ሊቀ ጳጳስ አንቶኒ ሙሄሪያ ለብሔራዊ የጸሎት ቀን በሱቡኪያ ቤተ መቅደስ የተገኙትን ሰዎች ሲባርኩ ሊቀ ጳጳስ አንቶኒ ሙሄሪያ ለብሔራዊ የጸሎት ቀን በሱቡኪያ ቤተ መቅደስ የተገኙትን ሰዎች ሲባርኩ  

የኬንያ ብፁዓን ጳጳሳት በብሔራዊ የጸሎት ቀን ሃገሪቷን ለአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም አደራ መስጠታቸው ተገለጸ

በኬንያ ናኩሩ ሃገረ ስብከት ሥር በሚገኘው የሱቡኪያ ብሄራዊ የቅድስት ድንግል ማሪያም ቤተ መቅደስ ውስጥ “በተስፋ ነጋዲያን ሀገራችንን ማደስ” በሚል መሪ ቃል በተከበረው ዓመታዊው ብሔራዊ የጸሎት ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን የተሰባሰቡ ሲሆን፥ በዚህም ቀን የሃገሪቷ ብፁዓን ጳጳሳት ሃገሪቷን የቤተክርስቲያን እናት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትጠብቅ አደራ መስጠታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በናይሪ ሊቀ ጳጳስ አንቶኒ ሙሄሪያ የተመራው የቅዱስ ቁርባን ስግደት ከመላው ኬንያ የተውጣጡ ብፁዓን ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ገዳማዊያትን እና ምዕመናንን በጸሎት፣ በማሰላሰል እና ለሀገራዊ ህዳሴ ቃል በመግባት በዕለቱ በተካሄደው መስዋእተ ቅዳሴ ላይ ተሳትፈዋል።

ኬንያ የክርስቶስ እናት ለሆነችው ቅድስት ማርያም መሰጠቷ
የኪሱሙ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የኬንያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር ሊቀ ጳጳስ ሞሪስ ሙሃቲያ ሃገሪቷ የጌታ እናት ለሆነችው በቅድስት ድንግል ማሪያም ጥበቃ፣ አማላጅነት እና የእናትነት እንክብካቤ ሥር እንድትሆን አደራ የተሰጠችበትን የጸሎት ሥነ ስርዓት የመሩ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ይህ ተግባር የማሪያምን የቤተ ክርስቲያን እናትነት እና የሰላም ንግሥትነት ሚና ላይ ያለውን ጥልቅ እምነት ያሳያል ብለዋል።

የኬንያ ብፁዓን ጳጳሳት ሀገሪቱ ውስጥ በሚታየው የጨለማ፣ ሙስና እና ኢፍትሃዊነት ተግባራት ምክንያት ለመለኮታዊ መመሪያ እና መሪነት የማርያምን አማላጅነት በመጠየቅ፥ ብሎም በሰዎች መካከል የታማኝነት እና የማህበራዊ ንቃተ ህሊና መንፈስን ለማዳበር የማርያምን ጥበቃ እና የእግዚአብሔር ብርሃን እንዲሰፍን በመጠየቅ ጸሎት አድርገዋል።

ለኬንያ ወጣቶች የተሰጠ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ
የኪሱሙ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሙሃቲያ ከኬኒያ ብፁዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለወጣቶች የተላከውን ሃዋሪያዊ ደብዳቤ ባነበቡበት ወቅት ወጣቶቹን “የተስፋ ዋና ተዋናዮች” በማለት የጠሩ ሲሆን፥ ወጣቶች በተስፋ፣ በእምነት እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ውስጥ እንዲነሳሱ እና እንዲቃኙ አሳስበዋል።

ወጣቶች ግልጽ የሆነ የገነት መዳረሻ ያላቸው የተስፋ ነጋዲያን መሆናቸውን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ “እግዚአብሔር አለ፤ እኛም ልጆቹ ነን፣ ክርስቶስም ሕያው ሆኖ በመካከላችን አለ” ያሉ ሲሆን፥ እርሱ ንድፈ ሐሳብ ወይም የሕይወት መርህ ሳይሆን እርሱ ራሱ ሕይወት ነው” በማለት ሃዋሪያዊ ደብዳቤውን በመጥቀስ ተናግረዋል።

ደብዳቤው በአምስት ዋና ዋና ጭብጦች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፥ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ያለን ማንነት፣ በታሪካችን ከክርስቶስ ጋር መገናኘት፣ የሞራል ድፍረት እና ንፅህና፣ ከስብራት ወደ ተስፋ እና ስለ ኬንያ ተስፋ ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።

