ኢየሱስ በበረሃ ኢየሱስ በበረሃ  

የጥር 22/2018 ዓ.ም የመጀመርያው የዐብይ ጾም ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.    ዘፍጥረት 2፡7-9፣3፡1-7

2.    መዝሙር 50

3.    ሮም 5፡12-19

4.    ማቴዎስ 4፡1-11

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የኢየሱስ ክርስቶስ መፈተን

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በዲያብሎስ እንዲፈተን መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። ፈታኙ መጥቶ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። እርሱ ግን “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ በመቅደሱ ጫፍ ላይ አቆመውና “‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል’ ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ራስህን ወደ ታች ወርውር” አለው። ኢየሱስም “‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። እንደገና ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየውና፥ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “ሂድ አንተ ሰይጣን ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው። ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ተወው፤ እነሆ መላእክት መጥተው አገለገሉት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን ከረማችሁ!

የዚህ የዐብይ ጾም ሳምንት የመጀመሪያ እለተ ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ በዲያቢሎስ በምድረ በዳ እንደ ተፈተነ የሚገልጸውን ታሪክ አቀረብልን (ማቴ. 4፡1-11)። “ዲያብሎስ” ማለት “ከፋፋይ” ማለት ነው። ስሙ የሚያደርገውን ይነግረናል፡ ይከፋፍላል። ኢየሱስን ለመፈተን ሲያደርገው በነበረው ጥረት እቅዱን ይፋ አድርጎታል። እንግዲያው ከማን ሊከፋፍለው እንደሚፈልግ እና እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ዲያብሎስ ኢየሱስን የሚከፋፍለው ከማን ነው? ከመፈተኑ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ጥምቀትን ከዮሐንስ ሲቀበል፣ ኢየሱስ በአብ “የምወደው ልጄ” ተብሎ ተጠርቷል (ማቴ 3፡17)፣ እና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በእርሱ ላይ ወረደ (ማቴ 3፡16) ስለዚህ ቅዱስ ወንጌል በፍቅር የተቀላቀሉትን ሦስቱን መለኮታዊ አካላት አቅርቦልናል። ይህ ብቻ አይደለም፡ ኢየሱስ ራሱ ወደ ዓለም የመጣው በእርሱና በአብ መካከል ባለው አንድነት እንድንካፈል ሊያደርገን እንደሆነ ይናገራል (ዮሐ. 17፡11)። ዲያቢሎስ ይልቁንም ተቃራኒውን ያደርጋል፡ ወደ ስፍራው የገባው ኢየሱስን ከአብ ለመከፋፈል እና እኛን አንድ ለማድረግ ካለው ተልእኮ ለማዘናጋት ነው።

አሁን እንዴት ለማድረግ እንደሚሞክር እንመልከት። ዲያብሎስ አርባ ቀን እንደ ጾመ እና እንደተራበ ደካማ የሆነውን የኢየሱስን የሰው ልጅ ሁኔታ ለመጠቀም ይፈልጋል (ማቴ. 4፡2)። ከዚያም ይህ ክፉ መንፈስ የአንድነት ተልእኮውን ሽባ ለማድረግ ሦስት ኃይለኛ "መርዞችን" በእሱ ውስጥ ለመትከል ይሞክራል። እነዚህ መርዞች ማበር ወይም ግንኙነት፣ አለመተማመን እና ስልጣን የተሰኙት ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ከቁሳዊ እቃዎች፣ ከፍላጎቶች ጋር የተያያዘ መርዝ፥ በሚያባብል ክርክር ዲያብሎስ ኢየሱስን ለማሳመን ሞከረ፡- “ተርበሃል፣ ስለ ምን ትጾማለህ? ፍላጎትህን አዳምጠህ አሟላው፤ መብትና ኃይል አለህ፤ ድንጋዮቹን ወደ ዳቦ ቀይር። ከዚያም ሁለተኛው መርዝ፣ አለመተማመን፡ “አብ የሚጠቅምህን ነገር ብቻ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ነህ? እሱን ፈትነው፣ አስጨንቀው! ራስህን ከቤተ መቅደሱ ከፍተኛ ቦታ ወርውረህ የምትፈልገውን ነገር እንዲያደርግልህ አድርግ። በመጨረሻም ሥልጣን የሚለውን መርዝ እናገኛለን፡- “አባታችሁ በፍጹም አያስፈልጋችሁም! ለምን የእርሱን ስጦታዎች ትጠብቃላችሁ? የዓለምን መመዘኛዎች ተከተል፣ ሁሉንም ነገር ለራስህ ውሰድ፣ እናም ኃይለኛ ትሆናለህ! " ይህ ጉዳይ አስፈሪ አይደለም? ነገር ግን ለኛም እንደዛ ነው፡ ከቁሳዊ ነገሮች ጋር መጣበቅ፣ አለመተማመን እና የስልጣን ጥማት ዲያቢሎስ ከአብ ለመለያየት የሚጠቀምባቸው ሶስት የተስፋፉ እና አደገኛ ፈተናዎች ናቸው። በመካከላችን ያሉ እህቶች እና ወንድሞች ለእኛ እንደ ማይጠቅሙን እና እኛም ብቻችን እንደ ሆንን እንዲሰማን በማድረግ ወደ ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሊከተን ይፈልጋል። ይህን በኢየሱስ ላይ ሊያደርግ ፈልጎ ነበር ዛሬም በእኛ ላይ የሚነዛው መርዝ ነው፣ ሊያደርግም ይፈልጋል።

