አባ ፌራሪ 'ቤተክርስቲያን ድሆችን ትወዳለች፥ ይህ ደግሞ ትልቅ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አለው' ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከጥቅምት 11 እስከ 16 ባለው ጊዜ ውስጥ የዓለም ታዋቂ ንቅናቄዎች ስብሰባ (Encuentro Mundial de Movimientos Populares, EMMP) አባላት ለአምስተኛው ዙር ስብሰባ ሮም ውስጥ እንደሚሰበሰቡ የተነገረ ሲሆን፥ የስብሰባቸው ተሳታፊዎች የሚያደርጉትን የኢዩቤልዩ ዓመት ንግደትን ተከትሎ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጥቅምት 13 በሚያደርጉት ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ መርሃግብር ላይ እንደሚሳተፉም ጭምር ተገልጿል።
የዓለም ታዋቂ እንቅስቃሴዎች ስብሰባ አስተባባሪ የሆኑት አባ ማቲያ ፌራሪ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ህዝባዊ ንቅናቄዎቹ ብዙ እውነታዎቻቸው የሚወክሉትን እንቅስቃሴዎች በተጨባጭ ለማደራጀት ወደ አዲስ ምዕራፍ የገቡት የወቅቱን አስፈላጊነት አስመልክተው እንደነበር ገልጸው፥ ከዚህም ባለፈ ቤተክርስቲያኒቷና ህዝባዊ እንቅስቃሴዎቹ እንዴት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚራመዱ፥ እንዲሁም ሥራዎቻቸው ድሆችን ማፍቀር ላይ የሚያተኩረው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ ከሆነው ‘ዳይሌክሲ ቴ’ ጋር ያለውን መስተጋብር ያሳያል ብለዋል።
አባ ፌራሪ አምስተኛው የዓለም ታዋቂ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ስብሰባን አስመልክቶ ጥቅምት 5 በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ‘ይህ ክስተት ብቻ ሳይሆን አንድ እርምጃ ወደ ፊት የተራመደ ሂደት’ መሆኑን የገለጹበትን ሁኔታ ሲያብራሩ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያስተማሩን ሂደቶችን መፍጠር እንጂ ለክስተቶች ያን ያህል ትኩረት መስጠት እንደሌለብን ነው” ያሉ ሲሆን፥ ይህ ሂደት የጀመረው ቤተክርስቲያን ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ማጀብ በጀመረችባቸው በበርካታ ከተሞች እና የዓለም ሀገራት እንደሆነ ጠቅሰው፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ካርዲናል በነበሩበት ወቅት በአርጀንቲና፣ ቦነስ አይረስ “ካርቶኔሮስ” ወይም [የወረቀት ቆሻሻ ሰብሳቢዎች] እንዲሁም “ትራባ-ጃዶረስ ኤክስ-ክሉዶስ” ወይም [የተገለሉ ሠራተኞች] በተሰኙ ፕሮጄክቶች በርካታ ሥራዎችን መስራታቸውን አብራርተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሲመረጡ ብዙዎቹ መንፈስ ቅዱስ በዚህ መንገድ ሌላ አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ ትክክለኛው ጊዜ አሁን መሆኑን እየተናገረ መሆኑን ተሰምቷቸው እንደነበር አስታውሰው፥ በዚህም ሂደት ቤተክርስቲያን ከህዝባዊ ንቅናቄዎች ጋር አብሮ ለመራመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ መንቀሳቀስ እንደነበረባት እና ባለፉት 10 ዓመታት የተደረገው ይህንኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
የዓለም ታዋቂ እንቅስቃሴዎች ስብሰባ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለራሳቸው እውቅና እንዲሰጡ ለመርዳት በጣም አስፈላጊ እንደነበር የገለጹት አባ ፌራሪ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በውቅቱ ለእነዚያ ስብሰባዎች ያደረጉት ንግግሮች ጠቃሚ መሆናቸው፥ ምክንያቱም በንግግሮቻቸው ውስጥ የህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የተሳትፎአቸውን እና ከቤተክርስቲያን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ውስጥ ጥልቅ ትርጉም ይገኛል ብለዋል።
አስተባባሪው ታዋቂ እንቅስቃሴዎች ለብዙ ሰዎች ተስፋን እንደሚሰጡ በማስታወስ፥ በአሁኑ ወቅት ሌላ ምዕራፍ ተጀምሮ ተስፋን ማደራጀት እንደሚገባ የጠቀሱ ሲሆን፥ ሆኖም ግን እንቅስቃሴዎቹ በሚገባ መደራጀት እንዳለባቸው እና ይህንን ተግባር ለመወጣት በእግዚአብሔር ቸርነት ለመሞከር ከመላው ዓለም የተውጣጡ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በድጋሚ እንደሚሰበሰቡ ገልጸዋል።
