መጥምቁ ዮሐንስ - መንግሥተ ሰማይ ቀራባለች እና ንስሐ ግቡ መጥምቁ ዮሐንስ - መንግሥተ ሰማይ ቀራባለች እና ንስሐ ግቡ 

የታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም የሁለተኛው ስብከተ ገና ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.      ኢሳያስ 11፡1-10

2.     መዝሙር 71

3.     ሮም 15፡4-9

4.    ማቴዎስ 3፡1-12

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት

በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። እንዲህም አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ።” በነቢዩ በኢሳይያስ “‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ” ተብሎ የተነገረለት ይህ ነውና። የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጠጉር የተሠራ ነበር፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበር። በዚያን ጊዜ ከኢየሩሳሌም፥ ከይሁዳ ሁሉና በዮርዳኖስም ዙሪያ ካሉ አውራጃዎች ሁሉ ሰዎች ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ ይጠመቁ ነበር።

ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ጥምቀት ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው “እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቁጣ እንድታመልጡ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ በልባችሁ ‘አብርሃም አባት አለን’ ብላችሁ አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት ይችላል እላችኋለሁ። አሁንም ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።

“እኔ ለንስሐ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን ለመሸከም የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹ በእጁ ነው፤ አውድማውንም ያጠራል፤ ስንዴውን በጎተራ ይከተዋል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው እሑድ የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት የምንጠባበቅበት የስብከተ ገና ሁለተኛ ሳምንት ነው። በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ላይ ከማቴዎስ ወንጌል ተወስዶ የተነበበው የዕለቱ ምንባብ የመጥምቁ ዮሐንስን ማንነት ይነግረናል። በወንጌልም እንዲህ የተጻፈውን እናገኛለን፥ “የዮሐንስ ልብስ ከግመል ጸጉር የተሠራ ነበር፥ . . . ምግቡም አንበጣ እና የበረሃ ማር ነበር።” (ማቴ. 3:4) (መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ያስተምር ነበር።” (ማቴ. 3:2) ባጭሩ የእግዚአብሔር መንግሥት መቃረቡን ይሰብክ ነበር። አጥማቂው ዮሐንስ መጀመሪያ ጊዜ ለሚያዩት ከባድ እና አጥባቂ ሰው በመምሰል ፍርሃት ሊቀሰቅስ ይችላል። እንዲህ የሚል ጥያቄ እራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን፥ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በምንጠባበቅበት ወቅት መጥምቁ ዮሐንስን ዋና የጉዟችን አጋር አድርጋ የምታቀርበው ለምንድነው? መጥመቁ ዮሐንስ ከጥንካሬው እና ከሚያሳየው የአጥባቂነት ስብዕና በስተጀርባ ያለው ምንድነው? የዮሐንስ ምስጢር ምንድነው? በመጥምቁ ዮሐንስ በኩል ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠን መልዕክት ምንድን ነው? ብሎ መጠየቁ መልካም ነው።

በእርግጥ መጥምቁ ዮሐንስ ከጥንካሬው በላይ የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን መመጻደቅ የሚቃወም ሰው ነው። ለምሳሌ በግብዝነታቸው የሚታወቁት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ሲቀርቡ የሚሰጣቸው ምላሽ በጣም ጠንካራ ነው! ዮሐንስ ተወዳጅ እና ታዋቂ እየሆነ በመምጣቱ አንዳንዶቹ በጉጉት ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። እነዚያ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ትክክል እንደሆኑ ይሰማቸው ስለ ነበር፣ የመጥምቁን ጥብቅ አቤቱታ በሰሙ ጊዜ ራሳቸውን ይበልጥ ጻድቅ አደረጉ። በልባችሁ አብርሃም አባት አለን ብላችሁ አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሳለት ይችላል እላችኋለሁ’ (ማቴ. 3:9)።

