በማይናማር የኢየሱሳውያን ማህበር አለቃ የሆኑት አባ ጊሪሽ ጥቅምት 8 በሮም በተካሄደው የሶስተኛው የበላይ አለቆች ስብሰባ ወቅት መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ ቅዳሴ በማይናማር የኢየሱሳውያን ማህበር አለቃ የሆኑት አባ ጊሪሽ ጥቅምት 8 በሮም በተካሄደው የሶስተኛው የበላይ አለቆች ስብሰባ ወቅት መስዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ ቅዳሴ 

አንድ የኢየሱሳውያን ካህን በጦርነት በምትታመሰው ማይናማር ሃይል ሳይሆን ታማኝ የሆነ አቀራረብ እንዲኖር ጥሪ አቀረቡ

በማይናማር የኢየሱሳውያን ማህበር አለቃ የሆኑት አባ ጊሪሽ ሳንቲያጎ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሃገር የሆነችው ማይናማር በእርስ በርስ ግጭት እየታመሰች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት በአከባቢው የሚገኙ ሚስዮናውያን በስቃይ ውስጥ ከሚገኘው የሃገሪቱ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የኢየሱሳውያን ማህበር ሃላፊው አባ ጊሪሽ ሳንቲያጎ የዓለም የተልዕኮ እሑድ ዋዜማ ላይ በሮም የተካሄደውን መስዋዕተ ቅዳሴ በመሩበት ወቅት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን እንደተናገሩት ሚስዮናውያን በስቃይ ውስጥ ከሚገኙት የማይናማር ህዝቦች ጋር እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በእስያ ካሉት በግጭት በጣም ከተጎዱ ሃገራት ውስጥ አንዷ በሆነችው ማይናማር ውስጥ ለዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት በሃገሪቱ የኢየሱሳዊያን ማህበር አለቃ የሆኑት አባ ጊሪሽ በጦርነት፣ በመፈናቀል እና በተስፋ መቁረጥ መካከል መኖር እና ማገልገል ምን ማለት እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ካህኑ ከሌሎች ኢየሱሳዊያን ካህናት ፊት ሆነው እንደተናገሩት፥ የዛሬው የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የሚለካው በስኬት ወይም በቁጥር ሳይሆን በሚሰቃዩ ሰዎች መካከል በታማኝነት በመገኘት ነው ብለዋል።

ካህኑ ይሄንን የተናገሩት ማይናማር የእርስ በርስ ግጭት፣ የጅምላ መፈናቀል እና የሀገሪቱን እምነት እና የህዝቦቿን ፅናት የፈተኑ ሰብዓዊ ቀውሶች እየተጋፈጠች ባለችበት ወቅት ሲሆን፥ በአንድ ወቅት “ወርቃማው ምድር” በመባል ትታወቅ የነበረችው ማይናማር፥ በበለጸጉ ሀብቶቿ፣ በወርቃማ ቤተ መቅደሶቿ እና በርህራሄ እና ስምምነት ላይ በተመሰረተ ጥልቅ የቡድሂስት መንፈሳዊነቷ ትታወቅ እንደነበር አስታውሰዋል።

“ይህ ሁሉ የሆነው ከሰባት አስርት ዓመታት በፊት ነው” ያሉት አባ ጊሪሽ ብሔርተኝነት ህዝቡን እንደጎዳ እና በዚህም የውጭ ዜጎች ከሃገሪቷ እንደሸሹ ገልጸው፥ ከእነዚህም መካከል ወደ ሕንድ የሸሹት የገዛ ወላጆቻቸው፣ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው እንደሚገኙበት እና እርሳቸውም ‘በስደተኝነት’ እንደተወለዱ አብራርተዋል።

ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ፣ “ወርቃማ ዘመኔ” ብለው በገለጹት ጊዜ ወደ ወላጆቻቸው የትውልድ ሃገር ወደ ማይናማር ለተልዕኮ እንደተላኩ የገለጹት አባ ጊሪሽ፥ በያንጎን አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ከዚህን በፊት የማያውቋቸው ዘመዶቻቸው እንደተቀበሏቸው ገልጸው፥ ከዘመዶቻቸው ጋር ተቃቅፈው እንደተላቀሱ እና ዳግመኛ የመቀላቀል ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም ግን ተመልሰው የመጡባት ማይናማር ትርምስ ውስጥ ያለች ሃገር እንደነበረች ገልጸው፥ በየሜዳው በአሞራ የተከበበ ሬሳ ወድቆ እንደሚታይ እና የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት ብዝበዛን እንዴት እንደሳበ ለመግለጽ ቅዱሳት መፃሕፍትን በመጥቀስ ተናግረዋል።

የበለጸጉ የተፈጥሮ ሀብቶች ባሉበት ቦታ ሁሉ ወታደራዊ እና ትላልቅ ጎረቤት ሃገራትን ዓይን እንደሚስብ የገለጹት አባ ግሪሽ፥ በውጤቱም በኮቪድ-19፣ በመፈንቅለ መንግስት፣ በኢኮኖሚ ውድቀት፣ በግዳጅ የምልመላ ህግ፣ በጎርፍ እና በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዳው ህዝቡ እንደሆነ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሃገር ውስጥ እና ወደ ሌሎች ሃገራት ስደተኛ መሆናቸውን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፥ በዚህም ቤተሰቦች ተለያይተዋል፣ ማህበረሰቦች ተከፋፍለዋል፣ ብሎም በርካታ ካህናት እና ገዳማዊያት ድሆችን ለማገልገል ሕይወታቸውን ለአደጋ እንደሚያጋልጡ ይገለፃል።

