ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጉት ጉብኝት “ከእግዚአብሔር የተላከ ጸጋ ነው” ተባለ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአፍሪካ ጉብኝታቸው መደምደሚያ በኢኳቶሪያል ጊኒ ከሚያዝያ 13 እስከ ሚያዝያ 15/2018 ዓ. ም. ድረስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር ሁለት ሳምንታት በቀሩበት በዚህ ጊዜ የአገሪቱ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ዝግጅቷን በሁለት አቅጣጫዎች እያጠናከረች እንደምትገኝ ታውቋል። እነርሱም የክህነት አገልግሎትን ማደስ እና የእግዚአብሔርን ሕዝብ እምነት እንደገና ማነሳሳት መሆኑ ተነግሯል።
የጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የሞንጎሞ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በሆኑት አቡነ ሁዋን ዶሚንጎ-ቤካ ኤሶኖ አያንግ የተፈረመው የብጹዓን ጳጳሳቱ መልዕክት ማዕከላዊ ግብዣ፥ “የሕይወታችንን እና የክህነት አገልግሎታችንን መሠረት ማጠናከር እና ማደስ” የሚል ሲሆን፥ ለክህነት ጥሪ እጅግ የላቀ ስጦታ ቤተ ክርስቲያኗ እግዚአብሔርን በማመስገን፥ ይህም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የፍቅር ምስጢር እንደሆነ የተረዳች መሆኗን ገልጸዋል።
የጉባኤው መልዕክት፥ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ኅብረት መመለስ እንደሆነ ምዕመናንን የሚያሳስብ፥ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ተግባር በግልጽ ለማሳየት በተጠራው በካኅን ማንነት ላይ አፅንዖት የሰጠ እንደሆነ ተመልክቷል።
በዚህም መሠረት ብጹዓን ጳጳሳቱ የውስጥ ሕይወትን መንከባከብ እንደሚገባ አጥብቀው በማሳሰብ፥ “ጸሎት እና መንፈሳዊነት ለሚታመን የክኅነት ሕይወት ዋና ምሰሶዎች ናቸው” ስሉ ገልጸዋል። ከእግዚአብሔር ጋር ዕለታዊ ግንኙነት ከሌለ የእረኝነት ተግባር ኃይሉን እንደሚያጣ አስረድተው፥ፈተናዎችን በመቋቋም እያንዳንዱ ሐዋርያዊ ተግባር ከጥልቅ ውስጣዊ ሕይወት የሚመነጭ መሆን እንዳለበት፥ “ይህንን ሃብት “በሸክላ ዕቃ” ለመያዝ የሚያስችል ኃይል ከእግዚአብሔር እንደሚመጣ ግልጽ ይሆናል” ብለዋል።
እንደዚሁም መልዕክቱ የካህናት ወንድማማችነት ተሞክሮ ለካህናቱ መንፈሳዊ ደህንነት መሠረታዊ ቢሆንም ያልተቋጨ ተግባር መሆኑን በመግለጽ በዚህ ረገድ እግዚአብሔር በጸጥታ ውስጥ የሚናገር በመሆኑ ወደ እግዚአብሔርም ሆነ ወደ ሰዎች ዘንድ መቅረብ እና ዝምታን የማዳበር አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ እንደ ሆነ ተመልክቷል።
ለመላው ሕዝብ “የጸጋ ጊዜ” ነው
ይህ ለካህናት የቀረበው እና በየካቲት ወር በብጹዓን ጳጳሳት የተፈረመው የማበረታቻ መልዕክት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የኢኳቶሪያል ጊኒ ብርሃን እና የወደፊት ተስፋ” በሚል መሪ ቃል በኩል ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ የላኩት ሰፊ መልዕክት አካል ነው።
መጪው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ታሪካዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን የአንድን ሰው ታሪክ እንደገና ለመመርመር፣ እምነትን ለማደስ እና ተስፋ በማድረግ ለወደፊቱ ራስን ለመክፈት የሚያግዝ እውነተኛ እና አስፈላጊ የጸጋ ጊዜ እንደሚሆን ተገልጿል። በዚህም መሠረት ካኅናት የክርስትናን ሕይወት ትርጉም እና ሕይወትን የሚመራ እና የሚለውጥ ብርሃንን እንደገና እንዲያገኙ እንዲሁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት እንዲኖራቸው ምእመናን ጋብዘዋል።
ቅዱስ ወንጌልን በመጥቀስ “የዓለም ብርሃን ለመሆን ተጠርተናል” ያለው የጉባኤው መልዕክት፥ እምነታችንን መናገር ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ነገር ግን በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በተጨባጭ የፍትህ፣ የአገልግሎት እና የበጎ አድራጎት ሥራ ፈጻሚዎች መሆን እንደሚገባ አሳስቧል።
እምነትን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1982 ዓ. ም. በኢኳቶሪያል ጊኒ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት ያስታወሱት ጳጳሳቱ፥ ይህም አገሪቱ ከዓመታት ቀውስ እንድታገግም የረዳት ተአምራዊ ጉብኝት እንደ ነበር ገልጸው፥ ሆኖም ከአሥርተ ዓመታት በኋላ እምነቱ አዳዲስ ተግዳሮቶች እንዳጋጠመው አስረድተዋል።
