እየተገነባ በሚገኘው የሳግራዳ ፋሚሊያ ባዝሊካ ላይ ባለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ የካታላዊያን እና የቫቲካን ባንዲራዎች ተሰቅለው እየተገነባ በሚገኘው የሳግራዳ ፋሚሊያ ባዝሊካ ላይ ባለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ የካታላዊያን እና የቫቲካን ባንዲራዎች ተሰቅለው   (©Basílica de la Sagrada Familia, Barcelona, España)

በባርሴሎና የሚገኘው ‘ሳግራዳ ፋሚሊያ’ የተሰኘው ባዝሊካ ማዕከላዊ ክፍል ተሰርቶ መጠናቀቁ ተነገረ

በባርሴሎና ውስጥ እየተገነባ በሚገኘው ‘ሳግራዳ ፋሚሊያ’ በተሰኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ባዝሊካ ውስጥ እየተተከለ የሚገኘው ግዙፉ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሃውልት ላይ የሚከናወነው የመስቀሉ የላይኛው ክንድ የመትከል ሥራ የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፥ የባዝሊካው ከፍተኛውን የውጭ ሥራ መጠናቀቁ እና በመዋቅሩ የውስጠኛው ክፍል እ.አ.አ. በ 2027 እና 2028 ቀጥሎ እንደሚሰራ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በባርሴሎና ውስጥ አዲስ እየተሰራ በሚገኘው ካቴድራል ውስጥ እየተሰራ ያለው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃውልት የመስቀሉን የላይኛው ክፍል የመትከሉ ሥራ የካቲት 13 መጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን፥ ‘ሳግራዳ ፋሚሊያ’ የተሰኘው የዚህ ባዝሊካ ከፍተኛው ቦታ የሆነውን የማዕከላዊ ግንብ ውጫዊ ሥራዎች መጠናቀቃቸው እና የመዋቅሩ የውስጠኛው ክፍል ሥራዎች በአውሮፓዊያኑ 2027 እና 2028 ቀጥለው እንደሚሰሩ ተነግሯል።

አራት በአራት ሜትር ስፋት እና ቁመት ያለው ይህ ሃውልት በአሁኑ ወቅት የባዝሊካው ከፍተኛው ቦታ ሆኖ የሚታይ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ በሳግራዳ ፋሚሊያ ውጫዊ ክፍል የሚገኙ የስድስት ማዕከላዊ ማማዎች ስብስብ ተሰርተው መጠናቀቃቸው ተገልጿል።

“ከአራቱ በጣም ረዣዥም የመስቀለኛ አምዶች በላይ ከፍ ሲል፣ ታላቁ የፋኖስ ግንብ ወይም ማማ አብሮ ከፍ ይላል፥ ገጽታው ሊታይበት የሚችልበት አራት ክንዶች ያለው አስደናቂ መስቀል 176 ሜትር ከፍታ ላይ ዘውድ ተጎናጽፏል፣ በመሃሉም ‘አግነስ ዴይ’ ወይም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል ይቀመጣል” የሚለው እና እ.አ.አ. በ 1929 በተፃፈው የሳግራዳ ፋሚሊያ ገላጭ ቤተመቅደስ አራተኛው አልበም መጽሃፍ ላይ የተወሰደው ጥቅስ የፕሮጀክቱን ተምሳሌታዊ ራዕይ የሚገልጽ መሆኑ ተገልጿል።

የማዕከላዊ ግንብ መዋቅር እና ባህሪያት
በኢየሱስ ክርስቶስን ምስል የተሰራው ሃውልት በባዚሊካው የመሃለኛው ክፍል ላይ የቆመ ሲሆን፥ ይህም እያንዳንዳቸው ከማዕከላዊው ግንብ ጋር እና በውስጠኛው ክፍል ባለው የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሃውልት ጋር በድልድይ የተገናኙበት በአራቱ የወንጌላውያን ማማዎች የተከበበ መሆኑ ትገልጿል።

