ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲው ማን-ኦሶ ንዳጎሶ፤ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲው ማን-ኦሶ ንዳጎሶ፤ 

የናይጄሪያ ብጹዓን ጳጳሳት በአገሪቱ የሚካሄዱ ጭፍጨፋዎች እና የጅምላ አፈናዎች እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ

በናይጄሪያ የተከሰተውን አሳዛኝ ሁኔታ የገመገሙት የናይጄሪያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የካዱና ሀገረ ስበት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲው ማን-ኦሶ ንዳጎሶ፥ “በኒጀር ግዛት ቦርጉ ውስጥ ከ60 በላይ ምዕመናንን ያፈናቀለ የቅርብ ጊዜ አረመኔያዊ አፈና እና በቤኑዌ ግዛት ኡኩም ሌሎች 17 ሰዎች በከባድ ሁኔታ መቁሰላቸው እና የ47 ንፁሃን ዜጎች አሰቃቂ ግድያ የፀጥታ ሁኔታውን የበለጠ እያባባሰ መጥቷል” ሲሉ አስታወቁ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅርቡ በናይጄሪያ የተከሰተውን አሳዛኝ ሁኔታን በማየት የናይጄሪያ ካቶሊክ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማቲው ማን-ኦሶ ንዳጎሶ በሳምንቱ መጨረሻ የሰጡትን መግለጫው በመጥቀስ ፊደስ የዜና ወኪል ሪፖርት አውጥቷል።

የናይጄሪያውያን ደህንነት የተጠበቀ አይደለም

“በመስጊድ፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በገበያ ወይም በቤታቸው ውስጥም ቢሆን ናይጄሪያውያን መገደላቸው፣ መጎዳታቸው እና በግዳጅ መፈናቀላቸው ቀጥሏል” ሲሉ የናይጄሪያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲው ማን-ኦሶ ተናግረዋል።

የናይጄሪያ ብጹዓን ጳጳሳት በልዩ ልዩ የታጠቁ ቡድኖች በተፈፀመ ጥቃት ለተጎዱት በሙሉ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ በቤኑዌ ግዛት ለሚገኙ ቤተሰቦች መጽናናትን በመመኘት፥ “የተጎዱትም ቶሎ እንዲያገግሙ እንጸልያለን” ሲሉ በቦርጉ ውስጥ ከሚገኝ የሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር ያላቸውን ልዩ አጋርነት ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትው ማን-ኦሶ በመግለጫቸው፥ “በኒጀር ግዛት እና በመላው ናይጄሪያ ውስጥ ከሚገኙ ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በፅኑ በመተባበር እንቆማለን፤ በቅርቡ የተጠለፉት 60 ሙስሊም ምዕመናን ደህንነታቸው ተጠብቆ ጉዳት እንዳይደርስባቸው እንደሚጸልዩ ከገለጹ በኋላ “በማንኛውም የአምልኮ ቦታ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በመላው ማህበረሰባችን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በመስጊዶች ላይ የተፈጸሙ የተቀናጁ ጥቃቶች

ብጹዓን ጳጳሳቱ የጠቀሷቸው ክስተቶች በኒጀር ግዛት ዓርብ ነሐሴ 15 የተፈጸመ፣ በሰሜን ማዕከላዊ ናይጄሪያ በሚገኘው በቦርጉ ክልላዊ መንግሥት (LGA) እና በቤኑዌ ግዛት፣ በሰሜን ማዕከላዊ ናይጄሪያ በሚገኘው የኡኩም ግዛት ውስጥ የተፈጸሙት ተከታታይ ጥቃቶች አካል እንደሆኑ ታውቋል።

የታጠቁ ቡድኖች ምናልባትም ከላኩራዋ ወይም ማሐሙዳ ከሚባል ተቀናቃኝ ቡድን ጋር በቦርጉ እና በዴካራ አውራጃ ማኅበረሰቦች እና መስጊዶች ላይ የተቀናጀ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፥ ኢላማዎቹ በዴካራ የሚገኙ በርካታ መስጊዶችን፣ ማዕከላዊ መስጊድን ጨምሮ በክፔንያ፣ በሳቦን-ጊዳን-ዛና እና እንደ ማሳካ በመሳሰሉ አካባቢዎች ያሉ መንደሮችን እንደሚያካትቱ ታውቋል።

አጥቂዎቹ በዓርብ ጸሎት ወቅት መስጊዶቹን ከወረሩ በኋላ ምዕመናኑን አፍነው በመውሰድ ብዙዎቹን በካይንጂ ሐይቅ ዙሪያ ወደሚገኙ ደኖች እንደወሰዷቸው ታውቋል። የታፈኑት ሰዎች ቁጥር ግምት የተለያየ ሲሆኑ አንዳንድ ምንጮች ከ60 በላይ እንደሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ከ100 በላይ እንደሆኑ ይናገራሉ። አንዳንድ የዓይን ምስክሮች እንደሚሉት ሽፍቶቹ ሴቶችን እና ሕፃናትን ከቤት ወደ ቤት እየገቡ ይዘው መጥለፋቸውን ተናግረዋል።

በመሬታችን ላይ የሚደርስ እልቂት ይቁም

በኡኩም ከነሐሴ 10 እስከ 11 ባለው ጊዜ ውስጥ ሞተር ሳይክል የያዙ የታጠቁ ቡድኖች በምባዙን እና ምባቴሬም አውራጃዎች በሚገኙ በርካታ ማህበረሰቦች ላይ በተመሳሳይ ጊዜ በፈጸሙት ጥቃት አርባ ሰባት ሰዎችን ገድለው በ17 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት አድርሰውባቸዋል።

በናይጄሪያ ማኅበረሰቦች ላይ የተፈጸሙትን ጥቃቶች እና ሌሎች የዓመፅ ድርጊቶችን ያስታወሱት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ “የመንግሥት ባለስልጣናት እና የአገሪቱ የጸጥታ ኤጀንሲዎች በአገሪቱ ላይ የሚደርሰውን እልቂት ለማስቆም የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ” በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የናይጄሪያ ካቶሊክ ብጹዓ ጳጳሳት ጉባኤ አባላት “ለወንበዴዎች፣ ለአሸባሪዎች፣ ለአጋቾች እና ለዋና አበዳሪዎቻቸው” የደም መፍሰስን እንዲያቆሙ በማለት ባቀረቡት ጠንካራ ጥሪ፥ “የሰው ልጅ ሕይወት የእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ የሚያጸድቅ ምንም ምክንያት የለም፤ በንጹሐን ሰዎች እንባ የወደፊት ሕይወትን መገንባት አይቻልም” ሲሉ መግለጫቸውን ደምድመዋል።

 

01 Sep 2026, 13:41