በሮም ትራስቴቬር ውስጥ በሚገኘው የሳንታ ማሪያ ባዚሊካ ውስጥ በብፁዕ ካርዲናል ዙፒ መሪነት የተደረገው የጸሎት መርሐ ግብር በሮም ትራስቴቬር ውስጥ በሚገኘው የሳንታ ማሪያ ባዚሊካ ውስጥ በብፁዕ ካርዲናል ዙፒ መሪነት የተደረገው የጸሎት መርሐ ግብር  (ANSA)

ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ቤተክርስቲያን በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ ታቀርባለች ማለታቸው ተነገረ

የጣሊያን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ማሪያ ዙፒ የዩክሬን ጦርነት የተጀመረበትን አራተኛ ዓመት ለማስታወስ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ ባዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ ሮም ተገኝተው እንደነበር ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ የተዘጋጀው እና በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን በተደረገው የጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ ብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ዙፒ “ሳንደክም ሁልጊዜ መጸለይ የምንችለው እንዴት ነው?” በሚል ሃሳብ አስተንትኖ ያደረጉ ሲሆን፥ የካቲት 17 የተካሄደው ይህ የአምልኮ ስነ ሥርዓት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ሙሉ ወረራ የጀመረችበትን አራተኛ ዓመት ለማስታወስ ሮም፣ ትራስቴቬር ውስጥ በሚገኘው የሳንታ ማሪያ ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደ መርሃ ግብር ወቅት እንደሆነ ተገልጿል።

‘መጠበቅ ባልተለመደበት ዘመን ጸሎት ጽናት መጠየቁን ቀጥሏል’ ያሉት የጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ፥ ጸሎት ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ በአንዳንድ ልማዶቻችን እና ስንፈቶቻችን እንዳንሸነፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፥ ምክንያቱም ይህ በመጨረሻም በክፋት ላይ፣ በጦርነት ላይ እንዲሁም ‘በዓለም አቀፋዊ ግዴለሽነት’ ላይ የሚደረግ የአመፅ አይነት እንደሆነ አስረድተዋል።

“የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የምትጠይቀው የጦር መሳሪያዎች ዝም እንዲሉ ብቻ ነው” ያሉት ካርዲናሉ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ደጋግመው እንደሚናገሩት “ቤተክርስቲያኒቱ ጥሪ የምታደርገው ጦርነት እንዲቆም፣ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና የሰላም መንገድ እንዲከፈት ብቻ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዩክሬን ጦርነት የተጀመረበትን ሦስተኛ ዓመት አስመልክተው ከዚህ ቀደም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እንደተናገሩት እነዚህ የጦርነቱ የአራት ዓመታት መታሰቢያዎች ለሰው ልጆች ሁሉ አሳዛኝ እና አሳፋሪ መሆናቸውን የጠቀሱ ሲሆን፥ “ውርደቱ ዛሬም መጨመሩን” ገልጸው፥ ግጭቶች በጦር መሳሪያ ሳይሆን በውይይት የሚፈቱ ናቸው በማለት በድጋሚ ተናግረዋል።

ይህ እንዲሳካ ግን ለጋራ ግብ አብሮ የመስራትን፣ ማህበራዊ እና የጋራ ስሜትን መመለስ አስፈላጊ እንደሆነ አስታውሰው፥ ምክንያቱም ሁላችንም ልንፈልገው የሚገባን ብቸኛው ድል የሰላም ትንሳኤ እንደሆነ፣ እንዲሁም “ይህን የሰላም ጩኸት እንድንሰማ” እና “ከድካም ነፃ እንድንወጣ” የሚያስችለን እና ይህ ድል የሚገኘው በጸሎት በመጽናት መሆኑን ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ገልጸዋል።

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ ቁርጠኝነት
በዚህ ረገድ እ.አ.አ. ከ 1991 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ ለዩክሬን ህዝብ ያለው አብሮነት እያደገ መምጣቱ መሰረታዊ ነገር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ ማህበረሰብ የሩሲያ ወረራ እንደጀመረ ሰፊ የሰብአዊ እርዳታ ትስስር ለመዘርጋት እንደቻለ ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበር በሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚያግዝበት ሦስት በኪየቭ፣ አንድ በሌቪቭ እና አንድ በኢቫኖ ከተማ በአጠቃላይ አምስት ማዕከላት ያሉት ሲሆን፥ ማህበሩ ጦርነት በሚካሄድባቸው ቦታዎች አቅራቢያ ባሉ ክልሎች በተለይም በክራማ-ቶርስክ፣ ኒኮፖል እና ሱሚ ከተሞች በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ 213 የእርዳታ ጭነቶችን፥ በድምሩ 4,450 ቶን ሰብአዊ እርዳታ የተላከ ሲሆን፥ 750,000 ሰዎች የምግብ፣ የአልባሳት እና የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ማግኘታቸው እና 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የህክምና እርዳታው ተጠቃሚ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፥ እነዚህ አሃዞች ጦርነቱ በሚቀጥልበት ወቅት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሚመጣ ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተነግሯል።

በዩክሬን ጦርነት የታየው ሰማዕትነት
በዩክሬን የታየውን የማህበረሰቡን ቁርጠኝነት በማስታወስ ስለ ህዝቡ “ደህንነት፣ የተስፋ ጭላንጭል እና የጋለ ስሜት” የተናገሩት ካርዲናል ዙፒ፥ ከዶንባስ የተፈናቀለችውን እና በአሁኑ ወቅት በኪየቭ ውስጥ በስደተኝነት የምትኖረውን ናዲያን በማስታወስ፥ ለቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበረሰብ ሚና ምስጋና ይግባውና “በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው የሌሎች ህይወት እንደሆነ” ናዲያ መረዳቷል ከጠቀሱ በኋላ፥ “ዓለም በፍቅር እጦት እየሞተች ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“ዓለም በሰዎች ጥላቻ እየሞተች ነው” ያሉት ካርዲናሉ፥ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ የተቀደሰ ጸጋውን፣ የተትረፈረፈ እና ሞቅ ያለ በረከቱን ከሰማይ እንዲያወርድልን መማጸናችንን ማቋረጥ እንደሌለብን መክረው፥ እያንዳንዳችን ከቅዱስ ጸጋው የሞቀ ዝናብ ጠብታ ልንሆን እንደምንችል እና እያንዳንዳችንም የፍቅር እጦትን ራሳችን በምንሰጠው ፍቅር ማሸነፍ እንደምንችል በመግለጽ አጠናቀዋል።

26 Feb 2026, 12:20