የደቡብ አፍሪካ ካቶሊካዊ ጳጳሳት በስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት አወገዙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የጉባኤው ፕሬዚደንት በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል እስጢፋኖስ ብሪስሊን ረቡዕ ግንቦት 12/2018 በፈረሙት ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ “በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የተቀሰቀሰው ዓመፅ፣ የሚደርስባቸው ማስፈራሪያ እና መፈናቀል በሰብዓዊ ክብር ላይ የሚፈጸም ከባድ ጥቃት ማኅበረሰባችንን ሊገልጹት በሚገቡ እሴቶች ላይ የተደረገ ክህደት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
የተቀሰቀሰው ዓመፅ እና ማስፈራሪያ
ብጹዓን ጳጳሳቱ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ፥ “በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የሚፈጸሙትን የዓመፅ፣ የማስፈራራት እና የማፈናቀል ድርጊቶችን በማያጠራጥር እና በማያሻማ ሁኔታ እናወግዛቸዋለን” ሲሉ ጽፈው፥ “በስደተኞች ላይ የሚፈጸሙ የዓመፅ ተግባሮች ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖራቸው እና ሊታገሷቸው የማይችሏቸው ናቸው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የደቡብ አፍሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ የመጣው፥ በአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች በተለይም በኳዙሉ-ናታል እና በጋውቴንግ የተከሰቱት የጥቃት ድርጊቶች እና ስጋቶች እየጨመሩ በመጡበት ጊዜ ሲሆን፥ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ የፀረ-ስደተኞች ሰልፎችም ተጠናክረው መቀጠላቸው ተመልክቷል።
የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መበራከት
በመኖሪያ እና ሥራ አካባቢዎች የጥቃት ዛቻ የደረሰባቸው ሴቶች ሕፃናትን ጨምሮ ግንቦት 11/2018 ዓ. ም. በደርባን ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ከለላን የጠየቁ ሲሆን፥ አንዳንድ ስደተኞች ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት ከፖሊስ ጣቢያው ውጭ ሌሊቱን በብርድ አሳልፈዋል።
ብጹዓን ጳጳሳቱ አለመረጋጋቱ የተፈጠረው ሰፋ ባሉ ምክንያቶች እነርሱም ማኅበራዊ ሰቆቃ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና የአስተዳደር ድክመት እንደሆኑ በመልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል። ሐዋርያዊ መልዕክቱ በተጨማሪም ቀጣይነት ያለው ሥራ አጥነት፣ የኑሮ አለመመጣጠን፣ ደካማ የአገልግሎት አቅርቦት፣ ሙስና እና በኢሚግሬሽን አስተዳደር ውስጥ ያሉ ድክመቶች ለችግር ተጋላጭ በሆኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ ቁጣ እንዲቀሰቀሱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁሟል።
“ለአሁኑ ቀውስ ዋና ምክንያት በመንግሥት አስተዳደር፣ በተጠያቂነት እና በአመራር ላይ የታዩ ውድቀቶች መሆናቸውን እና የድሆች ጩኸት ለረጅም ጊዜ ተሰሚነት ሳያገኝ መቆየቱን በግልጽ መናገር እንፈልጋለን” ሲሉ ጳጳሳቱ ተናግረዋል።
ወሳኝ የሞራል እና የፖለቲካ ወቅት
ብጹዓን ጳጳሳቱ እንዲሁም ተገቢ ጥበቃ የማይደረግላቸው ድንበሮች፣ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የተፋፋ ሙስና፣ የስደተኞች ጉልበት ብዝበዛ፣ አንዳንድ ስደተኞችን ያካተቱ የወንጀል ተግባራት እና በተወሰኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ ትርጉም ያለው ውህደት አለመኖር ስጋቶችን እንደፈጠረ ገልጸዋል። ሆኖም ከእነዚህ እውነታዎች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ ዓመፅን ወይም የጋራ ቅጣትን ሊያጸድቁ እንደማይችሉ አጥብቀው ተናግረዋል።
ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው ላይ፥ “በአገሪቱ ውስጥ ስጋቶች እና ቁጣዎች መኖራቸው እውነት እና መፈታትም ያሉባቸው ቢሆኑም ነገር ግን በሌላ ሰው ላይ የሚፈጸም ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም” ሲሉ ተናግረው፥ ደቡብ አፍሪካን ወሳኝ የሞራል እና የፖለቲካ ጊዜ እንደሚገጥማት አስጠንቅቀዋል።
“ክልላዊ ምርጫ ሊካሄድ በተቃረበበት ወቅት ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሕዝብ ሥልጣን ፈላጊዎች በሙሉ ባቀረቡት ልዩ እና አስቸኳይ ጥሪ፥ ስደት ያስከተለውን ቀውስ ወይም የማኅበረሰቦችን ስቃይ ለፖለቲካ ጥቅም እንዳውሉት” ሲሉ ጳጳሳቱ አሳስበዋል።
“ለምርጫ ጥቅም ሲሉ ፍርሃትን፣ መከፋፈልን እና ተጋላጭነትን እንደ መሣሪያነት መጠቀም በሥነ ምግባር ረገድ ተቀባይነት የሌለው እና ቀድሞውኑ ደካማ የሆነውን ማኅበራዊ ሁኔታን የበለጠ ሊያበላሸው ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።
የእያንዳንዱ ሰው ክብር
ብጹዓን ጳጳሳቱ የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሐዋርያዊ አስተምህሮ በመጥቀስ፥ እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ ሊጠበቅ የሚገባው የማይደፈር ክብር አለው” የሚለውን የክርስትና እምነት አረጋግጠዋል።
“ክርስቲያኖች እንደመሆናችን እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረ መሆኑን ወደ መሠረታዊው እውነት እንመለሳለን” ሲሉ መልዕክት ያስተላለፉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ “በጥላቻ፣ በማጭበርበር ወይም በዓመፅ ሰላማዊ ማኅበረሰብን መገንባት አንችልም” ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት በመልዕክታቸው መደምደሚያ፥ ፍትህ፣ ሥነ-ምግባራዊ አመራር፣ አንድነት እና ማኅበራዊ ኃላፊነት እንዲኖር ጥሪ አቅርበው፥ “እነዚህ እሴቶች ከሌሉ ዘላቂ ሰላም ሊኖር አይችልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።