በሁለት ወገን እና ሃሳብ ውስጥ ሆነው ጸጋን የማግኘት እና አዲስ ሕይወት የመጀመር ዕድል አላገኙም፤ ፍትሃዊ ነን በሚል ግምት እራሳቸውን ዝግ አደረጉ። ስለዚህ ዮሐንስ፥ ‘እንግዲህ ለንስሐ የሚሆን ፍሬ አፍሩ’ አላቸው። (ማቴ. 3:8) ልጁ ራሱን ሲጎዳ ተመልክቶት፥ ‘ነፍስህን አትጣላት!’ እንዳለው አባት የፍቅር ምክር ነበር። በእርግጥም ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ! ግብዝነት ከሁሉ የከፋ አደጋ ነው። ምክንያቱም እጅግ የተቀደሱ እውነታዎችን እንኳን ሊያበላሽ ይችላል። ግብዝነት ከባድ አደጋ ነው! መጥምቁ ዮሐንስም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ግብዞችን የተቃወማቸው ለዚህ ነበር። በማቴ. ምዕ. 23 ላይ እንደምናነበው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በጊዜው ለነበሩ ግብዞች ድምጹን ከፍ አድርጎ መናገሩን እናገኛለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እና መጥምቁ ዮሐንስ ይህን ያደረጉት ለምንድነው? ይህን ያደረጉበት ምክንያት እነዚያ ግብዝ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ልብ ገዝተው ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነበር። በዚያን ጊዜ ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳ ሁሉና በዮርዳኖስም ዙሪያ ካሉ አውራጃዎች ሁሉ ሰዎች ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፤ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በእርሱ ይጠመቁ ነበር።’ (ማቴ. 3:5-6) እግዚአብሔርን መቀበል ትሕትናን እንጂ ችሎታን አይጠይቅም። እግዚአብሔርን የምንቀበለው በችሎታ ሳይሆን በትኅትና መንገድ ነው። “በትህትና እንጂ እኛ ጠንካራ እና ታላቅ ሕዝቦች ነን…” ማለቱ ዋጋ የለውም። "በተጨባጭ መንገድ በዚህ፣ በዚህ ምክንያት ኃጢአተኛ ነኝ" በማለት እያንዳንዳችን መጀመሪያ ኃጢአታችንን፣ ድክመታችንን፣ ግብዝነታችንን ለራሳችን መናዘዝ አለብን። አንድ ሰው እራሱን በከፍታ ካስቀመጥበት ወርዶ በንስሐ ውኃ ውስጥ መጠመቅ አለበት።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! መጥምቁ ዮሐንስ በጠንካራ ንግግሩ እንድናስብ ያደርገናል። አንዳንድ ጊዜ እኛም እንደ ፈሪሳውያኑ በግብዝነት እንጠቃ ይሆን? እሳችንን ከሌሎች የተሻልን በማድረግ፣ ሕይወታችን በእጃችን ውስጥ እንዳለ በመቁጠር፣ የእግዚአብሔር እና የቤተ ክርስቲያን አስፈላጊነት በመዘንጋት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንንቅ ይሆን? የስብከተ ገና ወቅት የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት በደስታ እንዳንጠባበቅ የሚያደርጉንን ነገሮች ከፊታችን የምናስወግድበት የጸጋ ወቅት ነው። እራሳችንን ከትሑታን ጋር በማድረግ፣ በራስ ከመመካት ነፃ በመውጣት ኃጢአታችንን ተናዘን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን ተቀብለን አዲስ ሕይወት ልንጀምር ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ የትህትና መንገድ ነው። ራሳችንን ከበላይነት እና ከግብዝነት ስሜት ነጻ የምናደርግበት፣ ሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንደ እኛ ኃጢአተኞች መሆናቸውን እና የአዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኛ መምጣት ማየት የምንችለው በትኅትና መንገድ ነው። ይህን የትኅትና መንገድ የምንከተለው ለሌሎች ሳይሆን ለራሳችን ስንል ነው። ከድህነታችን፣ ከመከራችን እና ከሁሉ ጉድለታችን ጋር፣ ከሁሉም በላይ ከወደቅንበት ለመነሳት ካለን ፍላጎት ጋር ይቅርታን እና ድነት ማግኘት ያስፈልጋል።

አንድ ተጨማሪ ነገር ልናስታውስ ይገባል፥ ሕይወትን እንደገና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመጀመር ዕድሉ አለን፤ አልዘገየም። አይዞአችሁ! ኢየሱስ ክርስቶስ ቅርባችን ስለሆነ ይህ ጊዜ የመለወጥ ጊዜ ነው። "የሚያሳፍረኝ ችግር በውስጤ አለ" ብሎ ሁሉም ሰው ሊያስብ ይችላል። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጎንህ ከጎንሽ ነው። የሕይወት ጉዞን እንደገና መጀመር፣ ሌላ ተጨማሪ እርምጃ የመራመድ ዕድሉ ሁል ጊዜ አለ። እርሱ ሳይሰለች ይጠብቀናል። በፍጹም አይሰለችም! እኛ ሰልችቶን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ እርሱ ግን ተስፋ ሳይቆርጥ ይጠብቀናል። ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ የሚለውን የመጥምቁ ዮሐንስን ጥሪ እናዳምጥ። የስብከተ ገና ወቅት እንደ ሌሎች ጊዜያት ተመልክተነው በከንቱ ማለፍ የለበትም። ምክንያቱም ይህ ወቅት ለእኛ የጸጋ ወቅት ነው። የእግዚአብሔር ትሑት አገልጋይ የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር እና በትሕትና ጎዳና ላይ ከሚገኙት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ወደ ፊት መጓዝ የምንችልበትን ብቸኛውን የትኅትና መንገድ በማሳየት ትርዳን።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

20 Dec 2025, 14:16