በቅርቡ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቅድስናው የታወጀለት ቅዱስ ካርሎ አኩቲስን በመጥቀስ “ሁሉም ሰዎች እንደ ዋናው ቅጂ ተወልደው፣ እንደ ግልባጭ ወይም ‘ፎቶ ኮፒ’ ሆነው ይሞታሉ” ያሉ ሲሆን፥ “ወጣቶቹ የቤተክርስቲያኑ ዋና ቅጂ ወይም ኦሪጅናል ሰዎች በመሆናችሁ እንኮራባችኋለን” ካሉ በኋላ በተስፋ፣ በእምነት እና በበጎ አድራጎት ውስጥ የለውጡ ዋና ተዋናይ ሆነው እንዲነሳሱ እና እንዲሳተፉ በድጋሚ አሳስበዋል።

ወጣቶች የእግዚአብሔርን ድምጽ እንዲያሰሙ እና እንዲወዱ የጋበዙት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህንንም በማድረጋቸው የህይወትን ትርጉም እንዲያገኙ እና ሳምራዊቷ ሴት ከኢየሱስ ጋር በውሃ ጉድጓድ አጠገብ ስለተገናኘችበት ታሪክ ጋር ጉዞ እንዲያደርጉ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህል እና ከሃይማኖታዊ ጭፍን ጥላቻ የዘለለ እንደነበር ጠቅሰው፥ ወጣቶች እራሳቸውን እንደ ጎሳቸው ወይም ትውልዳቸው እንዳይመለከቱ፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የልብ ግልጽነት እና የመኖር ጥበብ ልዩ ውጤት አድርገው እንዲመለከቱ አሳስበው፥ “እያንዳንዳችሁ በእናት ሀገራችን ውስጥ የለውጡ ዋና ተዋናይ ናችሁ” በማለት አበረታተዋል።

የተስፋ መልዕክት
የኢምቡ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ፒተር ኪማኒ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ “እግዚአብሔር በአገራችን ውስጥ ድንኳኑን በመትከል በምናልፍባቸው ልዩ ልዩ ፈተናዎች ውስጥ እንኳን እርሱ እንዳለን የሚያሳይ ምልክት እንዲሆን አድርጓል” ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አገሪቷ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራ መሰጠቷ ኬንያውያን አማላጅ እንዳላቸው እና በቃና ዘገሊላ የወይን ጠጅ ባለቀበት ጊዜ ትዳሩን እንዳደሰችው ሁሉ ህይወታቸውን እንደምታድስ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

“ተስፋ መኖሩን እናም ተስፋ ማድረግ እንደማያሳፍር” የገለጹት ጳጳሱ ይህም ይሆን ዘንድ ከየት እንደመጣን እና የእግዚአብሔር አምሳያ እንደሆን ለሕዝብ ሁሉ ማሳየት እንደሚገባ እንዲሁም የኬኒያ ወጣቶች ከቤታቸው እና ከልባቸው ጀምሮ እስካሉበት ቦታ ድረስ መተማመን፣ እውነት፣ ታማኝነት፣ ፍቅር፣ ሰላም እና ተስፋ ሊገኙ የሚችሉበት አድርገው ሀገራቸውን ለሌሎች ሃገራት ተምሳሌት አድርገው ማሳየት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአንድነት መቆየት
ብፁዕ አቡነ ኪማኒ ከዚህም በተጨምሪ ወጣቶች በእምነት ተሰባስበው አንድ እንዲሆኑ እና እርስ በርስ የሚደማመጡበት አካባቢ እንዲፈጠር ብሎም እግዚአብሔር የሚነገራቸውን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንዲሰሙ፣ በፖለቲካም ሆነ በባህል መካከል ያለውን ሰብአዊ መለያየት እንዲቃወሙ የጋበዙ ሲሆን፥ በኬንያዊያን መካከል በሚታዩ ክፍፍሎች ውስጥ ሰላም፣ አንድነት እና ፈውስ ትልቅ ጉልበት እንዳለ ገልጸው፥ ማንም ሰው ወደ ኋላ እንዳይቀር የጋራ ጥቅም ከጠባብ ፍላጎቶች በላይ መሆን እንዳለበት፣ እንዲሁም እርቅ ትህትና እና ውይይትን የሚጠይቅ ሂደት መሆኑን አስረድተዋል።

የወጣቶች ጥሪ
ወጣቶች የእምነት ምስክሮች ሆነው የዓለም እና የሀገር መታደስ ምልክቶች መሆናቸውን የገለጹት ብፁዕነታቸው፥ ወጣቶቹ የተስፋ ምልክት እንደሆኑ እና ክርስቶስን የህይወታቸው ማዕከል አድርገው መፈለግ እንደሚገባ አሳስበው፥ ቅዱስ ካርሎ አኩቲስ ቅድስና በወጣትነት ዕድሜ እንደሚቻል በህይወቱ መመስከሩን አስታውሰዋል።

ብፁዕ አቡነ ኪማኒ በመጨረሻም ወጣት ኬንያውያን ሌሎችን ለማካተት የፍላጎት ምንጭ እንዲኖራቸው ቤተሰቦቻቸውን ማስቀደም እንደሚገባ በማበረታታት አጠቃለዋል።

07 Oct 2025, 14:00