በቬንዙዌላ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከተከሰተ በኋላ በቬንዙዌላ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከተከሰተ በኋላ  (AFP or licensors)

የላ ጉዌራ ቁምስና ካህን ለቬንዙዌላ መጸለይን በፍጹም ማቆም እንደማይገባ አሳሰቡ

ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በቬንዙዌላ ላይ የደረሰው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን አስመልክቶ የቅድስት ልበ ማርያም ቁምስና ካህን የሆኑት አባ አንቶኒዮ ሬላ ምድሪቷ በሃዘን እና በጥርጣሬ መዋጧን ነገር ግን በአንድነት እና በህብረት መቆሟን ገልጸው፥ ቁምስናቸው በአደጋው እጅግ ለተጎዱ ማህበረሰቦች የእርዳታ አገልግሎት የሚሰጥበት ማዕከል በመሆን የቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ መልሶ ግንባታ ጊዜን፣ ጽናትንና ጸሎትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በአከባቢው የሚገኙ ቤተሰቦች አሁንም ድረስ በፈራረሱ ሕንፃዎች መካከል በአደጋው ምክንያት የጠፉ ወዳጆቻቸውን የመገኘት ዜና በጉጉት እየጠበቁ ባሉበት እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ የቀደመ ህይወታቸውን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት በላ ጉዌራ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ረቡዕ፣ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. ቬንዙዌላ ላይ በደረሰው አውዳሚ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች ጎን መቆሟን እንደቀጠለች ተነግሯል።

የቅድስት ልበ ማርያም ቁምስና ካህን የሆኑት አባ አንቶኒዮ ሬላ ሁኔታውን አስመልክተው እንደተናገሩት ጉዳቱ ወደደረሰባቸው በርካታ አካባቢዎች መድረስ ከባድ ስለሆነ እና የጥፋቱ መጠን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት አጠቃላይ የአደጋውን መጠን መረዳት አሁንም አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው “ውድመቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር” ያሉ ሲሆን፥ አንዳንድ ቦታዎች የጦርነት ቀጠናዎችን እንደሚመስሉ እና ሌሎች አከባቢዎች ደግሞ አጠቃላይ ሕንፃዎች ወደ ፍርስራሽነት በመቀየራቸው የምጽዓት ቀን ትዕይንቶችን መስለው ወደ አዕምሮአቸው እንደሚመጡ አስረድተዋል።

በተስፋ እና በሀዘን መካከል
ከመሬት መንቀጥቀጡ አስራ አምስት ቀናት በኋላ በርካታ ቤተሰቦች አሁንም ድረስ የጠፉ ዘመዶቻቸውን በሕይወት የማግኘት ተስፋቸውን አጥብቀው መያዛቸውን የጠቆሙት ካህኑ፥ ሌሎች ደግሞ የሚወዷቸውን ሰዎች አካል ቅሪት ብቻ የማግኘት ልብ የሚሰብር እውነታ እንዳጋጠማቸው ገልጸው፥ በበርካታ ቤተሰቦች ዘንድ አሁንም ከፍተኛ ተስፋ እንዳለ እና በቅርቡ ከፍርስራሹ ስር በሕይወት የተረፉ ሁለት እህቶችን ማዳን መቻሉን አስታውሰዋል።

የመረጋጋት መንፈስን ማጣት ከስሜታዊ ጉዳት በላይ መሆኑን ያስረዱት ካህኑ፥ ከዚህም በተጨማሪ የውሃ፣ የምግብ እና የኢኮኖሚ ደህንነትን ጨምሮ በጣም መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንደሚነካ ጠቁመው፥ ምንም እንኳን አንዳንድ ሱቆች እንደገና ቢከፈቱም አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴዎች ግን ውስን መሆናቸውን እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በአደጋው ምክንያት የኑሮ መተዳደሪያቸውን እንዳጡ አስታውሰው፥ “በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው” ተናግረዋል።

