ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ኢስቶኒያ ዋና ከተማ ታሊን በተካሄደው የሰማዕቱ ጳጳስ ብፁዕ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች ጉባኤ ላይ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ኢስቶኒያ ዋና ከተማ ታሊን በተካሄደው የሰማዕቱ ጳጳስ ብፁዕ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች ጉባኤ ላይ 

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር እግዚአብሔር ህዝቡን ከጥላቻ አመድ ውስጥ መልሶ ሊገነባ ይችላል ማለታቸው ተነገረ

በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በሶቪየት አገዛዝ ዘመን ሰማዕት የሆኑ፣ ‘የዲፕሎማሲያዊ እና ቅድስና’ ዓርማ ተደርገው የሚወሰዱት እንዲሁም በሁሉም የጭቆና ዓይነቶች ውስጥ እውነትን ብቻ በማገልገል የሚታወቁት ብፁዕ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊችን አስመልክቶ በተካሄደ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ኢስቶኒያ፣ ታሊን ከተማ እንደተገኙ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሊቀ ጳጳስ ሪቻርድ ጋላገር የኢስቶኒያ ዋና ከተማ በሆነችው ታሊን ውስጥ ከየካቲት 13 እስከ 14 ድረስ ብፁዕ ኤድዋርድን በማስመልከት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በስፍራው የተገኙ ሲሆን፥ ብፁዕ ኤድዋርድ በሶቪየት የግዛት ዘመን በኢስቶኒያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የነበሩ፣ ለሰላምና ለነጻነት ሰማዕት የሆኑ ጀርመናዊ የኢየሱሳዊያን ማህበር ሊቀ ጳጳስ እንደነበሩ ተገልጿል።

ጳጉሜ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በታሊን ውስጥ ብፅዕናቸው የታወጀላቸው ሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ የ ‘ዲፕሎማሲ እና የቅድስና’ ህብረትን የሚወክሉ በዘመኑ ተምሳሌታዊ ገጽታ የነበራቸው አገልጋይ እንደነበሩ ተነግሯል።

በዲፕሎማሲ እና በቅድስና መካከል ያለው ቀይ ክር 
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በስፍራው ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የኢየሱሳውያን ማህበር ሊቀ ጳጳሱን “ቀጭን ቀይ ክር፣ ነገር ግን የማይበጠስ” በማለት የገለጿቸው ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳሱ በእነዚህ የባልቲክ ሃገራት ውስጥ እንኳን ሳይቀር ከፍተኛ ዲፕሎማሲን የቤተክርስቲያንን ታሪክ ከሚምሰክሩ ታላላቅ አገልጋዮች ተልእኮ ጋር ያዋሃዱ ሰው እንደነበሩ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ እ.አ.አ. በ 1942 ዓ.ም. በ51 ዓመታቸው በኪሮቭ ማረሚያ ቤት ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸው የተነገረ ሲሆን፥ እዚያም “እውነትን እና ሰብአዊነትን የሚጠላ ስርዓት ሰለባ” በመሆን በእስር ላይ በቆዩበት እና በስለላ ወንጀል በተከሰሱበት የሃሰት ክስ በጥይት ተመተው እንዲገደሉ ተፈርዶባቸው ሲጠባበቁ እንደነበር ተገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር የኢየሱሳዊያን ማህበር አገልጋዩ መስዋዕትነት በቤተክርስቲያኒቷ አረዳድ ዲፕሎማሲው እና የሃዋሪያዊ ሥራ ምንም እንኳን በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ቢኖሩም አንድ መሰረት እንዳላቸው፥ በሁሉም ዓይነት የጭቆና ሂደቶች ውስጥ ለእውነት እና ለሰብአዊ ፍቅር በማገልገል እንዴት እንደሆነ አሳይተዋል በማለት አብራርተዋል።

ድልድይ ገንቢ እና የታሪክ ጀግና
ከዚህም ባለፈ የጀርመን ተወላጅ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ ‘በፍቅር እና በምርጫ’ ኢስቶኒያዊ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በኢስቶኒያ ያላቸውን ተልዕኮ ለመወጣት ‘የውጭ ሃገር ዜጋ’ ሆኖ መቆየት እንደማይቻል በመረዳት ሆን ብለው ‘ሁሉንም ነገር ለሁሉም’ መሆንን የመረጡ ሲሆን፥ በተለይም እንደሌሎች ‘የባልቲክ ጀርመናውያን’ ወደ ጀርመን ከመመለስ ይልቅ በሶቭየት ህብረት ኢስቶኒያ በተያዘችበት ጊዜ እዛ መቆየትን መምረጣቸው ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት የኢስቶኒያን ህዝብ አሳዛኝ እጣ ፈንታ የተካፈሉ ሲሆን፥ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት “ሊቀ ጳጳሱ እዛ ለመቆየት መወሰናቸው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራቸውም እንደነበር አስረድተው፥ እንዲያውም ብፁዕ ኤድዋርድ በማስታወሻ ደብተራቸው ላይ እንዳስታወቁት “የማይታመን ደስታን” እና “ጥልቅ የሰላም ስሜትን” እንዳገኙበት አስታውሰዋል።