አባ ጊሪሽ በዚህ የመከራ ወቅት ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “ጌታ በአጠገቤ ቆመ ብርታትን ሰጠኝ” ብሎ የተናገረውን አጽናኝ ቃል ማስታወስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“እነዚህ ቃላት የተፃፉት የእኛ ዓይነት መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች ነው” ያሉት ካህኑ፥ “በካቺን ግዛት ውስጥ ተደብቆ የሚገኝ የኢሱሳውያን ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ወደ ድንበር አከባቢ ከተዛወረው ትምህርት ቤት እና በርካታ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከተጠለሉበት ካምፖች ውስጥ ያሉ ሰዎች እነዚህ ቃላት ለእነሱ የተፃፉ እንደሆነ ማሰብ አለባቸው ብለዋል።

በማይናማር ያለው የኢየሱሳውያን ተሞክሮ የቅዱስ ጳውሎስን እምነት እንደሚያንጸባርቅ ገልጸው፥ ይህ እምነት “እርግጠኛ አለመሆን እና መበታተን ቢኖርም ለቤተክርስቲያን እና ለኢየሱሳዊያን ማኅበር ታማኝ መሆንን ያሳያል ብለዋል።

“የእኛ ማህበረሰቦች ተልዕኮ ምን ማለት እንደሆነ ዳግመኛ ተገንዝበዋል” ያሉት ካህኑ፥ ተልዕኮ ትንሽ፣ ቀላል እና ድሀ መሆን እንደሆነ አስረድተው፥ በዛ ድህነት ውስጥ ዋናው ነገር መዋቅር ሳይሆን መገኘት፣ ቅልጥፍና ሳይሆን ታማኝነት፣ ቁጥር ሳይሆን ምስክርነት እንደሆነ ገልጸዋል።

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ ያለውን “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ” የሚለውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቃል የጠቀሱት አባ ጊሪሽ፥ በማይናማር ያሉ ኢየሱሳውያን የተጠሩት ለመከላከል ወይም ለመሸሽ ሳይሆን “የደህንነት ችግር ባለበት ጊዜም እንኳን ቢሆን ሄዶ ለማገልገል እንደሆነ አመላክተዋል።

“የተላክነው አቅም እንደሌለው ጠቦት በግ፣ ነገር ግን ነፃ ፥ እንደ ድሆች ነገር ግን ሰላምን እንደሚሰጡ ሰዎች ነው” ያሉት ካህኑ፥ ጉልበት ባጣን ጊዜ የእግዚአብሔር መገኘት ጉልበታችን ይሆናል፥ “ድምፅ ባጣን ጊዜ፣ መንፈሱ በምስክርነታችን በኩል ይናገራል” ብለዋል።

ካህኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን በመጥቀስ ተልዕኮ ማለት መገኘት እና ማዳመጥ ማለት እንደሆነ፥ ሰዎች በሚሰቃዩበት ቦታ መቆም፣ ድምፃቸው ወደማይሰማ ሰዎች ዘንድ መሄድ እና ሕዝቡን የማይጥል አምላክ እንዲገለጥ ማድረግ” እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

በማይናማር “ሰላም” የሚለው ቃል ጥልቅ ትርጉም እንዳለው ያስታወሱት አባ ጊሪሽ፥ “ዛሬ ‘ሰላም’ ማለት የተፈናቀሉትን እና የተራቡትን ማገዝ፣ ምንም እንኳን ዋጋ ቢያስከፍልም እውነትን መናገር እንዲሁም ለጥላቻ ወይም ለበቀል ቦታ አለመስጠት እንደሆነ ገልጸው፥ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ እንደላካቸው፥ እኛም ብቻችንን ሳንሆን በተልዕኮ ውስጥ ካሉ ካህናት፣ ገዳማዊያት፣ ወንድሞች፣ ምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ካላቸው ወንዶችና ሴቶች ጋር ተባብረን መስራት ይገባናል በማለት አሳስበዋል።

በአመፅ እና በጥፋት ውስጥም ቢሆን “ጌታ ከክፉ ሥራ ሁሉ ያድነናል” በማለት ከቅዱስ ጳውሎስ እምነት ተስፋን የሰነቁት ካህኑ፥ የእግዚአብሔር ታማኝነት በፍጹም እንደማይቀየር እና ከብዙ ነገር እንደሚሰውር ገልጸው፥ “የተጠራነው ማይናማርን እንድናድን ሳይሆን ከማይናማር ጎን እንድንቆም፥ ተስፋ በማያስቆርጠው እምነት የሚያድነውን አምላክ ለመግለጥ ነው” ብለዋል።

አባ ጊሪሽ በመጨረሻም የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እነሱ መቅረቡን አስታውሰው፥ የኢየሱሳውያን የሆነውን ደስታቸውን ዳግመኛ ማግኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደው የዓለም የተልዕኮ እሁድ ክብረ በዓል ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በተለይ ከግንቦት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ግጭት ውስጥ ላለችው ማይናማር እና ለዓለም ሰላም ልባዊ ጸሎት ያቀረቡ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ከሆነችው ሀገር የሚወጡ ሪፖርቶችን “አስጨናቂ” ብለው በመጥራት፥ ማይናማር ላይ በሲቪሎች እና በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ በተፈፀመው የታጣቂዎች ጥቃት እና የአየር ድብደባ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸው፥ በማይናማር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ተማጽነዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአመፅና በችግር ለሚሰቃዩት ሁሉ ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ “አፋጣኝ እና ውጤታማ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ልባዊ ጥሪዬን አቀርባለው” ያሉ ሲሆን፥ በማከልም የጦርነት መሳሪያዎች ሁሉን አቀፍ እና ገንቢ በሆነ ውይይት ለሰላማዊ አካላት ተላልፈው እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

23 Oct 2025, 14:31