የፍራንቺስካዊያን የመስቀሉ ሥር እህቶች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወደ ሆስፒታላችን የሚያደረጉት ጉብኝት 'ተዓምር ነው' ሲሉ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በሊባኖስ ጃል ኤድ ዲብ ከተማ የሚገኘውን የቅዱስ መስቀል የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታልን መጎብኘታቸው በእውነቱ ተዓምር ነው ሲሉ የሕክምና ማዕከሉን የሚመሩት የፍራንቺስካዊያን እህቶች ዋና ጸሐፊ ሲስተር ሜሪ የሱፍ ተናግረዋል።
የሀይማኖታዊ ቤተሰቡም ሆነ ሆስፒታሉ የተመሰረቱት እህት ሜሪ ‘አባ ያዕቆብ’ ብለው በሚጠሯቸው በብፁዕ ዣክ ሃዳድ ወይም “አቦና ያዕቆብ” መሆኑን የገለጹት እህት ሜሪ፥ እኚህ ሊባኖሳዊ የካፑቺን ካህን እ.አ.አ. ከ 1875 እስከ 1954 ዓ.ም. በህይወት እንደኖሩ እና ህይወታቸውን በሙሉ ድሆችን እና የተገለሉትን ለመንከባከብ የሰጡ መሆናቸውን አስታውሰው፥ የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታሉ በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙት ታላላቅ የአዕምሮ ህክምና ተቋማት አንዱ መሆኑን እና በቀን እስከ 1000 ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው እንደሆነ ገልጸው፥ ሃይማኖት እና ዜግነት ሳይገድበው የተቸገሩትን በሙሉ ተቀብሎ በማስተናገድ የሚታወቅ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ይህ ሆስፒታል ለሃገሪቷ ትልቅ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በሊባኖስ ላይ በደረሰው የድንገተኛ አደጋዎች ጫና ምክንያት፥ በተለይም በ 2012 ዓ.ም. የተከሰቱትን የኢኮኖሚ ቀውስ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ ቢጎዳም፥ ሆስፒታሉ ተልዕኮውን ለመቀጠል ችሏል።
በአሁኑ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ቤተክርስቲያን ለድሆች እና በጣም ተጋላጭ ለሆኑት ባላቸው ፍቅር ላይ በሚያተኩረው የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው በሆነው ‘ዳይሌክሲ ቴ’ ላይ በገለጹት መሰረት ከህዳር 21 እስከ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ሊባኖስን በሚጎበኙበት ወቅት ይሄንን ማዕከል በልዩነት እንደሚጎበኙ እና በዚህም ለታካሚዎች በተለይም የአእምሮ እና የአካል እክል ላለባቸው ድጋፋቸውን እና ቅርበታቸውን ያሳያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሆስፒታሉ የሚያደርጉት ጉብኝት ‘በሌላ ሰው ሊታከሙ የማይችሉትን ሰዎች የመንከባከብ ሀሳብ ለነበረው’ የሆስፒታሉ መስራች አባ ያዕቆብ የተሰጠ ስጦታ መሆኑን በአጽንዖት የገለጹት እህት ሜሪ፥ “እነዚህ ታካሚዎች ወደ እኛ ሆስፒታል ባይመጡ ኖሮ ሌላ የሚሄዱበት ቦታ አይኖራቸውም ነበር” በማለት አክለዋል።
ሌላ ማንም አጋዥ የሌላቸውን ሰዎች የሚያገለግሉ እህቶች
እህት ሜሪ የሆስፒታል ሥራ ውስጥ በቀጥታ ባይሳተፉም፥ የገዳሙ ዋና ጸሐፊ በመሆን የገዳማዊያቱን ሥራ በቅርበት የሚከታተሉ መሆኑን እና የገዳማዊያቱ ተቀዳሚ አገልግሎት የምሕረት ሥራ እንደሆነ ገልጸው፥ የገዳሙ መስራችም ማህበሩን ያቋቋመው ለዚሁ ተግባር መሆኑን አስረድተው፥ መስራቹ ‘በሕዝብ መካከል የእግዚአብሔር ልብ እና እጆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ’ ማለቱን አስታውሰዋል።
እ.አ.አ. በ 1930 ዓ.ም. የተመሰረተው የፍራንቺስካዊያን የቅዱስ መስቀሉ ሥር እህቶች ማህበር በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ እና በሌሎች ሀገራት ውስጥ የሚገኙ 23 ተቋማትን እንደሚያስተዳድር እና ከእነዚህም ውስጥ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የህክምና ማዕከላት እና ሌሎችም ተቋማት የሚገኙበት ሲሆን፥ ይህም የአካል ወይም የአዕምሮ እክል ያለባቸውን፣ አረጋውያንን እና ወላጅ አልባ ህጻናትን በመንከባከብ ላይ በማተኮር እንደሚሰራ ተገልጿል።
