የፈሪሳዊው እና የቀራጩ ምሳሌ የፈሪሳዊው እና የቀራጩ ምሳሌ 

የጥቅምት 30/3018 ዓ.ም 30ኛው መደበኛ ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.    ሲራክ 35፡12-14.16-19

2.    መዝሙር 33

3.    2 ጢሞ 4፡6-8. 16-18

4.    ሉቃስ 18፡9-14

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የፈሪሳዊው እና የቀራጩ ምሳሌ

ጻድቃን ነን በማለት በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እንዲህም አለ፦ “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፤ አንዱ ፈሪሳዊ ሌላውም ቀራጭ ነበር። ፈሪሳዊው ቆሞ እንዲህ ሲል በልቡ ጸለየ፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ! እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ፥ ቀማኛና ዐመፀኛ አመንዝራም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት እሰጣለሁ፤’ አለ። ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳን አልፈለገም፤ ነገር ግን ‘አምላክ ሆይ! እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ፤’ እያለ ደረቱን ይመታ ነበር። ከዚያኛው ይልቅ ይህ ሰው ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ እላችኋለሁ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይላልና፥ ራሱን ግን ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

 

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ሥርዓተ አምልኮ ላይ ከሉቃስ ወንጌል 18: 9-14 ተወስዶ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ የመጡ ሁለት ሰዎችን እነርሱም አንድ ፈሪሳዊ እና አንድ ቀራጭ ሰው ምሳሌ ያቀርብልናል። እነዚህ ሁለቱ ሰዎች ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ ይሂዱ እንጂ፣ ነገር ግን ቀራጩ ሰው ብቻ ከልብ ራሱን ወደ እግዚአብሔር አቅርቧል። ምክንያቱም ይህ ሰው ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የቀረበው በድኅነት፣ በትህትና እና ራሱን ሳይደብቅ በግልጽነት ነበር። ምሳሌው ሁለት ርዕሦችን የሚገልጽ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ራስን ቀና ማድረግ እና ሁለተኛው ራስን ዝቅ ማድረግ የሚሉ ናቸው።

በሉቃስ ወንጌል 18:10 ላይ እንደተገለጸው፥ “ሁለት ሰዎች ለመጸለይ ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ፤ አንዱ ፈሪሳዊ ሲሆን ሌላው ቀራጭ ነበር” ይለናል። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ አንድ ሰው ከአምላኩ ጋር መገናኘት ሲፈልግ እግዚአብሔር ወደሚገኝበት ከፍታ ወይም ተራራ ላይ እንደሚወጣ ያስታውሰናል። አብርሃም መሥዋዕቱን ወደ እግዚአብሔር ለማቅረግ ተራራ ላይ እንደወጣ፣ ሙሴም አሥሩን ትዕዛዛት ከእግዚአብሔር ለመቀበል ሲና ተራራ ላይ እንደወጣ እና በሉቃስ ወንጌል እንደተገለጸው የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ የተለወጠው ተራራ ላይ መሆኑን እናገኛለን። ስለዚህ ከፍ ወዳለ ሥፍራ መውጣት ፣ ከማይሆን ሕይወት ተላቅቀን ራስን ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ያለውን የልብ ፍላጎት ይገልጻል። “እኔ” ከሚል ራስ ወዳድነት ነፃ በመሆን፣ በከፍታ ወደሚገኝ እግዚአብሔር ለመድረስ መነሳታችንን ይገልጻል። ቆመን የምንጸልየውም ይህን ለመግለጽ ነው።

ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ከእርሱ ጋር ለመኖር እና በጸሎት ለመለወጥ ወደ እርሱ ማቅናት  የዛሬው የመጀመሪያ ርዕሣችን ሲሆን፣ ሁለተኛው እና አስፈላጊው ርዕሣችን ራስን ዝቅ ማድረግ የሚለው ነው። ራስን ዝቅ ማድረግ ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህንንስ እንዴት ማድረግ እንችላለን? ራሳችንን ወደ እግዚአብሔር ከፍ ማድረግ ከፈለግን ራሳችንን ዝቅ ማድረግ አለብን፤ ድክመታችንን እና ውስጣዊ ድኅነታችን ለማወቅ ከፈለግን ቅን አመለካከትን እና ትህትናን ማዳበር አለብን። በትህትና በእርግጥም የእግዚአብሔር መሆናችንን እና ወደ እርሱ የመቅረብ ብቃት እናገኛለን። ልባችንን በከበደው ቁስል፣ ኃጢአት እና መከራ ምክንያት የእግዚአብሔርን ምሕረት በመለመን፣ ፈውሱንም በማግኘት ከወደቅንበት እንነሳለን። ከውድቀታችን የሚያነሳን እግዚአብሔር ነው እንጂ እኛ አይደለንም። በትህትና ራሳችንን ዝቅ በማድረግ ወደ እግዚአብሔር በቀረብን ቁጥር እርሱ ያነሳናል።

