2026.02.17 thailand holy rosary church bangkok lunar new year 2026.02.17 thailand holy rosary church bangkok lunar new year 

በኢስያ የሚገኙ ካቶሊኮች የጨረቃን አዲስ ዓመት ማክበራቸው ተነገረ

በተለይ በቻይና እና በኢስያ ባሉ ሃገራት ውስጥ የጨረቃ ዑደትን መሠረት በማድረግ በሚቀመረው የዘመን አቆጣጠር አማካይነት የዘንድሮው አዲስ ዓመት የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን፥ ይሄንን ተከትሎ በመላው ኢስያ የሚገኙ የካቶሊክ ማህበረሰቦች እምነትን እና ባህልን በማጣመር በተለያዩ ቤተሰባዊ ጥምረቶች፣ የጸሎት መርሃ ግብሮች እና የበጎ አድራጎት ተግባራት ማክበራቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ሉናር” (Lunar) ማለት የጨረቃን ዑደት የተከተለ የቀን አቆጣጠር ማለት ሲሆን፥ ይህ አዲስ ዓመት የጸደይ ወቅት መባቻን የሚያበስር በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

በብዙ የኢስያ አገሮች የጨረቃ አዲስ ዓመት በቻይና ባህላዊ ወግ ላይ በመመስረት በስፍራው የሚገኙ ካቶሊካዊያን ቤተሰቦች የአባቶቻቸውን ልማዶች በመከተል ቀኑን በተለያዩ ክብረ በዓሎች በድምቀት እንደሚያከብሩ ይታወቃል።

ለቤተክርስቲያን ይህ ወቅት እንድምታው ከባህላዊ ፌስቲቫል በላይ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ በዚህ ወቅት የስብከተ ወንጌል፣ የምስጋና እና የቤተሰብ የእርቅ ጊዜያትን በማሳለፍ ለሃዋሪያዊ አገልግሎት መልካም እድልን እንደሚፈጥር ተገልጿል።

በዓሉን በዋነኝነት የሚያከብሩ ሀገራት ቻይና፣ ቬትናም፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ማሌዢያ፣ ታይላንድ እና ፊሊፒንስ ሲሆኑ፥ ባህልን በማስረጽ ዓይን ሲታይ ቤተክርስቲያን የጨረቃን አዲስ ዓመት የምትረዳው እምነት በኢስያ ህይወት ውስጥ በጥልቀት የገባበት ቅጽበት እንደሆነ ትገነዘባለች ተብሏል።

በክልሉ የሚገኙ አብዛኛው ካቶሊኮች አዲሱን ዓመት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የቤተሰባቸው እና የማህበረሰቡ ህይወት ማዕከል በማድረግ በአከባቢ ልማዶች በዓሉን እንደሚያከብሩ ይገለፃል።

በቬትናም እምነት እና ባህልን ማክበር
በቬትናም የጨረቃ አዲስ ዓመት ‘ቴት’ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ የዚህ ክብረ በዓል ዝግጅት የሚጀመረው የገና ሳምንት በሚገባበት የመጀመሪያ ቀን እንደሆነ እና የአከባቢው ቤተሰቦች ባህላዊ ምግቦችን በተለይም ከሩዝ የሚሰሩ ኬኮችን በማዘጋጀት፣ ቤታቸውን በማስጌጥ እና የቤተሰቦቻቸውን የመቃብር ስፍራ በማጽዳት እንደሚጀምሩ ተገልጿል።

ለካቶሊኮች እነዚህ ልምምዶች የሚታዩት በመንፈሳዊ ዓይን እና ዓመቱን በአዲስ መንፈስ በእግዚአብሔር በመታመን ሲሆን፥ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ በርካታ አማኞች በልዩ የምስጋና ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ለመሳተፍ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በመሰብሰብ እንደሆነ ተነግሯል።

ምዕመናኑ ላለፈው ዓመት በረከቶች ፈጣሪን በማመስገን እና ለሚመጣው ዓመት ለጌታ ያላቸውን ክብር እና ቁርጠኝነት በማደስ የሚያሳልፉ ሲሆን፥ ቴት ተብሎ በሚታወቀው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት መስዋዕተ ቅዳሴዎች የሚደረጉት ለልዩ ልዩ ዓላማዎች እንደሆነ እና የመጀመሪያው ቀን ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት በማድረግ፣ ሁለተኛው ቀን በህይወት ያሉትንም ሆነ የሞቱትን አያቶች እና ወላጆች ለማስታወስ፣ ሦስተኛው ቀን ሥራን፣ ጥናቶችን እና የግል ጥረቶችን ለመባረክ በሚል እንደሚደረጉ ተገልጿል።

በቬትናም የምትገኘው ቤተክርስቲያን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ለበጎ አድራጎት ሥራዎች አጽንዖት የምትሰጥ ሲሆን፥ በርካታ ደብሮች ድሆችን በመጎብኘት የተለያዩ ምግቦችን እንደሚያከፋፍሉ እና በተለይም ባህላዊ የሩዝ ኬኮች ክርስቲያናዊ የመረዳዳት እና የመተሳሰብ ምልክቶች እንደሆኑ ተነግሯል።

