ፓትርያርክ ሚናሲያን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሐዋርያዊ ጉብኝት ‘ሕመምን ወደ ተስፋ የለወጠ’ እንደሆነ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአርመናዊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ራፋኤል ቤድሮስ 21ኛ እንደተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሊባኖስ ባደረጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት በምድሪቷ ተስፋ፣ አንድነት፣ ሰላም እና ፍትሕን መዝራታቸውን ገልጸዋል።
ፓትርያርክ ሚናሲያን ራፋኤል ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ህዳር 24 የተጠናቀቀውን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን የመጀመሪያ ሐዋርያዊ ጉዞ አስመልክተው እንደተናገሩት ጉብኝቱ ለምድሪቱ ተስፋን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
ህያው እና ታማኝ ህዝብ
ፓትርያርክ ሚናሲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቱርክ እና ሊባኖስ በሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ንቃተ ህሊና እና እምነት መደነቃቸን ገልጸው፥ ብፁዕነታቸው በጉብኝታቸው ወቅት በዚህ የዓለም ጥግ ላይ በእምነቱ የጸና፣ በዝምታ የሚሰቃይ ነገር ግን ፅናቱ ጠንካራ የሆነ ህዝብ መኖሩን በአግራሞት መናገራቸውን አስታውሰዋል።
ፓትርያርኩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት እና በቤይሩት የውሃ ዳርቻ ላይ በተካሄደው የመዝጊያ ሥርዓተ ቅዳሴ ወቅት እነዚህን ባሕርያት በአካል ተገኝተው ማየታቸውን ገልጸዋል።
የሌላን ሰው ህመም መረዳት እና ማስተጋባት
ፓትሪያርክ ሚናሲያን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር የነበራቸውን ቆይታ በልዩ ስሜት በማስታወስ፥ “እኛ እየኖርንበት ያለንበትን ሁኔታ ስገልጽላቸው፥ ችግሩን ወደራሳቸው አምጥተው ለመረዳት እንደሞከሩ ከእይታቸው መረዳት ይቻላል” ያሉ ሲሆን፥ የብፁዕነታቸው ሁኔታ በልብህ ውስጥ ያለውን ጉዳት እንደሚረዳ እና ያንን ጉዳት እንደሚሸከም ሰው፥ ብሎም ጉዳቱን ወደ አዎንታዊ፣ ጥልቅ እና ጠንካራ ተስፋ እንደሚለውጠው ያስታውቃል ብለዋል።
የክልሉን ሰፊ ተግዳሮቶች ያነሱት ፓትሪያርክ ሚናሲያን ሰላምን ከእውነተኛ ፍትህ ፍለጋ ውጭ መገንባት እንደማይቻል አፅንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ በማህበራዊ እና በግል ለውጦች ላይ የተመሰረተ የሰላም ጥሪ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ የተደረገ ግብዣ
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉዞ ሁሉም የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሳኤ ጀምሮ 2,000 ዓመታት የተቆጠረበትን እና በጎረጎሳዊያኑ በ 2033 በኢየሩሳሌም በሚከበረው የድነት ኢዮቤልዩ ላይ እንዲገኙ የተደረገ ግብዣን እንደሚያካትት የገለጹት ፓትሪያርክ ሚናሲያን፥ ይህ ጅምር እንደሆነ እና አንድነት አስቀድሞ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል መኖሩን ጠቁመው፥ የመላው ቤተክርስቲያንን ጉዞ “የማይበገር መሳሪያ” ወደሆነው ጸሎት እንዲሆን አሳስበዋል።
“በፍፁም ብቻችንን አይደለንም”
ፓትርያርክ ሚናሲያን በመጨረሻም ለጳጳሳዊ መስዋዕተ ቅዳሴ ለጸሎት የተሰበሰቡትን እጅግ በርካታ ሰዎች በማስታወስ ‘ከመቶ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች በጋራ ሲጸልዩ በማየታቸው ልባቸው በደስታ በጣም እንደተነካ’ አስታውሰው፥ በመጨረሻም ‘መቼም ቢሆን ብቻችንን ያልቀረነው ለዚህ እንደሆነ ገልጸው፥ አብረን መጓዛችንን መቀጠል ያለብን በዚህ መሠረት ላይ ነው” በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።