በጋና የተካሄደው ብሔራዊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጽህፈት ቤት አውደ ጥናት በጋና የተካሄደው ብሔራዊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጽህፈት ቤት አውደ ጥናት 

በጋና የምትገኘው ቤተክርስቲያን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን የመጀመሪያ ሃዋሪያዊ መልዕክት በጉጉት እንደምትጠብቅ ገለጸች

በጋና የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለቴክኖሎጂ እድገት የምትሰጠውን ምላሽ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቀጣይ መመሪያ ጋር ለማስማማት በማለም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስራ አራተኛ የመጀመሪያ ሃዋሪያዊ መልዕክታቸው የሆነው “ማግኒፊካ ሂዩማኒታስ” (Magnifica Humanitas) መለቀቅ በንቃት እየጠበቀች እንደሆነ የገለጸች ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያኒቷ ይሄንን የገለጸችው እያደጉ የመጡት ቴክኖሎጂዎች በሥነ ምግባር እና በሃዋሪያዊ አገልግሎት ውስጥ ያላቸው ሚና ላይ ያተኮረ ቁልፍ የሀይማኖት አባቶች የተሳተፉበት የከፍተኛ ደረጃ አውደ ጥናት ላይ ሲሆን፥ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሃዋሪያዊ መልዕክት ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በቫቲካን እንደሚለቀቅ ጭምር ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአክራ በሚገኘው የብሔራዊ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት ውስጥ የተካሄደው ይህ ስትራቴጂካዊ አውደ ጥናት የሀገረ ስብከቶች የግንኙነት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተሮችን እና በጋና ውስጥ የሚገኙ ኃይማኖታዊ የበላይ መሪዎች ጉባኤ አባላትን ጨምሮ ሃምሳ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን አንድ ላይ ያሰባሰበ ሲሆን፥ አውደ ጥናቱ የተካሄደው በቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ጽህፈት ቤት ይሁንታ እና አስተባባሪነት እንደሆነ ተገልፆ፥ ይህም ቤተክርስቲያኒቷ በዓለም አቀፉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሥነ ምግባራዊ አንድምታ ላይ ያላትን ስጋት የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ሥነ-ምግባር፣ ትምህርት እና መብቶች
የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ቤተ ክርስቲያን ከቴክኖሎጂ ጋር ያላት ትስስርን ከእጅ አዙር አጠቃቀም ወደ ንቁ የሥነ ምግባር አስተዳደር መቀየር የሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፥ ከዚህም ባሻገር አውደ ጥናቱ በመርሃግብሮቹ ላይ የሰውን ልጅ ክብር በሚያስጠብቅ መልኩ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለማዳበር እና አጠቃቀሙን ለመምራት እ.አ.አ. በ 2020 ዓ.ም. በቫቲካን ድጋፍ የወጣውን የሥነ ምግባር ማዕቀፍ ማክበር እንደሚገባ ጥሪ ተላልፏል።

‘የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥነ ምግባር ለሰብዓዊ ልማት’ የሚል ተነሳሽነት አስተባባሪ የሆኑት ማሪያ አምፓሮ አሎንሶ እና ሉካ ባራልዲ በሥነ ምግባር፣ በትምህርት እና በመብት ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን የመሩ ሲሆን፥ በአውደ ጥናቱ ላይ የቴክኖሎጂ ምጥቀት የሰውን ልጅን ማገልገል ያለበት እንጂ የሰውን አስተሳሰብ፣ ህሊና እና ክብር የሚጎዳ መሆን እንደማይገባው ተመላክቷል።

ሰፋ ያለ ዓለም አቀፋዊ አለመመጣጠንን መፍታት
ከዚህም በተጨማሪ በጋና በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን በመቅረጽ ረገድ በስፋት የሚታየው ዓለም አቀፋዊው ኢፍትሃዊነት ያለውን አሉታዊ ሚና ያመላከተ ሲሆን፥ ጋና የብሔራዊ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂን እየመራች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፥ አፍሪካ በአጠቃላይ የዲጂታል መረጃን ለማከማቸት እና ለማስኬድ ከሚያስችለው ከዓለም አቀፍ የመረጃ ማዕከል አቅም ከአንድ በመቶ በታች እንደምትሸፍን፥ ይህም በውጫዊ ሥርዓቶች ላይ ጥገኛ መሆን እና የአካባቢያዊ አመለካከቶች መገለል ላይ ስጋት እንደሚፈጥር ተገልጿል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘውን አደገኛ የኮባልት ማዕድን የማውጣት ሂደት እና ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ባሉ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን የስነ ልቦና ጫና ጨምሮ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር የተገናኙትን የሰብዓዊ እና የአካባቢ ጉዳቶችን በተመለከተ ተሳታፊዎቹ የተወያዩ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ በትላልቅ የኮምፒዩተር ሥርዓቶች ከፍተኛ የውሃ ፍላጎት ላይ ያሉ የአካባቢያዊ ስጋቶችም ተነስተዋል።

ቤተክርስቲያን እና ሃሰተኛ ዲጂታል መሳሪያዎች
የፋይናንሺያል ግብይቶችን ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ የውሸት ቪዲዮዎች፣ የድምጽ ማስመሰል እና የማጭበርበሪያ ዲጂታል መሳሪያዎች ጨምሮ በቤተክርስቲያኒቱ ተቋማት ላይ እየተጋረጡ ስላሉት ስጋቶች ትኩረት የተሰጠ ሲሆን፥ በምላሹም አውደ ጥናቱ ‘አስቸኳይነት’ ‘ማረጋገጫን’ በፍፁም መሻር እንደሌለበት መመሪያ በማውጣት እምነትን እና ተጠያቂነትን የመጠበቅን አስፈላጊነት አመልክቷል።

አውደ ጥናቱ በመጨረሻ በጋና በሚገኙ ሃገረ ስብከቶች ውስጥ የዲጂታል መሳሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመመሪያ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ማዕቀፉ ከሃዋሪያዊ አገልግሎት እሴቶች ጋር መጣጣምን፣ የግል መረጃዎችን መጠበቅ እና በሁሉም የሰው ሰራሽ አስተውሎት በሚታገዙ ሂደቶች ውስጥ የሰዎች ቁጥጥር እንዲኖር ማድረግን እንደሚጠይቅ ተገልጿል።

25 May 2026, 14:33