አንድ ቁምስና ወደ የእርዳታ ማዕከልነት መለወጡ
የቅድስት ልበ ማርያም ቁምስና በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ካሉ ሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የጠቆሙት ካህኑ፥ የቤተክርስቲያኒቷ በርካታ ሐውልቶች ቢወድሙም እና የመሠዊያው ስፍራ በከፊል ቢጎዳም የቤተክርስቲያኑ መዋቅራዊ ሁኔታ ግን ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአጎራባች ቁምስናዎች ያለው ሁኔታ ግን በጣም የተለየ መሆኑን ያመላከቱት አባ አንቶኒዮ፥ ካቴድራሉ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት እና በመሬት መንቀጥቀጡ በደረሰባቸው አደጋ ምክንያት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ፈርሰው እንደገና መገንባት እንዳለባቸው የጠቆሙ ሲሆን፥ የቁምስናው ቤተክርስቲያን በአንፃሩ በጥሩ ሁኔታ ላይ ስለምትገኝ ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታው ወሳኝ ማዕከል መሆኗን ገልጸው፥ “ቁምስናው ለካህናት የመሰብሰቢያ ቦታ፣ እንዲሁም ለአጎራባች ማህበረሰቦች የእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከል መሆኗን አስረድተዋል።

ከቬንዙዌላ ውስጥ እና ከዚያም ባሻገር የታየው አጋርነት
ካህኑ ከመላው ቬንዙዌላ እና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተደረገውን ያልተለመደ የትብብር መንፈስን በአጽንዖት በማስታወስ “ይሄንን የሚያክል ከፍተኛ አደጋ ሲደርስ አይተው እንደማያውቁ” ጠቁመው፥ አደጋውን ተከትሎ ለታዩት በርካታ የሰብአዊነት ተነሳሽነቶች ያላቸውን ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የእርዳታ ጥረቱ በተወሰነ ደረጃ የተዛባበት ምክንያት የአደጋው መጠን ሰፊ በመሆኑ፣ እንዲሁም በርካታ ድርጅቶች እና ተቋማት በአንድ ጊዜ በመምጣታቸው እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሀገረ ስብከቱ እና የቁምስና ትስስሩን በማስተባበር ፈጣን የሆነ ሀብትን እና በጎ ፈቃደኞችን ማሰባሰብ የቻለው ካሪታስ ቬንዙዌላ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ካህኑ፥ ከአደጋው በኋላ ወዲያውኑ ምላሽ የሰጠው የመጀመሪያው ድርጅት ካሪታስ መሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል።

ትልቁ ፈተና በመከራ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር አብሮ መሆን ነው
ምግብ እና መድኃኒት ከማከፋፈል ባለፈ መንፈሳዊ እንክብካቤን ማድረግ የሀገረ ስብከቱ ካህናት ካጋጠሟቸው ፈተናዎች አንዱና ዋነኛው መሆኑን የጠቆሙት አባ አንቶኒዮ፥ ራስን በሌላ ሰው ቦታ አለማስቀመጥ ቀላል እንዳልሆነ ጠቁመው፥ የሰውን ችግር እንደራስ አለማየት በተግባር የማይቻል ነገር ነው ብለዋል።

አባ አንቶኒዮን ልባቸውን ከነኳቸው በርካታ አጋጣሚዎች መካከል በፍርስራሹ ውስጥ ተይዛ የቀረችውን የልጅ ልጃቸውን በከፍተኛ ትጋት የሚፈልጉ አንዲት አያት አሳዛኝ ሁኔታ እንደሆነ አስታውሰው፥ ከዚህም በተጨማሪ የአንድ ዓመት ሕፃን ልጅን ጨምሮ በቅርቡ የመሬት መንቀጥቀጡ ሰለባ ለሆኑ በርካታ ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈጸመበትን ሁኔታ በሃዘኔታ ገልጸው፥ “እንዲህ ባለው እውነታ ውስጥ የእምነትን የብርሃን ጭላንጭል ለማብራት ትክክለኛዎቹን ቃላት ማግኘት ቀላል ሥራ አይደለም” ብለዋል።

አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና መገንባት እና ተስፋን መመለስ
አሁን የተከሰተውን አደጋን የቬንዙዌላውያንን ጽናት ያሳየውን እና እ.አ.አ. በ 1999 ዓ.ም. በቫርጋስ ክልል ከደረሰው አስከፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ ጋር ያነፃፀሩት ካህኑ ይህ አደጋ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ አስታውሰዋል።

