የተኩስ አቁም ስምምነቱ እየተጠበቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ተስፋ እና ጸሎት እንዲደረግ አሳሰቡ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በጋዛ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን አስከፊ ጦርነት ለማስቆም የድርድር ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንዳለ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ባለበት በአሁኑ ወቅት፥ የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትሪያርክ ምዕመናን ተስፋን እንዲያሳድጉ፣ በፀሎት እንዲጸኑ፣ እንዲሁም የአመጽ እና የመከፋፈል አመክንዮን እንዲቃወሙ የሚያሳስብ ሃዋሪያዊ ደብዳቤያቸውን ይፋ አድርገዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ለሀገረ ስብከቱ ባስተላለፉት መልዕክት በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠረውን ከፍተኛ ስቃይ አስታውሰው ጦርነቱ እንዲቆም፣ የታገቱት እንዲለቀቁ እና ፍልስጤማዊያን እስረኞች እንዲፈቱ እየተደረገ ያለው ጥረት የመሻሻል ምልክቶችን እያሳዩ መሆኑን በደስታ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።
እስራኤላዊያን ታጋቾችን መልቀቅ፣ የተወሰኑ ፍልስጤማዊያን እስረኞች መፍታት ብሎም የቦምብ ጥቃት እና ወታደራዊ ጥቃቶችን ማቆምን የሚያካትተው የስምምነቱ ሂደት ለመጀመሪያ ጊዜ አዎንታዊ እድገት እያሳየ መሆኑን የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ መሆኑን የጠቀሱት ፓትሪያርኩ፥ ‘ይህ አስፈላጊ እና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ የመጀመሪያ እርምጃ ነው’ በማለት ጽፈዋል።
ሆኖም ግን እስካሁን ምንም ግልጽ ወይም ይፋ የሆነ ነገር የለም ያሉት ብፁዕነታቸው፤ አሁንም ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች እና ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ስላሉ፥ ሁሉም ነገር በትክክል መገለጽ እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ የስምምነት ሂደቶቹ ከእውነታው የራቁ ተስፋዎች ብቻ እንዳይሆኑ አሳስበዋል።
ለሁሉም ሰው አዲስ ጅማሮ ነው
ፓትርያርኩ ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊገለጽ የማይችል መከራን ተቋቁመው ለሚገኙት ፍልስጤማዊያን እፎይታ እንደሚያመጣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ‘በዘላቂነት ይቆማል ብለን ተስፋ የምናደርገው ይህ ጦርነት ለጋዛ ነዋሪዎች እፎይታን ስለሚሰጥ ከምንም በላይ ደስ ይለናል’ ካሉ በኋላ፥ ምክንያቱን ሲገልጹ ‘ይህ ለስምምነት የተቃረበ የሚመስለው አስከፊ ጦርነት መቆም በመጨረሻም ለእስራኤላውያን እና ፍልስጤማውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለምም ጭምር አዲስ ጅማሮ ይሆናል’ ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ አክለውም ሊመጣ የሚችለውን “የክህደት መንገድ” በመጥቀስ፥ የወታደራዊ ዘመቻው ማብቃት ወደ ዘላቂ ሰላም ለመምጣት “የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ” ብቻ መሆኑን ለምዕመናን አስታውሰዋል።
በዌስት ባንክ ውስጥ ያለው የማያቋርጥ ስቃይ
ፓትርያርኩ ከዚህም በተጨማሪ በዌስት ባንክ ውስጥ እያሽቆለቆለ ያለውን የደህንነት ሁኔታ አንስተው፥ የአከባቢው ማህበረሰብ በአሁኑ ወቅት በየቀኑ ለበርካታ ችግሮች እየተጋረጠ እንደሚገኝ፥ በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰፋሪዎች እየተከበቡ በሚገኙት በትናንሽ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ፍልስጤማዊያኑ ከደህንነት ባለስልጣናት በቂ ጥበቃ ስለማያገኙ የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል።
