በቅድስት ማርያም ካቴድራል ለቦንዲ ባህር ዳርቻ ጥቃት ሰለባዎች የተደረገ የመታሰቢያ ሥነ ስርዓት በቅድስት ማርያም ካቴድራል ለቦንዲ ባህር ዳርቻ ጥቃት ሰለባዎች የተደረገ የመታሰቢያ ሥነ ስርዓት   (© Giovanni Portelli Photography/Catholic Archdiocese of Sydney)

የሲድኒ ሀገረ ስብከት የገና ብርሃን ትርዒትን ለቦንዲ ጥቃት ሰለባዎች መታሰቢያ ማድረጉ ተነገረ

የቦንዲ የባህር ዳርቻ የሽብር ጥቃትን ተከትሎ የሲድኒው ሊቀ ጳጳስ አንቶኒ ፊሸር የአካባቢው ማህበረሰብ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካቴድራል ፊት ለፊት የጥቃቱ ሰለባዎችን በልዩ የገና ብርሃን ትርኢት ላይ ለማስታወስ አንድ ላይ መሰባሰባቸውን ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአውስትራሊያ ቦንዲ ባህር ዳርቻ ላይ የደረሰው አሰቃቂ የጅምላ ጥቃት ከተፈጸመ ከሶስት ቀናት በኋላ የአካባቢው ማህበረሰብ ከዓመታዊ የገና አከባበር ባህላቸው ውስጥ አንዱ የሆነውን የብርሃነ ልደቱ ብርሃን ትርዒትን ለተጎጂዎች መታሰቢያነት ማዋላቸው ተነግሯል።

በየዓመቱ በሲድኒ የሚገኘው የቅድስት ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ፊት ለፊት ምዕመናን ሃይማኖታዊ ምስሎችን እና ታሪኮችን ይዘው በመውጣት የሚያከብሩ ሲሆን፥ አስደሳች በሆነው በዚህ የገና በዓል ላይ ለመካፈል በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች እና ወጣቶች ከተለያየ ቦታ እንደሚመጡ ተገልጿል።

የሲድኒ ሊቀ ጳጳስ አንቶኒ ፊሸር ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በዚህ ዓመት የተከበረው የቅድመ ገና ክብረ በዓል ለየት እንደሚል ገልጸው፥ ትዕይንቱን ለጥቃቱ ሰለባዎች መታሰቢያነት ለማድረግ መወሰናቸውን አስረድተዋል።

“ትዝታቸው ለበረከት ይሁን”
የአይሁድ ረቢዎች፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች፣ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የኒው ሳውዝ ዌልስ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎች ካቴድራሉ ፊት ለፊት የጸሎት ጊዜያትን ባካተተው መርሃ ግብር ላይ የተገኙ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ፊሸር እንደተናገሩት በዚህ ስፍራ የተሰበሰቡት ተሳታፊዎች “ሁሉም ሰው የሚከበርበት እና የሚወደድበት ሰላማዊ ማህበረሰብ” ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በዝግጅቱ ወቅት በጥይት የተገደሉትን እያንዳንዱን ሰው የሚወክል 15 ሻማዎች ያበሩ ሲሆን፥ የሂንዱ፣ የአይሁድ እና የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ሻማውን እንዲያበሩ ዕድል እንደተሰጣቸው ተነግሯል።

ጥቃቱ በተፈፀመበት ቦታ ላይ ቋሚ መታሰቢያ ሊቀመጥ እንደሚችል ፍንጭ የሰጡት ሊቀ ጳጳሱ፥ በአሁኑ ወቅት ቦታው በሚሊዮን በሚቆጠሩ የአበባ ጉንጉኖች መያዙን ገልጸው፥ የጥቃቱ ሰለባዎች እና ቤተሰቦቻቸው አለመረሳታቸውን እና ወደ ፊትም እንደማይረሱ ገልጸዋል።

“አበቦች በዚህ መጠን እየቀረቡ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ፊሸር፥ ለሌሎች ሰዎች ዕድል ለመስጠት ቀድመው የተቀመጡ አበቦች መነሳት እንዳለባቸው ጠቁመው፥ በዚህም ምክንያት ሥፍራው ሰዎች ለመጸለይ እና ሰለባዎችን ለማስታወስ የሚሰበሰቡበት ሀውልት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ገናን አስመልክቶ በሚከበረው የብርሃን ትዕይንት ላይ ዋና ምልክት የነበረው “ትዝታቸው ለበረከት ይሁን” የሚል የአይሁዶች አባባል የተፃፈበት የሻማ ማስቀመጫ ምስል እንደሆነ ተገልጿል።

የሁለት ዓመታት ውጥረት እየተባባሰ ነው
በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ጥቃት የተፈጸመው በሲድኒ ውስጥ ከነበረው የሁለት ዓመታት ውጥረት በኋላ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት በእስራኤል እና በጋዛ መካከል ስላለው ጦርነት ሰዎች የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው እና ከጦርነቱ ጋር የተያያዘው ፖለቲካ በተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ጨምሮ ከባድ ችግር ማስከተሉን አብራርተዋል።

