ካሪታስ ኢየሩሳሌም ጋዛ ለሚገኙ እናቶች እና ህፃናት እርዳታ እያደረሰ እንደሆነ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ካሪታስ እየሩሳሌም በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በነበሩት ቀናት 10,000 የታሸጉ የጨቅላ ህጻናት ወተቶችን ወደ ጋዛ አድርሷል።
ይህ ተነሳሽነት የተኩስ አቁም ከታወጀ በኋላ ከተደረጉት መጠነ ሰፊ የሰብአዊ እርምጃዎች መካከል አንዱ ሲሆን፥ ይህም ለሁለት ዓመታት ግጭት ለተጎዱ ተጋላጭ ቤተሰቦች አፋጣኝ እፎይታ ይሰጣል ተብሏል።
የእርዳታ አቅርቦት
በካሪታስ ኢየሩሳሌም የህክምና ክፍል በኩል ለመላው የጋዛ ሰርጥ የተደረገው የድጋፍ ስርጭቱ ቅድሚያ የሰጠው በጦርነቱ ወቅት መሠረታዊ የአመጋገብ ሥርዓታቸው ለተስተጓጎለባቸው ጨቅላ ሕፃናት እና ትንንሽ ልጆች እንደሆነ ተነግሯል።
ይህንን ተመጣጣኝ የህፃናት ምግብ አቅርቦቱን ያደረሱት በተለያዩ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ የካሪታስ የህክምና ቡድኖች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ዋና ግቡም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ህጻናትን እና ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚታገሉ እናቶችን ለመድረስ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
የካሪታስ ኢየሩሳሌም ዋና ጸሃፊ አንቶን አስፋር የድርጅቱ ተልዕኮ የሰው ልጅን ክብር ለማስጠበቅ እና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመጠበቅ እንደሆነ በአጽንዖት ጠቅሰው፥ ጦርነቱ ከተከሰተ የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቡድኖቻቸው የጋዛን ህዝብ በተለይም በጣም ደካማ የሆኑትን ህፃናትን፣ እናቶችን እና አረጋውያንን ለመደገፍ ያለመታከት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፥ ለጨቅላ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ ስለ ምግብ ብቻ ሳይሆን፥ ህይወትን እና ተስፋን መመለስ ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል።
የተስፋ ጭላንጭል
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት በርካታ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ንጹህ ውሃ፣ ሕክምናና የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ ሳይችሉ ለወራት የቆዩ ሲሆን፥ በእነዚህ ግዙፍ ተግዳሮቶች መካከል ካሪታስ ኢየሩሳሌም በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለመድረስ በትጋት ሲሰራ እንደነበር እና ይህም አስፈላጊ ምግቦችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፥ ለማገገም አዝጋሚውን ጉዞ ለጀመሩ ማህበረሰቦች የታደሰ የተስፋ ስሜት እንደሚሰጡ ተገልጿል።
ካሪታስ ኢየሩሳሌም በደቡባዊ ጋዛ ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ቤተሰቦች የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ የስነ-ልቦና ማህበራዊ ድጋፍ እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ እየሰጠ እንደሚገኝ የገለጹት ሃላፊው፥ ሰብአዊ እርዳታ በአስተማማኝ እና ተደራሽ በሆኑ ኮሪደሮች በኩል መድረሱን ለማረጋገጥ ከአካባቢው የጤና ባለስልጣናት እና ከቤተክርስትያን አጋሮች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።