በችግር እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን የሚረዳው የካቶሊ የእርዳታ መስጫ ተቋም ድጋፍ ማድረጉን ቀጥሏል
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
‘በስደት፣ በችግር እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት የሚረዳው የካቶሊ የእርዳታ መስጫ ተቋም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን አቢያተ ክርስቲያናትን የሚያግዝ ጳጳሳዊ ተቋም ሲሆን፥ በፖላንድ የሚገኘው የዚህ ተቋም ቅርንጫፍ በአሁኑ ወቅት በሶርያ፣ ሊባኖስ፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በቅድስት ሀገር እና ዩክሬን ውስጥ የሰብዓዊ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በፖላንድ የተቋሙ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር የሆኑት አባ ጃን ዊቶልድ ዘሌዝኒ ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ የፋውንዴሽኑን ቀጣይ ጥረት እና ቁርጠኝነት በዝርዝር አመላክተዋል።
ተስፋው ተጨባጭ መሆኑ
‘‘በስደት፣ በችግር እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት የሚረዳው የካቶሊ የእርዳታ መስጫ ተቋም ተገኝቶ በሚሰራባቸው ቦታዎች ሁሉ መገኘት እንፈልጋለን” ያሉት ዳይሬክተሩ፥ ይህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእርዳታ ተቋም ሰዎች በጦርነት እና በስደት በሚሰቃዩበት ቦታ ሁሉ በመገኘት ድጋፍ የማድረግ ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን፥ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን እነዚህን ሰዎች ለማገዝ ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸው፥ በሚቀጥሉት ሳምንታት የፋውንዴሽኑ ተወካዮች ተቋሙ ለዓመታት የክርስቲያን ማህበረሰቦችን ሲያግዝ በነበሩባቸው ሶሪያ እና ሊባኖስ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዱን ጠቁመዋል።
የተቋሙ ተወካዮች መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በቫቲካን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት ብፁዕነታቸው ከተወካዮቹ ስለ ሃይማኖታዊ ነፃነት ሪፖርት ተቀበለው፥ ድርጅቱ በሚሰራው ሥራ ላይ ስላለው ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን ስደት ከሚደርስባቸው ምዕመናን ጎን እንደምትቆም ያረጋገጡ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ “የሃይማኖት ነፃነት መብት ብቻ ሳይሆን እውነተኛ እርቅ እንዲኖር የሚያስችል መሠረት ነው” ሲሉ አጽንዖት በመስጠት ተናግረዋል።
በድንበሮች ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች
‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢን ኒድ’ በአሁኑ ወቅት እየተገበራቸው ከሚገኙት ተነሳሽነቶች መካከል በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በናይጄሪያ ውስጥ ያሉ ፕሮጀክቶቹ የሚጠቀሱ ሲሆን፥ እነኚህ አከባቢዎች በተለያዩ ግጭቶች እና በስፍራው የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን በቁጥጥር ሥር ለማድረግ በሚደረጉ ትግሎች ምክንያት ስቃይ እየደረሰባቸው የሚገኙ በርካታ ሰዎች ያሉበት አከባቢ ሲሆን፥ ይህ ለናይጄሪያ የሚደረገውን የእርዳታ ፕሮጄክቶችንም እንደሚመለከት እና በመጪው ታህሳስ ፖላንድ ውስጥ የሚከበረው የአንድነት ቀን ለናይጄሪያ መታሰቢያ እንደሚሆንም ጭምር ጠቁመዋል።
ለዚህ ክብረ በዓል ወደ ፖላንድ ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ሰዎች መካከል በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት ምክንያት የሞት ዛቻ ከደረሰባቸው አባቶች አንዱ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጆን ባኬኒ ይገኙበታል ተብሏል።
በፖላንድ የ‘‘በስደት፣ በችግር እና በስቃይ ውስጥ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት የሚረዳው የካቶሊ የእርዳታ መስጫ ተቋም ቅርንጫፍ ዳይሬክተር የሆኑት አባ ዘሌዝኒ የተቋሙ በጎ ፈቃደኞች ከቅድስት ኤልሳቤጥ እህቶች ማህበር ጋር በመሆን በጦርነት የተጎዱ ሕፃናትን በሚንከባከቡበት በቤተልሔም ከተማ ውስጥም ተቋማቸው እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፥ “ተቋማችን ይሄንን ድጋፍ ባያደርግ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ክርስትና ይጠፋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር ድርጅታቸው ምንም እንኳን አስጊ ሁኔታዎች ቢኖሩም ወደ ዩክሬን በመጓዝ፣ በዋናነት በኦዴሳ እና በአካባቢው በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ በሚተገብሩት የእርዳታ እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ በቅርቡ የታተመውን ‘ዳይሌክሲ ቴ’ የተሰኘውን ሃዋሪያዊ ማሳሰቢያ ጨምሮ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።
ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አካላት
ፋውንዴሽኑ ከዚህም በተጨማሪ በፖላንድ ውስጥ ንብረቶቻቸውን ያጡ ገዳማትን የሚረዳ ፕሮጀክት ያለው ሲሆን፥ በዚህም ፕሮጄክት የነፍስ ወከፍ ልገሳ መላክን ጨምሮ መተዳደሪያ የሌላቸውን ገዳማትን እንደሚደግፉ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፥ በአከባቢው የሚገኙ እህቶች ይህ ድጋፍ በጣም ጠቃሚ እና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚነግሯቸው ገልጸዋል።
የተቋሙ የፖላንድ ቅርንጫፍ ኃላፊ እያንዳንዱ ልገሳ የሚከናወነው በጥንቃቄ እና በግልፅ እንደሆነ አረጋግጠው፥ በፖላንድ የሚገኘው ይህ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን የአፍሪካ እና ኢስያ የክህነት ምስረታንም እንደሚደግፍ ገልጸዋል።
“በካሜሩን የሚገኙ አንድ ጳጳስ 600 ዩሮ ከሰጡኝ አንድ ተጨማሪ የክህነት ተማሪ ልቀበል እችላለሁ” እንዳሏቸው ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፥ እኛ ስለ ካህናት እጥረት እናማርራለን፥ ነገር ግን እሳቸው ወደ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቱ የሚቀበሉት የእጩዎች ቁጥር በምንሰጠው ድጋፍ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ነግረውኛል’ ያሉ ሲሆን፥ ይህ የሚያመላክተው በአካባቢውም ሆነ ሌላ ቦታ የካህናት ምስረታ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።
ለተግባር የተደረገ ጥሪ
በቫቲካን በተደረገው ስብሰባ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የተቋሙ ሥራ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ልምድ የመነጨ መሆኑን ያስታወሱ ሲሆን፥ ይህም ተግባር ቁስሎችን ለመፈወስ እና እጆችን ለሰላም በመዘርጋት ድጋፍን ስለመስጠት እንደሆነ የጠቆሙት አባ ዘሌዝኒ፥ በመጨረሻም የተቋሙ ተልዕኮ የተመሰረተው የይቅርታ መሠረት ባለው ከዚህ አስተሳሰብ እንደሆነ፥ ብሎም በድህነት ጊዜ የሚረዳ ብቻ ሳይሆን ይቅርታንም በሚያስተምር ፍቅር እንደሆነ በመግለጽ አጠቃለዋል።