በተወሳሰበ እና ተለዋዋጭ በሆኑ ግጭቶች መሃል ሕይወታቸውን የሚመሩት እና በአከባቢው በሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰብ ላይ በየቀኑ የሚደርሰውን ስቃይ እና አለመረጋጋት በአጽንዖት የገለጹት ፓትሪያርኩ፥ ማህበረሰቡ ከደህንነት፣ ከጉዞ እና ከአገልግሎቶች ተደራሽነት ጋር በተያያዘ የሚደረጉ መደበኛ ውሳኔዎች እንኳን ተጽእኖ እንደሚያደርስባቸው ጠቁመዋል።
“የተስፋ ቃል” እንዲሰጥ የተደረገ ጥሪ
“እኛ የመጣነው የፖለቲካ መግለጫ ለመስጠት ወይም ስለ ሁነቶች ስትራቴጂካዊ ትንታኔ ለመስጠት አይደለም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፥ የቤተክርስቲያን ተልእኮ ከፖለቲካዊ አስተያየት ይልቅ መንፈሳዊ መመሪያን መስጠት እንደሆነ ጠቅሰው፥ ዓለም አስቀድሞ እንደዚህ ባሉ ቃላት የተሞላች እንደሆነ እና ይህም እውነታውን እምብዛም እንደማይለውጥ፥ ይልቁንም፣ በወንጌል ጸንተን እንድንኖር የሚረዳን መንፈሳዊ ራዕይ እንፈልጋለን ብለዋል።
ፓትርያርኩ በምድሪቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በቅድስት አገርም ሆነ በዓለም ዙሪያ ባሉ የበርካታ ሰዎች ነፍስ ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ሥቃይ ተጽእኖ በማስታወስ፣ መከራው እየተለመደ መምጣቱን አስጠንቅቀው፥ “የሚጠፋው እያንዳንዱ ሕይወት፣ የሚደርሰው እያንዳንዱ ጉዳት እና ረሃብ በእግዚአብሔር ፊት አሳፋሪ ድርጊት ሆኖ ይቀራል” ሲሉ አረጋግጠዋል።
ዓይኖቻችንን በኢየሱስ ላይ እናተኩር
በዓመፅ እና በተስፋ መቁረጥ ፈተና ውስጥ ምእመናን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያሳሰቡት ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፥ ብቻችንን ይህንን ምስጢር ልንረዳው እንደማንችል ጠቁመው፥ በራሳችን ሃይል በዚህ የክፋት ሚስጢር ፊት መቆም እና እሱን መቃወም እንደማይቻል የገለጹ ሲሆን፥ ይህም በመሆኑ ምክንያት ዓይኖቻችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብቻ እንድናተኩር ይገባል በማለት የዕብራውያን መልዕክት ምዕራፍ 12፡2 ን በመጥቀስ ጽፈዋል።
ፓትርያርኩ በማከልም ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የሚወዷቸውን ሰዎች፣ ብሎም ቤታቸውን እና መተዳደሪያ ንብረቶቻቸው ያጡ ሰዎችን መከራ በማስታወስ፥ የቤተክርስቲያን ምላሽ በፍቅር እና በይቅርታ እንጂ በበቀል መሆን እንደሌለበት ታምናለች ሲሉ በድጋሚ ገልጸዋል።
“መምህራችን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህይወቱን አሳልፎ በመስጠት ስጦታ እና ይቅርታ የሚሆን ፍቅር አሳየን” ያሉት ብፁዕነታቸው፥ ቁስሎቹ ለበቀል የሚያነሳሳን ሳይሆን በፍቅር የመከራን ሸክም የምናሸንፍበት ምልክት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጦርነት ማቆም ወደ ሰላም የሚደረግ የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው
ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ጦርነቱ አሁን ቢያበቃም የግጭቱ መንስኤ እስካሁን መፍትሄ አለማግኘቱን ገልጸው፥ መተማመንን መልሶ ለመገንባት እና ልብን ከጥላቻ ለማላቀቅ ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።
ጦርነት ማቆም የሰላም መጀመሪያን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን ሰላምን ለመገንባት የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ጠቁመው፥ ተስፋን ተጨባጭ ለማድረግ ወደፊት ያለውን ረጅም መንገድ ያመላክተናል ብለዋል።
ፓትርያርኩ የክርስቶስን ባዶ መቃብር በማስታወስ ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ስቃይ ለዘላለም እንደማይቆይ እና በረሃውን የሚያጠጣው እንባ የትንሳኤውን የአትክልት ስፍራ ዉብ እንደሚያደርግ ለምዕመናን አረጋግጠዋል።
የጾም እና የጸሎት ቀን
ፓትርያርኩ በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም. የጾም እና የጸሎት ቀን እንዲሆን ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ሁሉም ቁምስና እና የሃይማኖት ማህበረሰቦች በዚህ መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፉ በመጋበዝ አጠቃለዋል።