የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች  

ካርዲናል ኩፒች ‘ኪፕ ሆፕ አላይቭ’ ተብሎ በሚታወቀው ሽልማት ላይ ለተነሳው ውዝግብ ምላሽ ሰጡ

‘ኪፕ ሆፕ አላይቭ አዋርድ’ ተብሎ በሚታወቀው የሽልማት መርሃግብር ላይ የተነሳውን ክርክር ተከትሎ የቺካጎው ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች በሰጡት መግለጫ፥ ሌሎች ሰዎች ማህበራዊ ፍትህን ለማስፋፋት ለሚሰሩት ሥራዎች እውቅና መስጠት እንደሚገባ ብሎም አማኞች መቻቻል እና ትዕግስትን እንዲያዳብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ ዘላለም ኃይሉ

ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታየ ባለው የጽንፈኝነት ወይም የመከፋፈል አመለካከቶች የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸው፥ በጵጵስና የቆዩበትን 27 ዓመታት ጨምሮ በክህነት ያገለገሉበትን 50 ዓመታት በማስታወስ፥ በካቶሊክ ማህበረሰብ ውስጥ ያለው መከፋፈል “በአደገኛ ሁኔታ እየጠነከረ ሲሄድ” መመልከታቸውን አመላክተዋል።

እነዚህ ክፍፍሎች ‘የቤተ ክርስቲያን አንድነትን እና የወንጌል ሥርጭትን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳሉ’ ያሉት ካርዲናሉ፥ ብፁዓን ጳጳሳት ይሄንን ችግር በቀላሉ ችላ ብለው ሊያልፉት የሚገባ ጉዳይ እንዳልሆነ ጠቅሰው፥ ምክንያቱም አንድነትን የማሳደግ እና ሁሉም ካቶሊኮች የቤተክርስቲያንን አስተምህሮዎች በአጠቃላይ እንዲቀበሉ የመርዳት ግዴታ አለብን ብለዋል።

ካርዲናል ኩፒች በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር ዲክ ደርቢን ለኪፕ ሆፕ አላይቭ ሽልማት (Keep Hope Alive Award) መታጨታቸውን ተከትሎ የተነሳውን ክርክር በመጥቀስ የጉዳዩን አደገኛነት አሳስበዋል።

ሁሉንም መቃወም አይገባም
የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ ሴናተር ደርቢን በስደተኞች ፖሊሲ ላይ ለሚሰሩት ሥራ እውቅና ለመስጠት ማቀዳቸውን የጠቆሙት ካርዲናሉ “ሴናተሩ ሽልማት እንዲሰጣቸው የተወሰነው በዚህ ዘመን በጣም አስፈላጊ በሆነው በተለይ በስደተኞች ፖሊሲ ማሻሻያ ላበረከቱት አንድ አስተዋጽዖ እና ለስደተኞች ላደረጉት የማያወላውል ድጋፍ እንደሆነ አመላክተዋል።

ሴናተሩ ለሽልማቱ መታጨታቸውን የሚገልጽ መግለጫ ተከትሎ በርካታ የአሜሪካ ብፁዓን ጳጳሳትን ጨምሮ አያሌ የካቶሊክ ማህበረሰብ አባላት የኢሊኖይ ዲሞክራቱ ሴናተር ደርቢን ሕጋዊ ውርጃን ይደግፋሉ በሚል ሰበብ በቺካጎ ሊቀ ጳጳስ ውሳኔ ተቃውሞአቸውን የገለጹ ሲሆን፥ በዚህም የተነሳ ሴናተር ደርቢን ሽልማቱን ላለመቀበል መወሰናቸው ተነግሯል።

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በሰጡት መግለጫ ይህ ሁኔታ የዓለማችንን እውነታ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ጠቁመው፥ በተለይም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በርካታ ካቶሊኮች በፖለቲካው ምክንያት ቤት አልባ መሆናቸውን አንስተው፥ “የሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲ ፖሊሲዎች የካቶሊክን አስተምህሮ ስፋት በትክክል አይሸፍኑም” በማለት አስረድተዋል።

ካርዲናል ኩፒች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት የተከሰተውን ህመም አስታውሰው ይህ ችግር በቤተክርስቲያኒቷ እና በአሜሪካ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን መጠነ ሰፊ ፈተና እንደሚያንፀባርቅ በመግለጽ፥ አንድ የፖለቲካ መሪ የካቶሊክን አስተምህሮ ክፍሎች የሚቃወሙ አመለካከቶችን በያዘ ቁጥር ትልቁ ፈተና የሚሆነው ለማውገዝ ማፈግፈግ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ውይይትን ከማጎልበት ይልቅ መከፋፈልን እንደሚያመጣ አስጠንቅቀዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ኩፒች በሌሎች ጉዳዮች ላይ አለመስማማት ቢኖርም እንኳን አንዳንድ መልካም ሰዎች ለሚሰሩት ሥራ ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፥ ‘ሰዎች ለሰሩት መልካም ሥራ ማመስገን ለማሰላሰል እና ለመተባበር በር ሊከፍት ይችላል’ ካሉ በኋላ፥ ካቶሊኮች ግለሰቦች የሚያደርጉትን አስተዋፅዖ በመገንዘብ ለእድገት፣ ለጋራ ትምህርት እና ለጋራ ጥቅም የጋራ ቁርጠኝነትን መፍጠር ይችላሉ በማለት አስረድተዋል።