ኢየሱስ ግን ፈተናዎችን አሸንፏል። እንዴት? ከዲያብሎስ ጋር መወያየትን በማስወገድ እና በእግዚአብሔር ቃል መልስ በመስጠት። ከቅዱሳት መጻሕፍት ሦስት ሐረጎችን ጠቅሷል፣ ከቁሳቁሶች ነፃ ስለመሆን (ዘዳ 8:3)፣ መታመን (ዘዳ 6:16)፣ እና ለእግዚአብሔር አገልግሎት መስጠት (ዘዳ. 6:13)፣ የሚቃረኑ ሦስት ሐረጎች ወደ ፈተና ውስጥ ሊከቱን ይችሉ ይሆናል። እርሱ ከዲያብሎስ ጋር አይወያይም፥ ከዲያብሎስ ጋር አትከራከርም! ከእርሱ ጋር በመደራደር አሸናፊ መሆን የምትችል ሳይሆን በመለኮታዊ ቃል በእምነት በመቃወም አሸናፊ ያደርጋሃል። በዚህ መንገድ፣ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር እና በመካከላችን ያለውን አንድነት ከከፋፋዮች ጥቃት እንድንከላከል ያስተምረናል። እናም አንድነት ያስፈልገናል!

እናም፣ እራሳችንን እንጠይቅ፡ የእግዚአብሔር ቃል በህይወቴ ምን ቦታ አለው? በመንፈሳዊ ትግሌ ወደ እሱ እመለሳለሁ? መጥፎ ወይም ተደጋጋሚ ፈተና ካለብኝ፣ ለክፉ ነገር ምላሽ የሚሰጠውን የአምላክ ቃል ጥቅስ በመፈለግ ለምን እርዳታ አላገኘሁም? ከዚያም ፈተና ሲመጣ፣ አነባለሁ፣ እጸልያለሁ፣ በክርስቶስ ጸጋ አምኜ እኖራላሁ ወይ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። እንሞክር፣ በፈተናዎች ውስጥ ይረዳናል፣ ስለዚህም በውስጣችን በሚቀሰቅሱት ድምፆች መካከል፣ ቸር የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ይሰማል።

በሁለተኛ ደረጃ በዚህ የመጀመሪያው የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል (ማቴ. 4፡1-11) ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ “መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው” (ማቴ 4፡1) በማለት ይናገራል። እርሱ መንግሥተ ሰማያትን የማወጅ ተልእኮውን ለመጀመር ተዘጋጅቷል፣ እናም ልክ እንደ ሙሴ እና ኤልያስ (ዘጸሐት 24 ፣ 18 ፣ 1 ነገስት 19፡8) ለአርባ ቀናት ጾመ።

በዚህ የአርባ ቀን ጾም ማብቂያ ላይ ፈታኙ ዲያቢሎስ ኢየሱስን ችግር ውስጥ ለመክተት ሦስት ጊዜ ፈተነው። የመጀመሪያ ሙከራው ኢየሱስ የተራበ መሆኑን በማሰብ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” (ማቴ 4፡3) በማለት ሐሳብ ያቀርባል። ነገር ግን የኢየሱስ መልስ ግልፅ ነበረ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” (ማቴ 4፡ 4) በማለት ይመልሳል። እርሱም በምደረ በዳ ውስጥ በተደርገው ረጂም ጉዞ ውስጥ ሕዝቡን በመራበት ወቅት ሕይወቱ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ መሆኑን የተማረውና ሙሴን ያስታውሳል (ኦ. ዘዳግም 8፡3)።