በሉቃ. 18:13 ላይ፣ “ቀራጩ ግን በሩቅ ቆመና፥ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ ለማየት እንኳን አልደፈረም” ይላል። በሥራዎቹ ስላፈረ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ እንኳ አልደፈረም። እግዚአብሔርን ይቅርታ ለመነው፤ እግዚአብሔርም ይቅር ብሎት ከወደቀበት አነሳው። ነገር ግን ፈሪሳዊው ሰው በመተማመን መንፈስ፣ ምንም ክፋት እንደሌለበት በማመን፣ ስለ ራሱ ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ጀመረ፤ ሌሎችን ናቀ። ራሱን እያመሰገነ የሚሰሠራቸውን መልካም ሥራዎች እየዘረዘረ፣ "እኔ እንደዚያ ሰው አይደለሁም..." ብሎ መናገር ጀመረ። ሁላችንም በዚህ ወጥመድ ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። ይህ ትዕቢት ራስን ጻድቅ አድርጎ ወደ መቁጠር እና በሌሎች ላይ ወደ መፍረድ ያደርሳል። መንፈሳዊ ትዕቢት የሚባለው ይህ ነው። “እኔ ችግር የለብኝም! ከሌሎች እበልጣለሁ! ይህ ሰው ይህን ያደርጋል፣ ያኛውም ያንን ያደርጋል…” በዚህም ሳያስተውሉ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር በማጉደል በራስ ብቻ ይተማመናሉ። በራስ ዙሪያ ብቻ ይሽከረከራሉ። ትህትና የሌለበት ጸሎት ይህ ነው።

ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! የፈሪሳዊው እና የቀራጩ ሰው ሕይወት እንድናስብ ያደርገናል። ስለ እነዚህ ሁለት የተለያዩ ስዎች ስናስብ ራሳችንንም እንመልከት። እንደ ፈሪሳዊው ሰው ሌሎች ሰዎችን እንድንንቅ የሚያደርገን መመጻደቅ በልባችን ውስጥ ካለ ለይተን እንወቅ። ለምሳሌ መመስገንን ስንፈልግ እና ሁልጊዜ የራሳችንን መልካም ሥራ ብቻ ስንዘረዝር፣ ራስን ከመሆን ይልቅ ሌላ ሰው መስለን ለመታየት የምንጥር ከሆነ፣ በእርግጥም ከንቱ መመጻደቅ በልባችን ውስጥ አለ ማለት ነው። ራስን ማምለክ እና እዩኝ የማለት ባህርይ፣ ክርስቲያኖች፣ ካህናት እና ጳጳሳትም ጭምር በከንቱ ውዳሴ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን እንዲናገሩ ያደርጋቸዋል። ይህ ንግግር የቱ ነው? ብንል፥ እኔ እኔ ማለት፣ ‘ይህን ያደረግሁት እኔ ነኝ! ያንን የጻፍኩት እኔ ነኝ! ያንን የተናገርኩት እኔ ነኝ!’ ወዘተ። ብዙ “እኔ፤ እኔ” በሚባልበት፣ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ቦታ ጥቂት ብቻ ይሆናል። በብዙ አገሮች ሰዎች ‘እኔ፣ ከእኔ ጋር፣ ለእኔ፣ እኔ ብቻ" ሲሉ ይደመጣል። ስማቸውም ጭምር ‘እኔ’ የሚል ይሆናል። በአንድ ወቅት ሰዎች አንድ ካህን ስለ ለራሱ ብቻ እንደሚያስብ ይናገሩ ነበር። ሲቀልዱበትም፣ ‘እጣን ሲያጤን ሁሉ ራሱን ያጤናል’ ይሉት ነበር። እንደዚህ መሳቂያ ያደርጋችኋል።

እግዚአብሔር ፈቃዱ እንዲፈጸም ወደ መረጣት ሕያው ምልክት፣ በምስጋና ጸሎቷ፣ ታላላቅ ገዥዎችን ከዙፋናቸው እንዳወረዳቸው፣ ዝቅተኞችን ግን በክብር ከፍ እንዳደረጋቸው ወደተናገረች ትሑት የእግዚአብሔር አገልጋይ ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታችንን እናቀርባለን።

ምንጭ፡ የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)- ቫቲካ

 

 

08 Nov 2025, 16:53