አንድ ሊባኖሳዊ በዴርድጋያ በሚገኘው የመልካይት ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ ውስጥ የገና ዛፍ ሲያቆም - 2016 ዓ.ም. አንድ ሊባኖሳዊ በዴርድጋያ በሚገኘው የመልካይት ቤተክርስቲያን ፍርስራሽ ውስጥ የገና ዛፍ ሲያቆም - 2016 ዓ.ም.   (AFP or licensors)

በደቡብ ሊባኖስ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑ ተገለጸ

በዚህ ሳምንት የምስራቃዊ አብያተ ክርስቲያናትን የሚመለከቱ ዜናዎች መካከል ከሎቭር ዲ ኦሪየንት ጋር በመተባበር የወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው በደቡባዊ ሊባኖስ በሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሊባኖስ ባለፈው አርብ የሳልቫቶሪያን እህቶች የቀድሞ ትምህርት ቤት እና ገዳም የእስራኤል ጦር ባደረሰው ጥቃት መውደማቸው የተገለጸ ሲሆን፥ ይህ የመጀመሪያ ጥቃት እንዳልሆነ እና በ 2016 ዓ.ም. የሊባኖስ ባህላዊ ቅርስ ተብለው የተመዘገቡ በያሩን እና በዴርድጋያ ከተሞች የሚገኙ የመልካይት አብያተ ክርስቲያናት እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት መውደማቸው ተገልጿል።

በሂዝቦላህ እና በእስራኤል ጦር መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያት ቃውዛህ እና አልማኤል ቻብን ጨምሮ አንዳንድ የክርስቲያን መንደሮች ነዋሪዎቻቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተፈናቅለው መውጣታቸው የተነገረ ሲሆን፥ በርካታ ሊባኖሳዊያን እንደሚስማሙት ይህ ድርጊት ሲቪሎች ወደ ቄያቸው እንዳይመለሱ ታቅዶ የተደረገ ጥቃት እንደሆነ ተነግሯል።

በሊባኖስ የሚገኘው የመልካይት ግሪክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት ምክር ቤት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ “አብያተ ክርስቲያናት፣ ትምህርት ቤቶች እና መኖሪያ ቤቶች የድንጋይ ድርድሮች ብቻ ሳይሆኑ እነዚህን ቦታዎች ማጥቃት የሰውን ልጅ ክብር ማጥቃት” ጭምር እንደሆነ በመግለጽ ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

ምክር ቤቱ የሊባኖስ መንግስት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እነዚህ መንደሮች ሙሉ በሙሉ በዝምታ እንዲጠፉ ከመፍቀዳቸው በፊት ሰላማዊ ዜጎችን፣ ንብረቶቻቸውን እና የእምነት ተቋሞቻቸውን እንዲከላከሉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

12 May 2026, 15:37