በፈረንሳይ የሚገኙ ወጣቶች በሚቀጥለው ወር ለሚደረገው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጉብኝት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የፈረንሳይ ግዛቶችን ሦስት ጊዜ መጎብኘታቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ እነዚህ ጊዜያቶች እ.አ.አ. በ 2014 ዓ.ም. በስትራስቡርግ ለሚገኘው የአውሮፓ ፓርላማ ንግግር ያደረጉበት ወቅት፣ በ 2023 ለሜዲትራኒያን ጉባኤዎች ወደ ማርሴይ ከተማ የተጓዙበት ወቅት እንዲሁም በ 2024 ዓ.ም. በሕዝባዊ እምነት መገለጫዎች ላይ በተደረገ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኮርሲካን የጎበኙበት ወቅት መሆናቸው ይታወቃል።
ይህ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጉብኝት ከ18 ዓመታት በኋላ ወደ ፈረንሳይ የሚደረግ የመጀመሪያው ይፋዊ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚሆን የተነገረ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ 2008 ዓ.ም. በኖትር-ዳም ካቴድራል ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ ጋር የተገናኙት ወጣቶች በአሁኑ ወቅት ወላጆች መሆናቸውን፤ ልጆቻቸውም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን ጉብኝት በጉጉት እየጠበቁ እንደሚገኝ እና ይህ ጉብኝት ለልጆቹ በህይወት ዘመናቸው የመጀመሪያው፣ ለወላጆቻቸው ደግሞ "በአዋቂነት ዘመናቸው" የመጀመሪያው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት እንደሚሆን ተገልጿል።
80,000 መቀመጫዎች በቅጽበት መያዛቸው
በፓሪስ አቅራቢያ በሚገኘው 'ስታድ ደ ፍራንስ' ስታዲየም ውስጥ የተዘጋጁት ወደ 80,000 የሚጠጉ መቀመጫዎች በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መያዛቸው፣ ወጣቶቹ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጉብኝት ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ በፈረንሳይ ትልቁ የስፖርት ማዕከል ውስጥ በሚካሄደው በዚህ የመጀመሪያ ሃይማኖታዊ ስብሰባ ወቅት ቅዱስነታቸው ከወጣቶች ጋር በመሆን የምሽት ጸሎት እና የሱባኤ ጊዜን እንደሚያሳልፉ ተነግሯል።
ምንም እንኳን ለጉብኝቱ የተዘጋጀው ዝርዝር መርሃ ግብር እስካሁን ይፋ ባይደረግም፣ የሚዲያ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በፈረንሳይ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች ለክርስትና እምነት ያላቸው ፍላጎት እያደገ መምጣቱን የሚያሳዩ ሲሆን፥ የእነሱ አርአያ የሆኑት ሰዎችም ብዙውን ጊዜ የእምነት ምስክሮች መሆናቸው እንዲሁም በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ላይ ዝግጅት ከሚያቀርቡት ወጣቶች መካከል፣ ከእግዚአብሔር ጋር ስላላት ግንኙነት ዘወትር በግልጽ የምትናገረው የ17 ዓመቷ ታዋቂ ዘማሪ ሞንሮ እንደምትገኝበት ተመላክቷል።
ዘማሪዋ በዘንድሮው የዩሮቪዥን የሙዚቃ ውድድር ፈረንሳይን ወክላ የተወዳደረች ሲሆን፣ በዕለት ተዕለት ህይወቷም በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የፈረንሳይ ካቴድራሎች ውስጥ ሃይማኖታዊ መዝሙሮችን በማቅረብ እንደምትታወቅ ተነግሯል።
ከአጎስጢኖሳዊያን ር.ሊ.ጳ. ጋር ለመገናኘት እየተዘጋጀች ያለች የአጎስጢኖሳዊያን “ከተማ”
ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ለሚደረገው ውይይት በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘጋጁ ከሚገኙ ቡድኖች መካከል ‘ላ ሲቴ ሴሌስቴ’ የተሰኘው እና በፓሪስ ክልል ውስጥ ካሉ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች የመጡ ወጣቶችን የሚያገናኘው ትስስር አንዱ ሲሆን፥ ይህ “ሰማያዊት ከተማ” የሚል አቻ ትርጉም ያለው የቡድኑ ስያሜ በተፈጥሮ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ጋር የተቆራኘ መሆኑ ተነግሯል።
እስካሁን ያልተጠመቁትን ጨምሮ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዳንዶቹ ባለፈው ዓመት በሮም በተካሄደው የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ላይ የተሳተፉ ሲሆን፥ በወቅቱም ስለ እምነት በርካታ ጥያቄዎችን መጠየቃቸው እንዲሁም በሮም ያገኙት ተሞክሮ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን በፈረንሳይ በደመቀ ሁኔታ ለመቀበል እንዳነሳሳቸው ተነግሯል።
በስታድ ዴ ፍራንስ የሚደረገው የጸሎት ሥነ ሥርዓት አዘጋጆች መካከል የላ ሲቴ ሴሌስቴ ቡድን ተባባሪ መስራች እና የቅዱስ ማርቲን ማህበረሰብ አባል የሆኑት አባ አሌክሲስ ጄርሞን አንዱ ሲሆኑ፥ ካህኑ ከፈረንሳዩ ሳምንታዊ ‘ፋሚሌ ክሬቲን’ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወጣቶቹ ምንም እንኳን እምነቱን የተቀበሉት እና የተጠመቁት ከህፃንነት ዕድሜ ከፍ ካሉ በኋላ ቢሆንም የቅድስና መንገድን እንዲከተሉ የሚያበረታታና የፈረንሳይ ቅዱሳንን ታሪኮች የሚያካትት የጸሎት መርሃ ግብር እንደሚኖር አስረድተዋል።
አዳዲስ ምዕመናን የቤተክርስቲያን ተስፋ መሆናቸው
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በፓሪስ የካቶሊክ የትምህርት ተቋም ግቢ ውስጥ አዲስ ከተጠመቁ ምዕመናን እና ለሚስጥረ ጥምቀት ከሚዘጋጁት ወጣቶች ጋር በሚገናኙበት ወቅት ንግግር ያደርጉላቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ የእነዚህ ወጣቶች ቁጥር በቅርብ ዓመታት ውስጥ እየጨመረ መምጣቱ የፈረንሳይን ቤተክርስቲያን ያስገረመና ያስደሰተ ክስተት መሆኑ እና በዘንድሮው የትንