ብጹዓን ጳጳሳት እና የዕርዳታ ድርጅቶች፥ የዓለም መሪዎች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በርትተው እንዲሠሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዓለም ለ30ኛው ዓመታዊ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP30) እየተዘጋጀች ባለበት በዚህ ወቅት ከመላው ዓለም የተውጣጡ የአገራት መሪዎች እና ተወካዮች በዓለም ላይ ትልቁ ደን ወደሚገኝባት ብራዚል በማምራት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
ይህን ዓለም አቀፍ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ የአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ኮሚቴዎችን የሚመሩ ሁለት ጳጳሳት እና የካቶሊክ ዕርዳታ አገልግሎቶች ፕሬዝዳንት፥ የአየር ንብረት ፖሊሲን በማስመልከት ባወጡት የጋራ መግለጫ፥ “የእግዚአብሔርን ፍጥረት እና የሰውን ልጅ ከጉዳት ለመጠበቅ አስቸኳይ እና ደፋር እርምጃ እንዲወሰድ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ወደ ነበረበት የመመለስ እና የማደስ ጊዜው አሁን ነው
መግለጫውን በጋራ ያወጡት፥ በአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የአገር ውስጥ ፍትህ እና የልማት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቦሪስ ጉድዚያክ፣ በአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዓለም አቀፍ የፍትህ እና የሰላም ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት አቡነ ኤልያስ ዛይዳን እና የካቶሊክ ዕርዳታ ድርጅት ፕሬዝዳንት እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ሲን ካላሃን መሆናቸው ታውቋል።
የኢዮቤልዩ በዓል በሚከበርበት የተስፋ ዓመት እና ሰላሳኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት የወጣው መግለጫው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “የምድሪቱን ጩኸት እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ድሆችን፣ ቤተሰቦችን፣ የአገሬው ተወላጆችን፣ ስደተኞችን እና ምዕመናንን ጩኸት ማዳመጥ ያስፈልጋል” በማለት ያቀረቡትን ጥሪ መሠረት ያደረገ እንደ ሆነ ታውቋል።
ጳጳሳቱ እና ዋና ሥራ አስፈፃሚው በመግለጫቸው፥ የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት የሕይወት ስጦታ በከባድ አደጋ ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የእርስ በርስ ግንኙነቶችን መልሶ ለመገንባት እና ፍጥረትን ለማደስ የተቀደሰ አጋጣሚ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥ በብዝሃ ሕይወት መጥፋት፣ በአካባቢ ብክለት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ማኅበረሰቦች እየተጎዱ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
“የእግዚአብሔርን ፍጥረት በአግባቡ አለመንከባከብ ለሰብዓዊ ቤተሰብ ያለብንን ኃላፊነት ችላ ማለት ነው” ሲል ያስጠነቀቀው መግለጫው፥ የእርሻ ማሳዎችን እና ዓሳን በማጥመድ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችን በየቀኑ የሚያጋጥማቸውን ስጋቶች በመጥቀስ የአገሬው ተወላጆች መሬት መጎዳት በዓለም አቀፍ ደረጃ በልጆች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የሚያስከትለውን አደጋ ገልጿል።
በትውልዶች መካከል ያለው አንድነት ከመጠበቅ ሌላ አማራጭ የለም
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቀ ጳጳስ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል ርዕሥ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው፥ የአየር ንብረት የሁሉ እና ለሁሉም የታሰበ የጋራ ጥቅም እንደሆነ ገልጸው፥ በትውልዶች መካከል ያለውን አንድነት መጠበቅ ምርጫ የሚቀርብለት አለመሆኑን በሠነዱ ውስጥ አብራርተዋል። በመሆኑም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቦሪስ ጉድዚያክ፣ አቡነ ኤልያስ ዛይዳን እና ሚስተር ሲን ካላሃን የፓሪሱን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ፈጣን እና ድፍረት የተሞላበት እርምጃ እንዲወስዱ በማለት ለዓለም መሪዎች ጥሪያቸውን አቅርበው፥ “በሁላችን ላይ ተጽዕኖን የሚፈጥር በመሆኑ ይህን ዓለም አቀፍ ፈተናን ለመፍታት የጋራ ኃላፊነታችንን መውሰድ አለብን” ሲሉ አሳስበዋል።
በብራዚል-ቤለም ከተማ በሚካሄደው ሰላሳኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ “COP30” ሁሉም አገሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ማኅበራት የጋራ ጥረቶችን እንዲያደርጉ፣ የልቀት ቅነሳን ለማድረግ የሚገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ ኪሳራን እና ጉዳትን ለመከላከል የተሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦችን በቀጥታ በመድረስ ዋስትናን የሚሰጥ፣ ማኅበረሰብን ማዕከል በማድረግ ዘላቂነት ወዳለው ፍትሃዊነት የሚደረገውን ሽግግር የሚያረጋግጥ እና የአየር ንብረት ፋይናንስ ለዕዳ ጫና እፎይታን በመስጠት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ተመልክቷል።
መግለጫው እንዳመለከተው፥ እነዚህ እርምጃዎች በሙሉ ለተቀናጀ ሥነ-ምህዳር እና በሂደቱ ውስጥ ለሚገኙ ድሆች እና በማኅበረሰቡ ለተገለሉ ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት ላይ ሊሠሩ እንደሚችሉ ገልጾ፥ ሊቀ ጳጳስ ጉድዚያክ፣ ጳጳስ ዛይዳን እና ሚስተር ካላሃን የድጋፍ እና የአንድነት ጸሎታቸውን በማቅረብ እንዲሁም የጋራ መኖሪያ ምድርን በጋራ ከጉዳት ለመጠበቅ ቃል በመግባት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።