የአካባቢው ቤተክርስቲያን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች መካከል እንደ ሕንፃ ብቻ ሳይሆን ለማህበረሰባቸው እንደ መሰብሰቢያ፣ መጽናኛ እና ጸሎት ቦታ ተደርገው የሚታዩትን አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ የመገንባት ሁኔታ መሆኑን ያመላከቱት አባ አንቶኒዮ፥ ለምዕመናኖቻቸው ይህ ሥፍራ መኖሪያ ቤታቸው እንደሆነ አዘውትረው እንደሚነግሯቸው አስታውሰው፥ “ምዕመናን እግዚአብሔርን ለማመስገን፣ ለመጸለይ ወይም ከእርሱ ጋር ለመነጋገር በፈለጉበት ጊዜ ሁሉ ወደዚህ መምጣት ይችላሉ” ብለዋል።

የአምልኮ ቦታዎችን ከመገንባት በተጨማሪ በአደጋው ለተጎዱት ምዕመናን እና ለሃዋሪያዊ አገልግሎት ሰራተኞች የሚሰጠውን መንፈሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ያመላከቱት ካህኑ፥ ይህ አገልግሎት የሚከናወነው ከካህናት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚያገለግሉት ምዕመናን ጋር እንደሆነ አስረድተዋል።

ውሃ እና ምግብ በጣም አስቸኳይ ፍላጎቶች ሆነው ቀጥለዋል
በቁሳቁስ ደረጃ፣ በጣም አጣዳፊ በሆነ ሁኔታ ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል ምግብ እና ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ በርካታ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን የሚመሩት ከማኪታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ ከላ ጉዌራ ወደብ ወይም ከአነስተኛ የአካባቢ ንግዶች ጋር በተያያዙ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሆነ እና አብዛኛዎቹ በአሁኑ ወቅት መዘጋታቸው ወይም መውደማቸው ተገልጿል።

“አንዳንድ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን አላጡም፣ ነገር ግን ገቢያቸውን በማጣታቸው ምክንያት እራሳቸውን የሚደግፉበት ምንም መንገድ የላቸውም” ያሉት አባ አንቶኒዮ፥ ምንም እንኳን የመድኃኒት ልገሳዎች በብዛት ቢኖሩም እና ቁምስናው የማህበረሰብ መድኃኒት ባንክ ቢያቋቁምም፥ ቀጣይነት ያለው የምግብ አቅርቦትን ማረጋገጥ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ትልቁ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

አባ አንቶኒዮ በማከልም የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሰለባዎችን ለደገፉት ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ያላቸውን ልባዊ ምስጋና ገልጸው፥ የሚዲያው ትኩረት ወደ ሌላ ቦታ ሲዞር የነበረው አንድነት እንዳይጠፋ ጥሪ በማቅረብ፥ “የሚደረገው እርዳታ መቀነሱ ስለማይቀር እንደገና በሁለት እግራችን ለመቆም እንድንችል እና የመልሶ ግንባታውን ሥራ ለመጀመር አሁንም ተጨማሪ የእርዳታ እጆች ያስፈልጉናል” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአገራቸው ውስጥ የሚከናወኑትን ክስተቶች በከፍተኛ ስጋት ለሚከታተሉት በውጭ ሃገራት ለሚኖሩ ቬንዙዌላውያን የተስፋ መልዕክት ያቀረቡት አባ አንቶኒዮ በመጨረሻም፥ ለሁሉም በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ከልብ የመነጨ ጥሪ በማቅረብ “ለቬንዙዌላ መጸለይን አታቋርጡ” በማለት የተማጸኑ ሲሆን፥ ሁሉም ሰው በቁሳዊ መንገድ መርዳት ባይችልም፣ ነገር ግን ፍሬ የሚያፈራበት ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ስለሚደርስ ለህዝቡ በየቀኑ መጸለይ ዋጋ እንዳለው ጠቁመው፥ ቤተክርስቲያኒቱ ከተጎዱት ጋር መቆሟን የምትቀጥልበትን መንፈስ የሚገልጹ ቃላትን በመጥቀስ፥ “እምነት ነገሮችን ቀላል አያደርግም፤ በቀላሉ እንዲቻሉ ያደርጋቸዋል፣ ምክንያቱም ወደፊት እንድንራመድ በነፍሳችን ውስጥ ጥንካሬ ይሰጠናል” በማለት አጠቃለዋል።

14 Jul 2026, 14:27