የአዕምሮ ሆስፒታሉ በአምስት እልፍኞች የተለያዩ የህመም አይነቶችን የሚያክም ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የመድሃኒት ቤት፣ የተመላላሽ ታካሚዎች ክሊኒኮችን፣ የህክምና ክፍሎችን እና ሌሎችንም እንደሚያካትት እና ሆስፒታሉ ከአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች እስከ ሥር የሰደደ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች፣ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው የተተው ሰዎችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እንደሚደግፍ የገለጹት እህት ሜሪ፥ “በእርግጥ ህሙማኑ የሚንከባከባቸው ማንም ሰው ስለሌለ ሆስፒታሉን እንደ ቤታቸው አድርገው ይቆጥሩታል” ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በሆስፒታሉ ውስጥ ወደ 800 የሚጠጉ ታካሚዎች እንዳሉ እና ከ40 በላይ እህቶች ከሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ጋር አብረው እንደሚሰሩ የተገለጸ ሲሆን፥ በማዕከሉ ውስጥ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ እና ለሌሎች ታካሚዎች በመጸለይ በዚህ መልኩ ሥራቸውን የሚደግፉ 20 አረጋውያን መነኮሳት መኖራቸውም ተነግሯል።
እነዚህ ታካሚዎች በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተወደዱ መሆናቸው
“ሆስፒታሉ አነስተኛ መንደር ነው” ያሉት እህት ሜሪ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከባድ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ህፃናት የሚያስተናግደውን የ ‘ቅዱስ-ዶሚኒክ’ ፓቪልዮንን ወይም እልፍኝ እንደሚጎበኙ ገልጸው፥ “ህሙማኑ መጓዝ ስለማይችሉ ብፁዕነታቸው ወደ እነርሱ ይሄዳሉ” በማለት ገልጸዋል።
ታማሚዎቹ እራሳቸውን እያዘጋጁ እንደሆነ እና በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት በጣም መደሰታቸውን የጠቆሙት እህት ሜሪ፥ ‘አንድ በጣም አስፈላጊ ሰው እነሱን ለማየት ብቻ ወደ ሆስፒታል እንደሚመጣ እንደሚሰማቸው እና በዚህም ደስታቸው ወደር እንደሌለው’ ገልጸው፥ ቅዱስ አባታችን ወደ እነሱ ስለሚመጡ እጅግ በጣም ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ገዳማዊያቱም ጭምር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፥ ‘ይህን ጉብኝት ለእያንዳንዱ እህቶች በግለሰብ ደረጃ እንደተሰጠ ልዩ በረከት እና ተሃድሶ እንደሚቀበሉት’ ጠቁመው፥ ለዚህም ራሳቸውን ከልብ እያዘጋጁ እንደሆነ እና አካላዊ ድካም ቢኖርም ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት ጀምሮ እስከ 105 ዓመት ያሉ ገዳማዊያት በሙሉ በእውነት ደስተኛ እንደሆኑ አስረድተዋል።
“በእርግጥ ይህ ይገባናል ወይ ብለን እየተገረምን እንገኛለን” ያሉት እህት ሜሪ፥ ‘ይህ ጉብኝት እንዲደረግልን ስላደረጉ መስራታችንን እናመሰግናለን’ ካሉ በኋላ፥ እነዚህ በሽተኞች በቅዱስ አባታችን እና በቤተክርስቲያን ልብ ውስጥ ምን ያህል ውድ እንደሆኑ ገልጸው፥ “እኛ በአባ ያዕቆብ የተመሰረትነው ትሑት የፍራንሲስካውያን የመስቀል እህቶች እንደዚህ አይነት ጉብኝት ይገባናል ወይ በማለት እያንዳንዱ ሰው እራሱን እየጠየቀ ነው” በማለት ገልጸዋል።
በልባቸው ‘ቤተክርስቲያን ይህን ያህል የምታከብረኝ ከሆነ ምን ያህል በራሴ ላይ ደጋግሜ መስራት አለብኝ’ በማለት እራሳቸውን እንደሚጠይቁ የገለጹት እህት ሜሪ፥ የእርሳቸውንና የሌሎች ገዳማዊያት እህቶችን ተልዕኮ በማሰላሰል ‘እንባ በከንቱ እንደማይፈስ እና ፈተና ሁሉ የትንሳኤ መንገድ ሊሆን እንደሚችል’ አስረድተው፥ ቅዱስ አባታችን በተመረጡ ጊዜ “በክርስቶስ አማካይነት ሁላችንም አንድ ነን” በሚለው መሪ ቃል መሰረት በእውነት በሰላም እንድንኖር የእግዚአብሔር ህልውና ወደ እኛ ዘልቆ እንዲገባ ማድረግ አለብን ብለዋል።
እህት ሜሪ በመጨረሻም ይህ ጉብኝት የብፁዕ ዣክን የቅድስና ሂደት የበለጠ ለማራመድ እንደሚረዳ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ‘ብፁዕነታቸው በተለይ የኢኮኖሚ ቀውሱ ቢያጋጥመንም ይሄንን በመቋቋም ተልዕኳችን በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ማንም ማድረግ የማይችለውን ይሄንን ጉብኝት በማድረጋቸው በእውነት ተዓምር ነበር’ በማለት አጠቃለዋል።