ሁሉም እርስ በእርሱ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል
ስለ ‘ኪፕ ሆፕ አላይቭ’ ሽልማት መርሃ ግብር ያነሱት ካርዲናል ኩፒች፥ የመርሃ ግብሩ ዓላማ ለጋራ መተሳሰብ የሚሆን ቦታ መፍጠር እንደሆነ ጠቅሰው፥ በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ ለስደተኞች የሚሟገቱት ካቶሊኮች፣ ቤተክርስቲያን በማህፀን ውስጥ ስላለው ህይወት የምታደርገውን ጥበቃ ጭምር እንደሚደግፉ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በማህፀን ውስጥ ለሚገኝ ጽንስ ጥበቃ እንዲደረግ የሚሟገቱ ሰዎች የተሟጋችነት ተግባራቸውን በማስፋት፣ የመኖር ህልውና ስጋቶችን በመሸሽ ለሚሰደዱ ስደተኞችም ጭምር መሟገት እንደሚገባ አሳስበው፥ “ሁለቱም ቡድኖች ካቶሊኮች ስለሆኑ” ቤተክርስቲያን በአንድ ጉዳይ ብቻ እንደማትገለጽ መዘንጋት የለበትም በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ካርዲናል ኩፒች ይህ ክስተት ቤተክርስቲያኗ ፅንስ በማስወረድ ላይ ያላትን አቋም እንደ ማዳከም ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ መተርጎም እንደሌለበት ያሰመሩበት ሲሆን፥ የቤተክርስቲያን አስተምህሮን በመጥቀስ ፅንስ ማስወረድ የሞራል ክፋት እንደሆነ እና ቤተ ክርስቲያን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የምታስተምረው ትምህርት “የማይለወጥ” መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጡ ሲሆን፥ ‘ቤተክርስቲያን የሰውን ልጅ ሕይወት ለመጠበቅ ሕጎችን እንዲሁም የእምነት ነፃነት መብትን ማስከበሯን ትቀጥላለች’ ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ብፁዓን ጳጳሳት ‘ሮ ቪ ዋድ’ ተብሎ የሚታወቀው እና እ.አ.አ. በ 1973 ዓ.ም. የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕገ መንግሥቱ ፅንስ የማስወረድ መብትን እንደሚጠብቅ የወሰነበትን አስደናቂ ውሳኔ የሰጡትን ጠንካራ ምላሽ በማስታወስ፥ የብፁዓን ጳጳሳቱ ምላሽ በማህፀን ላሉ ሕፃናት ያላቸውን የማያወላውል ጥበቃ እንደሚያመላክት ጠቁመው፥ ከዚህም በተጨማሪ ቤተክርስቲያን ለስደት ያላትን የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት አጽንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፥ በመጨረሻም “ተስፋ ማድረግ ከቀጠልን ወደፊት መራመድ እንችላለን” በማለት አጠቃለዋል።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስተያየት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጠኛ ጉዳዩን አስመልክቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ አንድ ሴናተር በዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት ውስጥ ለ40 ዓመታት ሲያገለግል በቆየበት ወቅት የሚሰራውን አጠቃላይ ሥራ መመልከት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ምንም እንኳን ችግሮሽ እና ውጥረቶች ቢኖሩም፥ ከቤተክርስቲያን ትምህርት ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮችን ማጤን አስፈላጊ እንደሆነ በአጽንዖት ገልጸዋል።

የሞት ቅጣትን እየደገፈ ወይም በአሜሪካ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ኢሰብአዊ ድርጊትን ዝም ብሎ እየተመለከተ፥ በአንፃሩ “ፅንስ ማቋረጥን እቃወማለሁ” ማለቱ በእውነት የህይወት ደጋፊ እንዳልሆነ ያሳያል በማለት አስምረውበታል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እነዚህ በጣም ውስብስብ ጉዳዮች እንደሆኑ አስታውሰው፥ ‘ማንም ሰው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሙሉ መረጃ እንዳለው ባላውቅም፥ ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ እንደ አሜሪካዊ ወይም ኢሊኖይ ዜጎች እንዲሁም እንደ ካቶሊኮች፥ ከምንም በላይ እንደ ሰው የበለጠ መከባበር እንዲኖር እጠይቃለሁ’ ያሉ ሲሆን፥ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የቤተክርስቲያን ትምህርት በጣም ግልፅ ስለሆነ 'እነዚህን ሁሉ የሥነ ምግባር ጉዳዮች በቅርበት መመልከት እና እንደ ቤተ ክርስቲያን ወደፊት መፍትሄውን መፈለግ ይኖርብናል' ብለዋል።

02 Oct 2025, 14:04