ህዝባዊ ንቅናቄዎች ከቤተክርስቲያን ጋር ጥምረት መፍጠር እንዳለባቸው ያነሱት አባ ፌራሪ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የጠየቁን ይህንኑ እንደ ነበር አስታውሰው፥ ምክንያቱም ግንኙነቱ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በቤተክርስቲያን እና በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች መካከል እንደሆነ ገልጸው፥ ለብፁዕነታቸው ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች በየዕለቱ ችግር በሚያጋጥማቸው ወቅት፣ በመንገድ ላይ ሲሆኑ፣ በባህር ላይ ሲሆኑ እና አስቸጋሪ ታሪኮች ሲያጋጥሟቸው ከቤተክርስቲያን ጋር መጓዙ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል።
“ቤተክርስቲያን እንደ እናት ሆና በኢየሱስ ስም ታጅባቸዋለች ያሉት” አባ ፌራሪ፥ በአሁኑ ወቅት የህዝባዊ እንቅስቃሴዎቹ ልኡካን በአካባቢያቸው ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ዕለት ተእለት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለማብራራት ስለሚረዳቸው ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ለመገናኘት እንደገና መምጣታቸው አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥ “ይህ በጣም አስደናቂ ይመስለኛል ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈልገው ይህቺን ቤተክርስቲያን ነው” በማለት ገልጸዋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ከሚያደርጉት ስብሰባ ምን እንደሚጠብቁ የተጠየቁት አስተባባሪው፥ መጀመሪያ ብፁዕነታቸውን እና አጠቃላይ ቤተክርስቲያኒቷ በእጅጉ እንደሚያመሰግኑ ገልጸው፥ እግዚአብሔር በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ እና በቤተክርስቲያኑ በኩል ድሆችን እና ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን መንከባከብ እንደሚፈልግ እርግጠኞች ነን ብለዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ የሆነው ‘ዳይሌክሲ ቴ’ ይህን በሚገባ እንዳስተማራቸው አስታውሰው፥ መላው ቤተክርስቲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈልገውን ነገር ተግባራዊ ማድረጉን ስለምትቀጥል የተለየ የምንጠብቀው ነገር የለንም ብለዋል።
ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር በየቀኑ ከእነሱ ጋር የምትጓዝ ቤተክርስቲያን መሆን ማለት፣ ሰዎች እየተሰቃዩ በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ፣ ፍትህ በሌለበት ቦታ ሁሉ፣ ግጭት ባለበት ቦታ ሁሉ እና ድጋፍ የሚሹ ሰዎች ባሉበት ሁሉ የምትገኝ ቤተክርስቲያን ማለት ነው ካሉ በኋላ፥ ታዋቂ እንቅስቃሴዎች ማለት እራሳቸውን የሚያደራጁ ድሆች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ‘አብረን ስንራመድ በእውነት በዓለም ላይ ተስፋን መፍጠር የምንችለው ለዚህ ነው’ ብለዋል።
ታዋቂ እንቅስቃሴዎች በድሆች እና ለድሆች ቅርብ በሆኑ ሰዎች የተዋቀሩ እንደሆኑ የጠቀሱት አባ ፌራሪ፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ‘ዳይሌክሲ ቴ’ በጣም ድንቅ እንደሆነ እና በጣም ጠቃሚ የሆኑ ብዙ መልዕክቶች እንዳሉት አስታውሰው፥ ነገር ግን በተለየ ሁኔታ የሚያደንቁት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በማሳሰቢያው ምዕራፍ ውስጥ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ስለ ቤተክርስትያን ታሪክ እና ለድሆች ስላላት ፍቅር ታሪክ ማካተታቸው እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም የሚያስተላልፈው መልዕክት ቤተክርስቲያን ከህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ጋር አብራ መጓዟ እንግዳ ነገር ሳይሆን የቤተክርስቲያን ታሪክ አካል እንደሆነ ስለሚያሳይ ይህ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ብለዋል።
‘ዳይሌክሲ ቴ’ ቤተክርስቲያን ለድሆች የምታደርገውን አገልግሎት ብቻ የሚናገር ሳይሆን፥ ቤተክርስቲያን ድሆችን እንደምትወድ እና ይህም የተለየ እንደሆነ፥ ምክንያቱም ሰውን የምታገለግል ከሆነ በፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለምህ ምክንያት ወይም ጥሩ ሰው ስለሆንክ እና መርዳት ስለምትፈልግ ብቻ ሊሆን ይችላል፥ ይህም የተለመደ ነው፥ ነገር ግን ይህ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገው ነገር አይደለም ብለዋል።
አባ ፌራሪ በመጨረሻም ቤተክርስቲያን ድሆችን እንደምትወድ እና ይህም ፍቅር ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፥ ‘ይህንን ፍቅር በመመልከት ብቻ የክርስቶስን ምስጢር፣ የቤተክርስቲያንን ምስጢር እና ለምን ከሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ጋር እንደምትሰራ መረዳት ይቻላል’ በማለት አጠቃለዋል።