ጥቅምት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው እና በ 85 ሜትር ከፍታ ላይ በባለ 12 ገጽ ደረጃዎችን የሚያካትተው ይህ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃውልት ባለ አስራ ሁለት ጎን የወለል ፕላን ያለው ሲሆን፥ አጠቃላይ ቁመቱ 172.5 ሜትር ይደርሳል ተብሏል።

ፓነሎች የተገነቡት ቀደም ብለው በተዘጋጁ ድንጋይ እና ብረትን በማጣመር ሲሆን፥ ይህ ዘዴ ግብዓቶቹ ከግንባታው ስፍራ ውጪ እንዲዘጋጁ እና በኋላ እንዲጓጓዙ ብሎም በደረጃ እንዲጫኑ ያስቻለ እንደሆነ እና የመጨረሻው የግድግዳው ንጣፍ የ 142.5 ሜትር ርዝማኔ በመያዝ ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም. መጠናቀቁ ተነግሯል።

በማማው ክፍል ስር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያወድሱ ጽሑፎች ያሉ ሲሆን፥ እነዚህ ጽሁፎች “ቱ ሶለስ ሳንክተስ፣ ቱ ሶለስ ዶሚነስ እና ቱ ሶለስ አልቲሲመስ” ወይም በአማሪኛው አቻ ትርጉም “አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ፣ አንተ ብቻ ጌታ ነህ፣ አንተ ብቻ ልዑል ነህ” የሚሉ በሚያብረቀርቅ ነጭ ሴራሚክ እና ጡብ ላይ የተፃፉ እና በዘንባባ ቅርጽ በተሰሩ ጌጦች የተከበቡ ናቸው።

ይህ የማማው ክፍል 29 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን ግንባታው የተጀመረው ግንቦት 2017 ዓ.ም. ነው። ግንቡ ባለ አራት ማዕዘን እና ባለ ባለ ሶስት አቅጣጫ ያለው የመስቀል አክሊል የተደፋበት ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በመስታወት እና በነጭ በሚያብረቀርቅ ሴራሚክ ተሸፍኗል። መስቀሉ 17 ሜትር ቁመት እና 13.5 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፥ የመጀመርያው ክፍል የታችኛው ክንድ የተገጠመለት ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሆነ እና ቁመቱ 162.91 ሜትር እንደሚደርስ ተገልጿል።

መስቀሉን የመገጣጠም ሥራ
የመስቀሉ ሥራ የተጀመረው ባለፈው ዓመት በጀርመን ሃገር ሲሆን፥ ከዚያም ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የሳግራዳ ፋሚሊያ ባዝሊካ እየተሰራበት በሚገኝበት ስፍራ የደረሰ ሲሆን፥ ነጭ የሚያብረቀርቅ ሴራሚክ፣ የውስጠኛው የድንጋይ መዋቅር እና ባለቀለም መስታወቱ በመላ ካታሎኒያ በሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎች እና ዎርክሾፖች መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

የጋውዲ መቶኛ ዓመት
ይህ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሃውልት መጠናቀቅ ከአንቶኒ ጋውዲ ሞት መቶኛ ዓመት ጋር መገጣጠሙ የተነገረ ሲሆን፥ የሳግራዳ ፋሚሊያ ታሪካዊ መሰረት እና አርክቴክት የሆነው ስፔናዊው አንቶኒ ጋውዲ የካታላዊያን አርክቴክት እና ዲዛይነር ሲሆን፥ በስፋት የካታላዊያን ዘመናዊነት አባት በመባል ይታወቃል።

የግንባታው ዋና አርክቴክት ጆርዲ ፋውሊ እንደተናገሩት “የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሃውልት መጠናቀቁ የግንባታው ምዕራፍ ከመጠናቀቁ የበለጠ ነገርን የሚያመለክት እንደሆነ እና የአንቶኒ ጋውዲ የዓመታት ሥራና ጥናት ውጤት መሆኑን አመላክተዋል።

23 Feb 2026, 15:10