ኢየሱስና ዘኬዎስ ቀረጥ ሰብሳቢው ኢየሱስና ዘኬዎስ ቀረጥ ሰብሳቢው 

የሕዳር 07/2018 ዓ.ም የ31ኛው መደበኛ ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.      ጥበብ 11፡22-12፡2

2.     መዝሙር 144

3.     2ኛ ተሰሎንቄ 1፡11-22፡2

4.    ሉቃስ 19፡1-10

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ እና ቀራጩ ዘኬዎስ

ወደ ኢያሪኮም ገብቶ በዚያ በኩል አልፎ እየሄደ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው ነበረ፤ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፤ ሀብታምም ነበረ። ኢየሱስ ማን እንደሆነም ለማየት ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ አቃተው። በዚያችም መንገድ ማለፍ ነበረበትና ወደ ፊት ቀድሞ ሮጠና በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በቤትህ መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ፤” አለው። ፈጥኖም ወረደ፤ በደስታም ተቀበለው። ሁሉም አይተው “ከኀጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ፤” ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን “ጌታ ሆይ! ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድኾች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን መጥቶ አል፤ ምክንያቱም እርሱም የአብርሃም ልጅ ነውና፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና፤” አለው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ ጸሎት ላይ ከሉቃ. 19: 1-10 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በዘኬዎስ መካከል የተደረገውን ግንኙነት ይተርካል። ዘኬዎስ በኢያሪኮ ከተማ የሚኖር የቀራጮች አለቃና ሃብታም ሰው ነበር። በዚህ ታሪክ መካከል መፈለግ የሚል ቃል ተጠቅሶ እናገኛለን። ዘኬዎስ ኢየሱስ የቱ እንደሆነ ለማየት ይፍልግ ነበር፤ ነገር ግን ቁመቱ አጭር በመሆኑ ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሊያየው አልቻለም። (ሉቃ. 19:3) በተመሳሳይ ምዕራፍ ቁጥር 10 ላይ፥ “ኢየሱስም የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአል” ተብሎ የተጻፈውን እናገኛለን። በእነዚህ ሁለት ፍለጋዎች ላይ እናተኩር፤ የመጀመሪያው ዘኬዎስ ኢየሱስን ለማየት መፈለጉን እና ሁለተኛው ኢየሱስ ዘኬዎስን ለማየት መፈልጉ ነው። ዘኬዎስ ቀራጭ ነበር፣ ማለትም የሮማውያን ገዢዎችን ወክለው ቀረጥ ከሚሰበስቡት አይሁዳውያን መካከል አንዱ ነበር። ይህን ሥልጣን የተጠቀም እና የትውልድ አገሩን የከዳ ሰው ነበር። ስለዚህ ዘኬዎስ ሃብታም እና በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላና የወጣለት ኃጢአተኛ ሰው ነበረ። በሉቃ. 19:3 ላይ ዘኬዎስ በቁመት አጭር ሰው እንደ ነበር ይነግረናል። ይህ ምናልባት የልቡን ትንሽነት፣ የተበላሸ ስብዕናውንና፣ ታማኝነት የጎደለው ሕይወቱንና በአመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን ያመላክታል።

ነገር ግን ማወቅ ያለብን ዋናው ነገር ዘኬዎስ አጭር ሰው እንደ ነበር ነው። ሆኖም ኢየሱስን ማየት ይመኝ ይፈልግ ነበር። ኢየሱስን እንዲያይ የገፋፋው አንድ ነገር አለ። ኢየሱስ በዚያ በኩል ያልፍ ስለነበር ዘኬዎስ ኢየሱስን ለማየት ብሎ ከሕዝቡ ፊት ቀደመና በአንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ። (ሉቃ. ምዕ. 19:4) በሃብቱ ሁሉንም ተቆጣጥሮ የነበረ ዘኬዎስ፣ ራሱን መሳቂያ በማድረግ፣ ኢየሱስን ለማየት ብሎ የማይመጥነውን መንገድ ወሰደ፥ ሾላ ዛፍ ላይ መውጣት።  ለምሳሌ አንድ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አንድ ትዕይንት ለማየት ዛፍ ላይ ቢወጣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በጥቂቱ እናስብ። የሰው መሳቂያ ይሆናል። ዘኬዎስም ኢየሱስን ለማየት ብሎ ራሱን የሰው መሳለቂያ አደረገ። ዘኬዎስ ምንም እንኳን ዝቅተኛነት ቢያጠቃውም፣ ኢየሱስን የሚመስልበት ሌላ መንገድ መፈለግ እንዳለበት ይሰማው ነበር። ኢየሱስን ገና አላወቀውም፤ ነገር ግን ከብልሹ ሥነ ምግባር ነፃ የሚያወጣውን ሰው ያገኝ እንደሆን ይጠብቅ ነበር። ይህ ልብ ልንለው የሚገባን መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በሕይወት ውስጥ ሁሉም ነገር ያለቀለት አለመሆኑን ዘኬዎስ ያስተምረናል። ፈጽሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሊኖር አይገባም። መለወጥ እንችላለን።  ነገሮችን እንደገና መጀመር እንችላለን። ዘኬዎስ ያደረገው ይህን ነው።

