በቱርክ ውስጥ የካቶሊክ ማህበረሰብ ቁጥር እያደገ መምጣቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ቱርክ 99 በመቶ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሃገር ስትሆን፥ አነስተኛ ቢሆንም የክርስትና እና የአይሁድ ሃይማኖቶችም በሀገሪቱ ይገኛሉ።
አባ አሌክሳንደር ጀርኔጅ በቱርክ ስላለው አሁናዊ ሁኔታ ከስፍራው ሆኖ እየዘገበ ከሚገኘው ከቫቲካን ዜና ባልደረባ ክሪስቶፈር ዌልስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢስታንቡል ስለሚገኘው በቁጥር አነስተኛ ስለሆነው የካቶሊክ ማህበረሰብ አንስተው ተወያይተዋል።
የኦስትሪያ እና የጀርመን ግዛት ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ቪንሰንት ማህበር ካህን የሆኑት አባ ጀርኔጅ በቱርክ ዋና ከተማ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የኦስትሪያ ማህበረሰብ የበላይ ጠባቂ ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን እዚያ ያሉት ካቶሊኮች የተለያየ አስተዳደግ እና ዜግነት ያላቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።
ካህኑ ከዚህም በተጨማሪ የቱርክ ካቶሊኮች ቁጥር እያደገ መምጣቱን በመግለጽ ‘የአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን እያደገች መሆኗን በማየታቸው ታላቅ ደስታ እንደሚሰማቸው’ ተናግረዋል።
እ.አ.አ. በ 1924 ዓ.ም. የወጣውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተከትሎ ቱርክ በምንም ዓይነት ሕጋዊ ሃይማኖት የማትገዛ እና ከሃይማኖት ነፃ ወይም ሴኩላር በሆነ መንግሥት እንደምትተዳደር የሚታወቅ ሲሆን፥ በሀገሪቱ ውስጥ አናሳ ቁጥር ያለው ክርስትና ወደ 100,000 አካባቢ እንደሚጠጋ የተነገረ ሲሆን እነዚህም በተለያዩ ቤተ እምነቶች በመከፋፈል የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ፣ የአርመን እና የአሦር-ካልዲያን ተብለው ተከፍለዋል።
አባ ጀርኔጅ ከሌሎች የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር የሚኖረውን ክርስቲያናዊ ግንኙነት “በጣም የተለመደ” መሆኑን ገልጸው፥ እርስ በርሳቸው እንደሚጠያየቁ እና ‘የአንድነት የጸሎት ሳምንት’ በሚል ኢስታንቡል ውስጥ ስምንት ሙሉ ቀናት እንደሚያከብሩ አስታውሰዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በስፍራው መገኘት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ የመጀመሪያው እና ታሪካዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ምሳሌ በሆነው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ብፁዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊን ጨምሮ ከሲቪል እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር እንደሚሰበሰቡ እና ክልላዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለመ የመተጋገዝ ምልክትን ያለበት እንደ ሆነ ገልጸው፥ ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝት በኒቂያ ጉባኤ 1700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ መገኘትን ጨምሮ አንካራን፣ ኢስታንቡልን እና ቤሩትን የሚጎበኙ መሆናቸውን የጠቆሙት አባ ጀርኔጅ፥ “በጣም ደስተኞች ነን፣ እናም ይህን ታላቅ አጋጣሚ በጉጉት እንጠባበቃለን” በማለት ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ኢስታንቡልን የጎበኙ የመጀመሪያው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አይደሉም። ከእሳቸው በፊት አራት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወደዚህ ስፍራ ሃዋሪያዊ ጉዞ ያደረጉ ሲሆን፥ ርዕሰ ለቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ እ.አ.አ. በ1967፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ 1979፣ ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ በ2006 እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ 2014 ዓ.ም. ወደስፍራው ሃዋሪያዊ ጉዞ አድርገው እንደነበር ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ በኋላ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ 23ኛ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አንጀሎ ሮንካሊ በኢስታንቡል ውስጥ እ.አ.አ. ከ 1935 እስከ 1944 ድረስ በቱርክ እና በግሪክ ሐዋርያዊ ልዑክ ሆነው አገልግለዋል።