ለቬትናም ካቶሊኮች እነዚህ ድርጊቶች የአዲሱን ዓመት እውነተኛ መንፈስ፣ በእምነት እና በሰላም ላይ የተመሰረተ ደስታን ያንፀባርቃሉ ተብሏል።

በታይላንድ ውስጥ ቤተሰብ እና ጸሎት
የታይላንድ ካቶሊኮች በበኩላቸው የጨረቃ አዲስ ዓመትን የቤተሰብ ግንኙነቶችን በማደስ፣ ሙታንን በማስታወስ እና ስለ ወደፊቱ ጊዜ በመጸለይ ላይ በማተኮር በተመሳሳይ መንፈስ የሚያከብሩ ሲሆን፥ አባ ፒተር ፒያቻር ከሊካስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት “የጨረቃ አዲስ ዓመት የቤተሰብ ትስስርን ለማጠናከር እና ለሚመጣው ዓመት ለመጸለይ እድል እንደሚሰጥ” ጠቁመዋል።

በእነዚህ ጊዜያት ልዩ የምስጋና ቅዳሴዎች እንደሚደረጉ እና በዚህም ቤተሰቦች ተስፋቸውን እና እቅዳቸውን ለእግዚአብሔር አደራ እንደሚሰጡ አባ ፒተር የገለጹ ሲሆን፥ ለምእመናን ባስተላለፉት መልዕክት ከካቶሊክ አስተምህሮ ጋር የሚስማሙ ባሕላዊ ድርጊቶች የሚበረታቱ ቢሆንም አጉል እምነቶችን ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሃገሪቱ ውስጥ ከሚደረጉ የተለያዩ ልማዶች ውስጥ በጣም ጎልቶ የሚታወቀው ‘አንግ ፓኦ’ ተብሎ የሚታወቀውን ገንዘብ የያዙ ቀያይ ፖስታዎችን መስጠት እንደሆነ ገልጸው፥ የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴ ማጠቃለያ ላይ ይሄንን ባህላዊ አንግ ፓኦ ፖስታ ለሁሉም እንደሚያሰራጩ እና ይህ ምልክት የአዲሱን ዓመት አስደሳች ተስፋ ከቤተክርስቲያን የጋራ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር ለማያያዝ እንደሚያገለግል ጠቁመው፥ በዚህ ልምምድ ቁሳዊ ልግስና እንደ ማህበረሰብ አካል ከመንፈሳዊ ህብረት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ገልጸዋል።

በማሌዥያ ባህላዊ መግለጫዎች
በማሌዥያ አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ የጨረቃ አዲስ ዓመትን ለመቀበል በቀይ ፋኖሶች እና በዓሉን በሚገልጹ ባነሮች የሚያጌጡ ሲሆን፥ በርካታ ደብሮች በዓመቱ የመጀመሪያ ቀን ላይ የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚካፈሉ ተነግሯል።

ሆኖም አንዳንድ ካቶሊኮች የቅድመ አያቶቻቸውን የአምልኮ ሥርዓት ወይም ባህላዊ ክንውኖችን በመከተል የቤተሰብ ልማዶች ላይ ለመሳተፍ በሚል ከመስዋዕተ ቅዳሴው እንደሚቀሩ ተነግሯል።

ወላጆችን ለማክበር ከተሰጠው ትእዛዝ ጋር በሚስማማ መልኩ የአባቶችን አምልኮ በበርካታ ካቶሊኮች ዘንድ የልባዊ አምልኮ መግለጫ እንደሆነ በሰፊው የሚቀበሉት ሲሆን፥ ለእነዚህ ካቶሊካዊያን ይህ መርሃ ግብር ምስጋና እና ትውስታን የመግለፅ ባህላዊ መንገድ ተደርጎ እንደሚታሰብ ተገልጿል።

ሌሎቹ የህብረተሰቡ ክፍሎች ግን በሁሉም የነፍስ ቀን እና የቅዱስ ቁርባን በዓላት ላይ ለሙታን በሚደረጉ ጸሎቶች ላይ ማተኮርን የሚመርጡ ሲሆን፥ እነዚህ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም የጨረቃ አዲስ ዓመት በማሌዥያ ጥልቅ ቤተሰብን ያማከለ፣ እምነት የሚጎለብት እና የሚጠናከርበት በዓል እንደሆነ ተገልጿል።

የምስጋና እና የበጎ አድራጎት ወቅት
በመላው ኢስያ የጨረቃ አዲስ ዓመት የቤተሰብን፣ የምስጋና እና የልግስናን አስፈላጊነት የሚያጎላ ጉልህ ወቅት ሆኖ የሚከበር ሲሆን፥ በእነዚህ በዓላት ቤተክርስቲያን ለረጅም ጊዜ በቆዩ ባህላዊ ልማዶች ውስጥ ወንጌል በእውነተኛነት ጸንቶ መኖር እንደሚችል ትመሰክራለች ተብሏል።

በኢስያ የሚገኙ ካቶሊኮች የመከባበር፣ የመተሳሰብ እና የጸሎት እሴቶችን በመቀበል፥ የጨረቃን አዲስ ዓመት በትውፊት ላይ የተመሰረተ እና በክርስቶስ ብርሃን ወደሚበራበት የእምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ወቅት በመቀየር ማክበራቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል።

19 Feb 2026, 14:01