አንድ የናይጄሪያ ጳጳስ ር.ሊ.ጳ. ሊዮ ዲጂታል ሚዲያን በኃላፊነት መጠቀም እንደሚገባ ያቀረቡትን ጥሪ ማስተጋባታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የናይጄሪያው ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኢማኑኤል ባደረጉት ንግግር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለ60ኛው የዓለም የማህበራዊ ግንኙነት ቀን ባስተላለፉት መልዕክት ላይ በማተኮር እንደገለጹት “ለሰው ልጅ ድምጽ እና ፊት ጥበቃ ማድረግ” የሚለው መሪ ቃል ዓለም ሊሰማው የሚገባ ወቅታዊ ማሳሰቢያ እንደሆነ ጠቅሰው፥ በወቅታዊው የማህበራዊ ተግባቦት ግንኙነቶች ውስጥ የሰው ፊት እና ድምጽ ሚና እየቀነሰ መምጣቱን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ እና በዚህ ጉዳይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያላቸውን ስጋት አመላክተዋል።
ግንኙነት ኅብረትን ማሳደግ አለበት
“ትክክለኛው የሐሳብ ልውውጥ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር ያለንን መግባባት ማሳደግ አለበት” ያሉት የተግባቦት እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ኢማኑኤል፥ መጥፎ የሐሳብ ልውውጥ ፍጹም ተቃራኒ እንደሆነ፥ ይህም መለያየትን፣ ውጥረትን እና ግጭትን እንደሚፈጥር በአጽንዖት ተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ ኢማኑኤል እንደተናገሩት ኮሙኒኬሽን ወይም ተግባቦት ግጭቶችን በሚፈጠሩበት ጊዜ እንኳን የሰው ልጆችን ማግለል ወይም ከግንኙነት ውጪ ማድረግ እንደማይገባ ገልጸው፥ በሌላ አነጋገር ተግባቦት ሌሎችን በፍፁም ማራቅ የለበትም ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ብፁዕነታቸው የዓለም የተግባቦት ቀን መልዕክት እምነትን፣ ሰብዓዊነትን እና ዲጂታል መገኘትን በዕለት ተዕለት ግንኙነታችን ውስጥ ሚዛናዊ ለማድረግ እንድንችል ለመርዳት ያለመ መሁኑን ጠቅሰዋል።
ሁሉንም ዲጂታል ሚዲያዎች ከማጣጣል መቆጠብ
ብፁዕ አቡነ ኢማኑኤል በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆን እንደማይገባ እና “ከልብ ያልሆነ” ብለው በጠሩት ተግባቦት መራቅ እንደሚገባ አስጠንቅቀው፥ በቴክኖሎጂ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆን ቤተሰብን፣ ጓደኝነትን እና የጋራ ግንኙነቶችን ሊጎዳ ይችላል ብለዋል።
ሆኖም ግን ብፁዕ አቡነ ኢማኑኤል እንደገለጹት ዲጂታል ሚዲያን ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ከልክ በላይ ዋጋ ማሳጣት እንደማይገባ አስጠንቅቀው፥ ይልቁንም ‘ኃላፊነት በተሞላበት እና የሚዲያ እውቀትን በሚጠይቅ ሁኔታ’ መጠቀም እንደሚገባ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ “በህብረተሰባችን ውስጥ ለሰዎች ድምጽ እና ፊት ጥበቃ በማድረግ ብቻ በዓለማችን ውስጥ በብዙ መልኩ የጠፋውን ሰብአዊነትን ዳግመኛ ማረጋገጥ እንችላለን” በማለት አጠቃለዋል።