጳጳስ በመሩት የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ በድምቀት የተከበረ ሲሆን፥ በወቅቱ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ተስፋስላሴ በመርሃ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ የሳሌዝያን ገዳምን የመሰረቱትን የመጀመሪያዎቹን መስራቾች አመስግነው፥ ብፁዕነታቸው በተለይም ሀገረ ስብከቱ ባሳለፈው ከባድ ወቅት ገዳሙ ላሳየው አብሮነት ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
እ.አ.አ. ከ 1975 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ማገልገል የጀመረው የሳሌዝያን ዶን ቦስኮ ገዳም በተለይ በአዲስ አበባ በማኅበራዊ ሥራዎች በንቃት የሚንቀሳቀስ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፥ ገዳሙ ከሚሰጣቸው የመደበኛ የትምህርት መርኃ ግብሮቹ በተጨማሪ በተለይም በበርካታ ክህሎቶች እና ሙያዎች ተማሪዎች የአጭር እና ረጅም ጊዜ ስልጠና የሚወስዱበት የቴክኒክ እና ሙያ ተቋም በመገንባት ለበርካታ ወጣቶች ህይወት መለወጥ ምክንያት ሆኗል።
ይህ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያ በተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ታዳጊ ህፃናትን ራሳቸውን በትምህርት እና ሙያ ስልጠና እንዲያጎለብቱ፣ ብሎም ራሳቸውን እንዲችሉ እና ባለሙያ ሆነው በአምራችነት እግዚያብሄር ወደሰጣቸው ቤተሰብ ወይም ማህበረሰብ እንዲቀላቀሉ፥ በተለይም የቴክኒክ እና ሙያ የትምህርት ዘርፎች ለበርካታ ዓመታት ማሰልጠኑ ይታወቃል።
የቅዱስ ዮሀንስ ቦስኮ ሳሌዝያን ገዳም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ134 በላይ ሀገራት ውስጥ እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን፥ በብፁዕ አቡነ ስብሀትለአብ ወርቁ ግብዣ በ1968ዓ.ም. በሶስት ሚሲዮናውያን አማካይነት በኢትዮጵያ፣ መቀሌ ላይ የመጀመሪያውን ቤት በመክፈት አገልግሎት የጀመረው ገዳሙ፥ጉዞውን በመቀጠል በዲላ፣ አዲግራት ጎልዓ፣ በዝዋይ፣ በአዲስ አበባ ጎተራ፣ በአድዋ፣ በኤርትራ ደቀምኃረ፣ በመካኒሳ፣ በቢሾፍቱ፣ በጋምቤላ፣ በአዳሚቱሉ፣ በአስመራ፣ በባረንቱ፣ በሽሬ እና በወላይታ ሶዶ በመክፈት የገዳሙን አገልግሎት ማስፋፋት እንደቻለ ተገልጿል።
የሳሌዝያን ገዳም ለሃምሳ ዓመታት ያክል በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውስጥ የዶን ቦስኮን ፈለግ በመከተል እና በታማኝነት በመጋራት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ወጣቶች ህይወት በመለወጥ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 1975 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን ወደ መቀሌ ከመጡ በኋላ ተልእኮው በቁርጠኝነት፣ በመስዋዕትነት እና በማያወላውል መልኩ ለወጣቶች ትምህርት እና ሁለንተናዊ ልማት በተለይም በድሆች እና በጣም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በማገልገል የቅዱሱን ራዕይ አስቀጥለዋል።