የመዳከም ምልክት የታየበትን የክርስትና ሕይወት ተሞክሮ ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ ይህም “የቅድስና ስሜት ማጣት፣ የቅዱሳት ምስጢራት ልምምድ መቀነስ፣ በሃይማኖቶች መካከል ልዩነቶች እና በመሠረታዊ ትርጓሜዎች ምክንያት የሚፈጠር መከፋፈልን ያሳያል” ብለዋል።
እንዲሁም እምነትን ከወላጆች ወደ ልጆች የማስተላለፍ ልማድ በመቋረጡ፥ በቁምስና ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ማኅበራት አለመበርታት እና ወጣቶችን በመልካም ሥነ-ምግባር፣ በገንቢ ሃሳቦች እና ጥሩ ምኞቶች በማነጽ አርአያ የሚሆኑ የማኅበራዊ ተቋማት አለመኖር በማስታወስ፥ እንደ ሙስና፣ የቤተሰብ ሕይወት መዳከም እና ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቁ የሚያደርጉ የተወሳሰቡ ማኅበራዊ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
“እነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ ከአሉታዊነት ባሻገር በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሃድሶን ለማካሄድ ዕድል እንደሚሰጡ ተደርገው እንዲወሰዱ፥ ዛፍ የደረቀ ቢመስል ነገር ግን ሥሩን በማርዘም እንደገና እንደሚለመልም ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም አዲስ ፍሬን ለማፍራት እምነቷን እንድታጠናክር ተጠርታለች” ብለዋል።
መለወጥ፣ እርቅ እና ተስፋ
በዚህ መሠረት ብጹዓን ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው፥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት ግልጽ የሆነ የዝግጅት መንገድ በማቅረብ፥ ከፍተኛ ጸሎት እና ከልብ የመነጨ ለውጥ እና የጋራ እርቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፥ “ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከልንን ጸጋ የምንቀበልበት እና በአገሪቱ ዜጎች መካከል ጤናማ ግንኙነቶችን እንደገና ለመገንባት ዕድል የሚሰጠን ነው” ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ መሠረታዊው ጥያቄ ቀጥተኛ እና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚፈታተን እንደሆነ በመግለጽ፥ “ከቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ ግንኙነታችን የተሻለ ይሆናል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የሐዋርያዊ እረኝነት ትርጉም ያለው ጉብኝት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚያደርጉት የሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር እንደገለጸው፥ ማክሰኞ ሚያዝያ 13/2018 ዓ. ም. ጠዋት ወደ ቀድሞዋ የኢኳቶሪያል ጊኒ ዋና ከተማ ማላቦ እንደሚደርሱ በዚያም “ትምህርት ለሰብዓዊ ክብር የተስፋ መንገድ ነው” በሚለው ሃሳብ ላይ በማትኮር ንግግር ያደርጋሉ።
ቀጥለውም በአገሪቱ ምሥራቃዊ ድንበር ላይ ወዳለች የሞንጎሞ ከተማ በመጓዝ እዚያ በምትገኝ የወደብ ከተማ መስዋዕተ ቅዳሴን ያቀርባሉ። በባታ ስታዲየም ከወጣቶች እና ከቤተሰቦች ጋር ተገናኝተው ንግግር የሚያደርጉ መሆኑን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ “ለዝግጅቱ ስኬታማነት ሲባል ቁምስናዎች በሙሉ በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ፣ ምዕመናን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ትርጉም እንዲረዱ በመርዳት የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን እንዲተባበሩ” ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም በኢኳቶሪያል ጊኒ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪን ለመቀበል ስትዘጋጅ በተለይም በችግረኞች መካከል የክርስትናን ሕይወት ለማደስ፣ የወንጌል ተልዕኮን ለማጠናከር እና ተስፋን ለማቀጣጠል ዕድል እንደሚሆናት ተነግሯል።
“ዓይኖቻቸውን የዓለም ብርሃን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማተኮር፥ አገሪቱ በእግዚአብሔር በማመን እና ኅብረተሰቡም ከልብ ለመለወጥ የሚያስችል ሕያው እምነትን እንደገና እንዲያገኝ” በማለት የኢኳቶሪያል ጊኒ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ግብዣቸውን አቅርበዋል።