ሰዎች በአመለካከት የመለያየት መብት እንዳላቸው የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ፊሸር፥ እነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ሰዎች የፀረ-ሴማዊነት አመለካከታቸውን እንዲያሳዩ ማስቻሉን እና ለአይሁዶች ያላቸውን የጥላቻ ደረጃ የሚያሳዩበት መሆኑን ጠቁመው፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተንኳሽ የሆኑ ንግግሮች እጅግ መበራከታቸው እንዲሁም የአሉታዊነት ስሜት እና እውነተኛ የሰላም እድልን አለማመን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሄዱን አመላክተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ፊሸር አንዳንድ ሰዎች ‘አንድ እስራኤላዊ በህይወት እያለ ጦርነቱ አያልቅም’ በማለት የሚናገሩትን ንግግር አስታውሰው፥ እንዲህ ዓይነቱ ንግግር ብጥብጥ እንደሚያስነሳ እና ይህ አስተሳሰብ አንዳንድ ወጣቶችን አክራሪ እያደረገ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል።

በሂደት ላይ ያለ ስራ
ይህ ጥቃት የተፈጸመው ሁሉም ካቶሊኮች እያንዳንዱን የፀረ-ሴማዊነት ተግባር እንዲቃወሙ ጥሪ የሚያደርገው እና ‘ኖስትራ አቴቴ’ የተሰኘውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ሰነድ 50ኛ ዓመት ባከበረች ማግስት መሆኑ ተነግሯል።

ሊቀ ጳጳስ ፊሸር ይህ የጥላቻ ስሜት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ የተከሰተ መሆኑን አስታውሰው፥ ይህም በመሆኑ ምክንያት ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላም ቢሆን ይህ የቫቲካን ጉባዔ ጥሪ በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ መኖር ያለበት ነገር መሆኑን አሳስበው፥ ደግመን ደጋግመን ሰዎች አይሁዶችን እንዲወዱ ጥሪ ማድረግ እንደሚገባ፥ በተለይም ክርስቲያኖች የአይሁድ ሕዝብ ዘሮች በመሆናቸው ይህ አስቸኳይ ጥሪ ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 11ኛ፣ ጳውሎስ ስድስተኛ እና ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ክርስቲያኖች የአይሁድ ልጆች መሆናቸውን ደጋግመው መግለፃቸውን ያስታወሱት የሲድኒ ሊቀ ጳጳስ፥ “ለወላጆቻችን እንደምናደርገው ሁሉ ለእነሱም ልዩ አክብሮት ልንሰጣቸው ይገባል” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ፊሸር አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ እየተስፋፉ ያሉ የሚመስሉትን ፀረ ሴማዊ ንግግሮች እና ባህሪያት ለመዋጋት ካቶሊኮች ሰዎችን ፍቅር እና አክብሮትን ለማስተማር፣ እንዲሁም አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ በግጭት ሳይሆን በሰላማዊ ውይይቶች ውስጥ እንዲሳተፉ ለማድረግ በስብከት እና በትምህርት በኩል እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

ለአንድነት እና አፍቃሪ ማህበረሰብ ለመገንባት ወደፊት መጓዝ
ሊቀ ጳጳስ ፊሸር እንዳብራሩት ምንም እንኳን ጥቃቱ በአይሁድ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም፥ በዚህ ጥቃት ምክንያት መላው ማህበረሰባቸው ልቡ እንደተነካ ገልጸው፥ በአውስትራሊያ እ.አ.አ. በ 1996 ከተፈጸመው የጅምላ ጥቃት በኋላ የጅምላ ግድያ የተለመደ አለመሆኑን የጠቆሙት ሊቀ ጳጳሱ፥ አብዛኛው ህዝብ ሃገሪቷ ደህንነቷ የተጠበቀ ሆኖ እንደሚሰማው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን ሰሞኑን የተፈጸመው ጥቃት ብዙዎችን ድንጋጤ እና ፍርሃት ውስጥ ያስገባ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ህዝቡ ከዚህ ጉዳት እንዲፈወስ እና ወደፊት እንዲራመድ ለመርዳት የቤተክርስቲያን ሚና ሞራላዊ ድጋፍ እና የሥነ ልቦና ምክር ላይ ማተኮር እንደሆነ እና ለሙታን መጸለይ እንደሆነ አብራርተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ የነበሩ ቦታዎች ለማጽናናት በሚመጡ ሰዎች ብዛት ተጨናንቀው ስለነበር ሃገረ ስብከታቸው ትምህርት ቤቶቻቸውን፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እና የምክር አገልግሎት ተቋሞቻቸውን አሳልፈው መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ፊሸር እንደገለጹት አሁንም ድረስ ለማቀራረብ የሚያስፈልጉ በርካታ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳን ከገና ብርሃን ትርኢት እና የመታሰቢያ አገልግሎት ጋር ወደፊት አዎንታዊ እርምጃ መኖሩን ጠቁመው፥ “ሰዎች አንድ እንድንሆን፣ እንድንከባበር እና በፍቅር እንድንኖር ይፈልጋሉ” በማለት ተናግረዋል።

በዝግጅቱ ላይ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተውጣጡ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በካቴድራሉ ፊት ለፊት ተገኝተው እንደነበር ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ ይህም በመሆኑ ምክንያት “ይህን የመታሰቢያ ሥነ ስርዓት ለማካሄድ ከሁሉ የተሻለው ቦታ የቅድስት ማርያም ካቴድራል እንደሆነ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች በጋራ መስማማታቸውን እና ምክንያቱም ደግሞ ይህ ስፍራ የሁሉም እምነት ተከታዮችን የማሰባሰብ ታሪክ እንዳለው በመግለጽ አጠቃለዋል።

19 Dec 2025, 13:29