በዚህ ረገድ ሁለተኛው ፍለጋ ወሳኝ ነው፤ ይህም የኢየሱስ መፈልግ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፉትን እንዲፈልግ ከአብ ዘንድ ተልኮአል። ወደ ኢያሪኮ በደረሰ ጊዜ ዘኬዎስ በነበረበት ዛፍ አጠገብ አለፈ። የወንጌሉ ቃልም እንዲህ በማለት ይተርካል። ኢየሱስም ወደስዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ ቀና ብሎ ተመለከተና ዘኬዎስን “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በአንተ ቤት መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ከዛፉ ውረድ” አለው። (ሉቃ. 19:5) ይህ በእውነቱ አስደናቂ ምስል ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ዘኬዎስን ያየው ከታች ሆኖ ነው፣ የድነት ታሪክ የሚጀምረው ከዚህ ነው። እግዚአብሔር እኛን አሳንሶን ወይም አዋርዶን አያውቅም።  በእኛ ላይ ሊፈርድ አልመጣም። ነገር ግን በተቃራኒው፣ እግራችንን እስከ ማጠብ ድረስ ዝቅ ብሎ ከታች ሆኖ እያየን ክብራችንን መለሰልን። በዚህ መንገድ፣ በዘኬዎስ እና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ያለው የዓይን ግንኙነት አጠቃላይ የመዳን ታሪክን የሚገልጽ ይመስላል። የሰው ልጅ ከመከራው ሁሉ ጋር የእግዚአብሔርን ቤዛነት ይፈልጋል። ነገር ግን በመጀመሪያ እግዚአብሔር በምሕረቱ ያድናቸው ዘንድ ፍጥረታቱን ይፈልጋል።

ወንድሞች፣ እህቶች ሆይ! ይህን እናስታውስ። እግዚአብሔር እኛን ለማግኘት የሚያደርገው ፍለጋ፣ በስህተቶች በተሞላ ሕይወታችን ምክንያት የሚያበቃ ሳይሆን ምን መሆን እንደምንችል በማወቅ ገደብ በሌለው እምነት ነው። አንዳንድ ጊዜ በስነ ምግባር ዝቅተኞች እንደሆንን የሚሰማን ከሆነ፣ በሚያጋጥሙን ፈተናዎች ምክንያት ቅዱስ ወንጌል ከሚጠይቀን በታች ሆነን ብንገኝ፣ በችግር እና በኃጢያት ውስጥ የተዘፈቅን ብንሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁል ጊዜ በፍቅር ይመለከተናል። ወደ ዘኬዎስም እንደመጣ ሁሉ ወደ እኛም ይመጣል። በስማችን ይጠራናል። ብንቀበለው ወደ ቤታችንም ይመጣል። ለመሆኑ ምን ደረጃ ላይ እንገኛለን? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል። ለምንም ብቁዎች አይደለንም በማለት እራሳችንን እናገልላለን ወይስ ጭንቅ ውስጥ ሆነን ኢየሱስን ጋር ለመገናኘት እንፈልጋለን? ከስህተታቸው ወይም ከውድቀታቸው እንደገና ለመነሳት የሚታገሉትን እንዴት እንመለከታቸዋለን? ራስን ከፍ በማድረግ እንፈርድባቸዋለ? እንንቃቸዋለን? ወይም እናገልላቸዋለን?  አንድን ሰው ከወደቀበት እንዲነሳ ለመርዳት ወደ ታች መመልከት ተገቢ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚያቅፍ፣ የጠፉትን በርህራሄ የሚፈልግ የኢየሱስ ክርስቶስ ዓይነት አመለካከል ሊኖረን ይገባል። ቤተ ክርስቲያንም ሁል ጊዜ የኢየሱስ ክርስቶስ ዓይነት አመለካከት ሊኖራት ይገባል እንጂ የተሳሳቱን ሰዎችን የማግለል ወይም የመፍረድ እይታ ሊኖራት አይደለም።

ትህትናዋን እግዚአብሔር የተመለከታት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አዲስ አመለካከት ለእኛ እና ለሌሎች እንዲኖረ በጸሎታችን እንጠይቃታለን።

ምንጭ፡ የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

 

15 Nov 2025, 09:08