እንደ አብዛኛው ቅዱሳን ሊቀ ጳጳሱም “ከብሔራዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ ማንነታቸው መውጣት መቻላቸው እና በዚህም ምክንያት ከአገልጋይም በላይ “እውነተኛ ጳጳስ” እንደነበሩ፥ እንዲሁም የካቶሊክ መገኘት አናሳ በሆነበት ምድር “ያልተለመደ ድልድይ ገንቢ እና አስታራቂ” እንደነበሩ ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊው አክለውም ኢየሱሳዊው ሊቀ ጳጳስ ‘የአንድን ህዝብ ክብር ከፍ ለማድረግ የሚረዳ የሰብዓዊ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት መረብ እንዴት እንደሚታደስ’ ያውቁ እንደነበረ ገልጸው፥ ተልዕኮዋቸው ፖለቲካዊ ባይሆንም፥ ነገር ግን ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተፅእኖ እንደነበረው አስታውሰዋል።

“ብፁዕ ኤድዋርድ ታላላቅ አምባገነናዊ አስተሳሰቦች የኢስቶኒያን ማንነት ለማፈን በሚፈልጉበት ጊዜ ለሃገሪቷ የሞራል ድምጽ ሆነዋል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በኢስቶኒያ ታሪክ እንደ ታላቅ ጀግና ተደርገው እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።

እውነት የሰው ልጅ አስተሳሰብ እና ተግባር ነፍስ መሆኗ
በአሰቃቂ ምርመራ እና እስራት ጊዜ እንኳን ቢሆን ሊቀ ጳጳሱ ጽናታቸው ፈጽሞ እንዳልተለያቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ‘ለላይኛው እውነት ታማኝ ሆነው መኖራቸው እና ፍቅር ክፋትን ማሸነፍ የሚችል ብቸኛው ሃይል መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በአጽንዖት ገልጸዋል።

“በዚህም ምክንያት አሁን ባለንበት የግጭቶች እና ስጋቶች ዘመን ታሪካቸው በፍጥነት ያበረታታናል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ በቅዱሳን ተልዕኮ ውስጥ እንደ አንድ ከፍተኛ ዲፕሎማሲ ‘እውነት ተቀጥላ ነገር ሳትሆን፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አስተሳሰብ እና ተግባር ነፍስ ናት’ ብለዋል።

መከፋፈልን ለማስወገድ የቤተክርስቲያን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት
የኢስቶኒያው ሊቀ ጳጳስ የሰው ልጅ ክብር አደጋ ላይ ሲወድቅ ከዝምታ የበለጠ አደገኛ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ እውነትን በቃልና በተግባር ከማውጣት ወደ ኋላ አለማለታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ መንፈስ ባለፈው ክፍለ ዘመን በዚህ የአውሮፓ ክፍል ለነጻነት እና ለፍትህ በሚደረገው ትግል ውስጥ በርካታ ወንዶችን እና ሴቶችን ማነሳሳቱ ተገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር እንዳሉት ይህ መንፈስ የሚታየውን መከፋፈል ለማሸነፍ ዓላማ በማድረግ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የምታደርገውን እያንዳንዱን ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ መምራት እንዳለበት አሳስበው፥ ቅዱሳን አገልጋዮች በሰው ልጅ እውነት ላይ እንደማይደራደሩ እንዲሁም መልሳቸው ለሕይወት ቆራጥ የሆነ እና አምባገነንነትን በጽኑ የሚቃወሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በማከልም ሁለቱም የሃዋሪያዊ ሥራ እና የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎች ሁልጊዜ ርቀቶችን ማገናኘት፣ መለያየትን ማስወገድ፣ ለውይይት እና ለግንኙነት ቦታ መስጠት መሆኑን ጠቅሰው፥ የመጨረሻው ተጠቃሚ ሁል ጊዜም የሰው ልጅ መልካም ተግባር መሆን እንዳለበት እና እውነተኛ ሰላም አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት የዚህ በጎ ሥራ ፍሬ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

የማይሆን ነገር የሚቻል ይሆናል
ከዚህ በመነሳት ጥሪው መሆን ያለበት “ሀገራትን ከጥላቻ አመድ መልሶ መገንባት የሚችለው የእግዚአብሔር ፍቅር ብቸኛው ኃይል ነው” በማለት ለመመስከር ዝግጁ የሆኑ ‘የሰላም አምባሳደሮች’ እንድንሆን የጠቆሙት ሊቀ ጳጳስ ጋራገር፥ ከዚህም በተጨማሪ በኢስቶኒያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች በቁጥር አነስተኛ ማኅበረሰብ ቢሆንም ቤተክርስቲያኒቷ የምታሳየውን “ታማኝነት” እና “የእረኝነት ተግባር” በማወደስ፥ የካቶሊክ ማህበረሰብ “ስፍር ቁጥር የሌላቸው በርካታ መከራዎችን ማሳለፉን አስታውሰዋል።

የበርሊን ግንብ ከፈረሰ ከአንድ ዓመት በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል ዳግማዊ ወደ ፕራግ ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ፥ ጉብኝታቸው “መለኮታዊ ምሕረት” “የክስተቶች ዝግመተ ለውጥን መፍቀዱ እና በጣም አጨቃጫቂ በሆነበት ቦታም ቢሆን የእምነት ዳግም መወለድ በዚህች የተከበረች ምድር እንዲፈጠር ማድረጉን አጽንዖት ሰጥተው በመግለጽ፥ ሁሉም ሰው ከጥቂት ወራት በፊት የተደረገውን ጉብኝት የማይቻል እንደሆነ አድርጎ ያስብ ነበር ብለዋል።

ዋናው ነጥብ የማይታሰብ የሚመስለው በእግዚአብሔር ዘንድ የሚቻል እንደሆነ የጠቆሙት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ በእርሱ መታመን እንዳለብን እና ዛሬ “የማይቻል” የሚመስለው ሰላም እንደሚፈጸም ያላቸውን እምነት በመግለጽ አጠቃለዋል።

23 Feb 2026, 13:09