ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ የጋዛ ስምምነት 'ወደ ተስፋ የሚወስደን የመጀመሪያ እርምጃ ነው' ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በጋዛ ሰርጥ የሚካሄደው ጥቃት እንዲቆም እንዲሁም በሃማስ የተያዙ ታጋቾችን እና የፍልስጤም እስረኞችን በአስቸኳይ እንደሚፈቱ የሚገልጸው ስምምነት ይፋ መደረጉን በደስታ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።
በእየሩሳሌም የሚገኙት የላቲን ፓትርያርኩ ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ መድረሳቸው ከተገለጸ በኋላ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እና በታማኝነት ተፈፃሚነት እንደሚኖረው ያላቸውን ‘ጽኑ ተስፋ’ ገልጸው፥ ይህ ስምምነት “የዚህ አስከፊ ጦርነት ማብቂያ ጅምር” እንደሚሆን ያላቸውን እምነት አስረድተዋል።
ፓትሪያርኩ በመግለጫቸው በጋዛ እየተሰቃየ ለሚገኘው ህዝብ ሰብአዊ እርዳታን መፍቀድ እና በቂ ዕርዳታ ያለ ቅድመ ሁኔታ መግባቱን ማረጋገጥ ‘ፍፁም አስቸኳይ’ መሆኑን አጉልተው በማሳየት፥ “ከምንም በላይ ይህ እርምጃ ለፍልስጤማውያን እና ለእስራኤላውያን የፈውስ እና የእርቅ መንገድ እንዲከፍት እንጸልያለን” ብለዋል።
መንበረ ፓትርያርኩ በድርድሩ ላይ የተሳተፉትን ሁሉ እንደሚያመሰግን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ “ይህ ስምምነት እንዲደረግ ያላሰለሰ ጥረት በማድረጋቸው” ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የመጀመርያው ምዕራፍ በጋዛ ያለውን ግጭት ለማስቆም መንገድ የሚከፍት ሲሆን፥ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ በከፊል ለቀው የሚወጡበት እና በሐማስ ተይዘው ያሉት ታጋቾች በሙሉ የሚለቀቁበት እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ስምምነቱ ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ይፋ ባደረጉት ባለ 20 ነጥብ እቅድ ላይ የተመሰረተ ነው ተብሏል።
“የመጀመሪያ ደረጃ ግን አስፈላጊ”
የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ስምምነቱን “መልካም ዜና” እንደሆነና ስምምነቱን ‘ረጅሙ የሰላም መንገድ የመጀመሪያው እርምጃ’ በማለት የገለጹ ሲሆን፥ ከሁለት ዓመታት ስቃይ በኋላ ለሁሉም የሚሆን መልካም ዜና መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህም በጣም ደስተኛ እንደሆኑ እና ትልቅ እፎይታም እንደሆነ ገልጸዋል።
ብፁዕ ካርዲናሉ አክለውም ብዙ ተጨማሪ ርምጃዎች እንደሚቀሩ እና በእርግጥም ተግዳሮቶች እንደሚኖሩ ገልጸው፥ ነገር ግን በዚህ ጠቃሚ እርምጃ የተሰማቸውን እፎይታ በድጋሚ ገልጸዋል።
“ከፊታችን ያለው መንገድ ረጅም እንደሆነ እናውቃለን” ያሉት ፓትሪያርኩ፥ ብዙ መሰናክሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ እና አፈፃጸሙ ቀላል ባይሆንም፥ ነገር ግን በእስራኤል እና በፍልስጤም በተለይም በጋዛ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ቤተሰቦች መተማመንን እና አልፎ ተርፎም ደስታን የሚፈጥር እጅግ አስፈላጊ የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከተኩስ አቁም ባሻገር ያለውን መመልከት
ፓትርያርኩ በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ተግዳሮቶች ከቫቲካን ዜና ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ከዚህ በኋላ በሚመጣው ጉዳይና አተገባበሩ ላይ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፥ ነገር ግን ተደራዳሪ ወገኖቹ ዘንድ ፍላጎቱ ካለ እና እነዚህን ተግዳሮቶች ካሸነፉ፥ ሌሎቹንም መሰናክሎች ማሸነፍ እንደሚችሉ አብራርተዋል።
“ስለ ሰላም ለመናገር በጣም ገና ሊሆን ይችላል” ያሉት ፓትሪያርኩ፥ ሁከትና ብጥብጡን ለማስቆምና ወደፊት ባለው የጋራ ግብ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበው፥ አክለውም “አሁንም ድረስ ብዙ መሰናክሎች እንደሚኖሩ፥ ነገር ግን የእኛ ግዴታ ወታደራዊ ግጭቶች እንዲያበቁ መስራት እና ለጋዛ ብቻ ሳይሆን ለመላው የፍልስጤም ህዝብ ሃሳቡን በግልጽ ማብራራት ተገቢ እንደሆነ በአፅንዖት ገልጸዋል።
የአካባቢውን ማህበረሰቦች መደገፍ
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በድርድሩ ውጤት የተሰማቸውን ደስታ በድጋሚ ገልፀው፥ መንበረ ፓትሪያርኩ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ጋር በመሄድ ተጨባጭ የሆነ እገዛ የማድረግ ተልዕኮውን እንደሚቀጥል ጠቁመው፥ ወደፊት የምናደርገው ነገር አሁን እየሰራን ከምንገኘው ሥራ በላይ ሳይሆን፥ ማህበረሰባችንን መደገፍ እና መርዳት እንዲሁም ለጋዛ ህዝብ፣ ለፍልስጤማውያን እና ለእስራኤላውያንም ጭምር የበለጠ መረጋጋት ሊያመጣ የሚችለውን ሁሉንም ነገር ማመቻቸት እንደሆነ ገልጸዋል።
በግጭቱ የወደሙትን መሰረተ ልማቶች ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊና ማህበራዊ ትስስርን መልሶ መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም ጭምር ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው፥ “አወቃቀሮችን ብቻ ሳይሆን ይህ ጦርነት የፈጠረውን የሰው ውድመት መልሶ ለመገንባት መርዳት አለብን” ብለዋል።
ለጸሎት የተደረገ ጥሪ
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በመጨረሻም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥቅምት 1 ላይ እንዲደረግ በታወጀው የሰላም የጸሎት ቀን ላይ ሁሉም ሰው እንዲሳተፍ መንበረ ፓትሪያሪኩ ያለውን ጥሪ በድጋሚ በማቅረብ አጠቃለዋል።