የኤሲኤን ፕሬዝዳንት ሰላም እና የእምነት ነፃነት የተሳሰሩ መሆናቸውን ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከሃይማኖታዊ ስደት ጀርባ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸው
በችግር ላይ የሚገኙ አቢያተ ክርስቲያናትን የሚረዳው ‘ኤይድ ቱ ዘ ቸርች ኢን ኒድ’ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ረጂና ሊንች ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ አፅንዖት ሰጥተው ከተናገሩት ውስጥ የሀይማኖት ስደት ካለፉት ጊዜያት ይልቅ በአሁኑ ወቅት በግልጽ እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም አንዱ ምክንያት ህብረተሰባቸውን በሃይል ለመቆጣጠር የሚጥሩ አምባገነን መንግስታት ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱ እና ይሄንንም ተግባር ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ቀላል እንዳደረገው ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የበርካታ እምነት ተከታዮች ሰለባ የነበሩበት፣ መስከረም 1 ቀን 1994 ዓ.ም. ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ በዓለም ላይ ጂሃድዝም እየተስፋፋ መምጣቱን ሁሉም ሰው የተገነዘበ ይመስላል ብለዋል።
በስደት ላይ ያሉ ሰዎች አስገራሚ ምስክርነት
ወይዘሮ ሊንች የአካባቢ ሁኔታዎችን ለመገምገም እና የኤሲኤን ፕሮጀክቶችን ለመጎብኘት ወደ ተለያዩ ክልሎች በሚጓዙበት ወቅት ከአካባቢው ማህበረሰቦች የሚተላለፉ ጠንካራ መልዕክቶችን እንደሚሰሙ ገልጸው፥ ከዚህም በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ የሚያገኟቸው ካቶሊኮች እምነት በጣም ጠንካራ እንደሆነ በመጥቀስ፥ “እነዚህ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የመጨረሻውን ዋጋ ሊከፍሉ እንደሚችሉ እያወቁ፣ ነገር ግን በእምነታቸው ጸንተው ይኖራሉ” በማለት ገልጸዋል።
በተለይ ክርስቲያኖች አናሳ እና ደሃ በሆኑበት ፓኪስታን ያጋጠማቸውን ነገር ያስታወሱት ሃላፊዋ፥ በዚህ ስፍራ የሚገኙ ክርስቲያኖች ከእነሱ ይልቅ ክርስቶስ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደተሰቃየ እና የራሳቸውን ስቃይ ከእሱ ጋር ሲያነጻጽሩ ምንም ነገር እንዳልሆነ በልበ ሙሉነት እንደነገሯቸው አስታውሰዋል።
እንዳልተረሱ ለዓለም ማሳወቅ
እንደ ወይዘሮ ሊንች ከሆነ ከኤሲኤን አስቸኳይ ተግባራት መካከል አንዱ ስለ ሃይማኖታዊ ስደት ዓለም አቀፍ ግንዛቤን ማሳደግ እንደሆነ ገልጸው፥ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር በ 2013 ዓ.ም. መጋቢት ወር ላይ ወደ ኢራቅ መጓዛቸውን በማስታወስ፥ በወቅቱ ለአንዳንድ ካቶሊካዊያን ጓደኞቻቸው የት እንደምሄዱ ሲነግሯቸው ግራ ተጋብተው 'ለምን የሙስሊም ሃገር ወደ ሆነችው ኢራቅ እንደምጓዝ በአግራሞት እንደጠየቋቸው አስታውሰው፥ “እነዚህ ሰዎች ከመጀመሪያዎቹ የቤተክርስቲያን ዘመናት ጀምሮ በስፍራው የነበሩ ክርስቲያኖች እንደሆኑ አያውቁም ነበር” ብለዋል።
የጸሎት እና የአብሮነት ኃይል ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ አበክረው የተናገሩት ሊንች፥ በሰሜን ናይጄሪያ ወይም ሌሎች አሰቃቂ ጭካኔዎች በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በሄዱበት ወቅት ሰዎች ብቻቸውን እንዳልሆኑ መገንዘባቸው ምን ያህል ትርጉም እንዳለው መረዳታቸውን ጠቁመው፥ እሳቸው ወክለው የመጡት ዘወትር የሚጸልዩላቸው ሩቅ ሃገራት ያሉ ሰዎችን እንደሆነ እንደሚገነዘቡ እና በዚህም ለእነሱ የሚጸልይ አንድ የክርስቶስ አካል መኖሩ ጥልቅ የሆነ ጥንካሬ እና ተስፋን እንደሚሰጣቸው፣ ብሎም የመጽናኛ ምንጭ እንደሚሆናቸው አስረድተዋል።
በዓለም ዙሪያ 5,500 የእርዳታ ፕሮጀክቶች መኖራቸው
የኤሲኤን ሥራ የመንግስት ወይም የህዝብ ድጋፍ ሳይኖር ሙሉ በሙሉ በግል ልገሳ የተደገፈ ተጨባጭ የሆኑ ፕሮጀክቶችን እንደሚያካትት የገለጹት ሃላፊዋ፥ በዓለም ዙሪያ 5,500 ከሚሆኑት በመካሄድ ላይ ካሉት ፕሮጄክቶቻቸው መካከል ቤተክርስቲያኒቱ ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናትን ወይም ዘርዓ ክህነት ማዕከሎችን ለመገንባት ወይም ለእህቶች እና ካቴኪስቶች ምስረታ የሚረዱ ግብአት በሌለባቸው ድሃ ክልሎች ውስጥ በርካታ የሚስዮናውያን ጥረቶች እንደሚገኙበት ጠቁመው፥ ድርጅቱ እምነትን የሚያዳብሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ፣ ትምህርታዊ እና የሃዋሪያዊ ሥራ ፕሮግራሞችን እንደሚደግፍ የገለጹ ሲሆን፥ ክርስቲያኖች ከባድ ስደት በሚደርስባቸው ክልሎች ተቋማቸው የአደጋ ጊዜ እርዳታ እንደሚሰጥም ጭምር አስረድተዋል።