በሁለተኛው ሙከራ (ማቴ. 4፡5-6) ዲያቢሎስ የበለጠ ብልህ ሆኗል፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንም መጥቀስ ይጀምራል። እየተከተለ የሚገኘው ዘዴ ግልፅ ነው - በእግዚአብሔር ኃይል ላይ እጅግ በጣም የምትተማመን ከሆነ እንግዲህ ይህንን መተማመን አሳየኝ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንክ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና” (ማቴ 4፡6) በማለት ይጠይቀዋል።   ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ እንኳን ኢየሱስ እራሱን ግራ ሊያጋባ አላሰበም፣ ምክንያቱም አንድ አማኝ የሆነ ሰው እግዚአብሔር እንደማይፈትነው ያውቃል፣ በእርሱ መልካም ፈቃድ ይተማማናል። ስለዚህ ሰይጣን እንደመሳሪያ በመጠቀም በማጣቀሻነት በመጥቀስ በተረጎመው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ኢየሱስ ሌላ ጥቅስ ተጠቅሞ መላሽ ይሰጣል “ጌታ አምላክህን አትፈታተነውም ተብሎ ተጽፉዋል” (ማቴ 4፡7) በማለት ይመልሳል።

በመጨረሻም ሦስተኛው ሙከራ (ቁ. 8 እስከ 9) የዲያቢሎስን እውነተኛ አስተሳሰብ ያሳያል፣ የእግዚአብሔር መንግሥት መምጣት በእርሱ ላይ ድል የመቀናጃ ጅማሬ ስለሆነ ይህ ክፉ መንፈስ  የኢየሱስን ተልእኮ ከመፈፀሙ በፊ መሲሁ ፖሌቲካዊ ተልዕኮ እንዲኖረው ለማደረግ በማሰብ የእርሱን ተልዕኮ አቅጣጫ ለማስቀየር ይፈልጋል። ነገር ግን ኢየሱስ እንደ ጣዖት የሆነውን ምድራዊ ስልጣን እና ሰብዓዊ ክብር አምላኪነትን አልቀበልም በማለት በመጨረሻም ስይጣንን “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” (ማቴ 4፡10) አለው። እናም በዚህ ነጥብ ኢየሱስ ለእግዚኣብሔር አባቱ ያለውን ታማኝነት ከገለጸ በኋላ መላእክት እሱን ማገልገል ይጀምራሉ (ማቴ 4፡11)።

ዛሬም ቢሆን ሰይጣን የሰዎችን ሐሳቦች ለመፈተን በሰዎች ሕይወት ውስጥ ገብቷል፣ ሕሊናን ብቻ ለማርካት ከሚሞክሩ ብዙ ድምጾች ጋር ተቀላቅሉዋል። ከብዙ ማዕዘኖች የሚመጡ ለሕይወታችን ደስታን የሚሰጡ የሚመስሉ መልእክቶች እና ፈትናዎች ይመጣሉ። ራስን መቻል እንዳለብን፣ የህይወት እርካታን፣ ለራሳችን የህይወትን ደስታ የሚሰጡን ከእግዚአብሔር ይልቅ ብዙ አማራጭ መንገዶችን እንድንመለከት የሚያደርግ ሙከራ መሆኑን የኢየሱስ ተሞክሮ ያስተምረናል። ነገር ግን ይህ ሁሉ ቅዤት ነው፣ ዲያቢሎስ በሚያሳየን መንገድ የምንጓዝ ከሆነ ከእግዚኣብሔር እንርቃለን፣ ከእግዚኣብሔር እየራቅን በምንሄድበት ወቅት ደግሞ ወዲያውኑ የሚጠብቀን የሚከላከልልን ማንም እንደሌለ እንገነዘባለን፣ ታላላቅ የሆኑ ፈተናዎች እና ችግሮች በሚገጥሙን ቁጥር ለመቋቋም እንቸገራለን፣ ከእዚያም አቅመ ቢስ እንደሆንን እንረዳለን።

የእባቡን ጭንቅላት የቀጠቀጠችሁ እመቤታችን ድንግል ማርያም በዚህ በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት ፈትና በሚገጥመን ወቅት ጠንቃቃ እንድንሆን፣ ለዚህ ዓለም ጣዖት እንዳንገዛ፣ ከክፉ መንፈስ ጋር የሚደርገውን ውጊያ ማሽነፍ እንችል ዘንድ ኢየሱስን እንድንከተለው፣ እኛም እንደ እርሱ አሸናፊዎች ሁነን መውጣት እንችል ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብላ በትህትናዋ የከፋፍለህ ግዛውን ትምክህት ያሸነፈች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዐቢይ ጾም መንፈሳዊ ተጋድሎ ማድረግ እንችል ዘንድ በአማላጅነቷ ትርዳን።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት)- ቫቲካን

 

 

28 Feb 2026, 14:07