ለሶሪያ፣ ኢራቅ እና ዩክሬን እርዳታ
በችግር ላይ የሚገኙ አቢያተ ክርስቲያናትን የሚረዳው ይህ ዓለም አቀፍ ተቋም እ.አ.አ. ከ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአከባቢው የሚገኙ ክርስቲያኖች በድህነት የሚኖሩበት እና በተለይም በከባዱ የክረምት ወራት በሕይወት ለመትረፍ በሚታገሉበት ሶሪያ ውስጥ ያለማቋረጥ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ድርጅቱ የመኖሪያ ቤቶችን እንደሚገነባ፣ ትምህርት ቤቶችን በገንዘብ እንደሚደግፍ፣ ለጨቅላ ሕፃናት የዱቄት ወተት እንደሚያቀርብ እና ለህፃናት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ በኢራቅ የካልዳውያን ሃገረ ስብከት ውስጥ የሚገኘውን የኤርቢል ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲን በሕግ፣ በምህንድስና፣ በሥነ ሕንፃ እና በሌሎች ዘርፎች ለሚማሩ ወጣት ክርስቲያኖች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት እንደሚደግፍ የገለጹት ወይዘሮ ሊንች፥ አክለውም በዩክሬን በተለይም በጦርነት ቀጠና ላይ የሚያገለግሉ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ካህናትን እንደሚያግዙ፥ እንዲሁም ካህናት እና ገዳማዊያት ከምዕመኖቻቸው ጋር አብረው እንዲጓዙ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ጥያቄ
ኤሲኤን የሃይማኖት ነፃነትን የሚያረጋግጠው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 18ን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ዘመቻ መጀመሩን ያስታወሱት ሃላፊዋ፥ “ይህ ወሳኝ ጉዳይ” እንደሆነ ጠቅሰው፥ “የሃይማኖት ነፃነት ሰብአዊ መብት እንጂ ስጦታ” እንዳልሆነ የገለጹ ሲሆን፥ ሰዎች እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ይህ መብት ከአሁን በኋላ ከግምት ውስጥ እንደማይገባ ሲገነዘቡ ብቻ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህ በመሆኑም ምክንያት ለመጪው ትውልድ ሲባል በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻውን መቀላቀል አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
የኤሲኤን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሰላም እና የሃይማኖት ነፃነትን ያገናኙበትን ንግግር በማስታወስ “ሰዎች እነዚህን መብቶች ሲነፈጉ ኅብረተሰቡ ወደ አምባገነንነት እና ፈላጭ ቆራጭነት መሄድ ይጀምራል” በማለት አስጠንቅቀዋል።
የር.ሊ. ጳጳሳቱ ጠንካራ ድጋፍ
ወይዘሮ ሊንች የሀይማኖት ነፃነት ለማስፈን፣ ውይይትን ለማዳበር እና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የማያቋርጥ ጥሪዎች አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ ብፁዕነታቸው ደጋግመው ስለተናገሩ ያላቸውን ምስጋና ገልጸው፥ ምክንያቱም አማኞችም ሆኑ ክርስቲያን ያልሆኑትንም ጭምር በርካታ ሰዎች ወደ እርሳቸው ስለሚመለከቱት የእርሳቸው ጥሪ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በቫቲካን ውስጥ በርካታ የዓለም መሪዎች እንደሚጎበኟቸው በማስታወስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ጎላ አድርገው ያነሱ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ከኤሲኤን ተወካዮች ጋር ተገናኝተው በመወያየታቸው ያላቸውን ምስጋና በመግለጽ፥ ምንም እንኳን እርሳቸው የዓለምን ሸክሞች በትከሻቸው ላይ ቢሸከሙም ከእሳቸው የሚፈልቀው የመረጋጋት ስሜት አስደናቂ እንደሆነ አስታውሰው፥ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን በማግኘታችን በእውነት ተባርከናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ወሳኝ ሚና
ወይዘሮ ሊንች በመጨረሻም የመገናኛ ብዙሃን ስለነዚህ ጉዳዮች ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚና በማንሳት፥ አዎንታዊ ታሪኮችን ማካፈል አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ የሰዎችን ስቃይ መዘገብም አስፈላጊ መሆኑን አመላክተው፥ “ሰዎች የምንኖርበትን እውነታ በተረዱ ቁጥር እርምጃ የመውሰድ እድላቸው እየጨመረ ይሄዳል” በማለት አሳስበዋል።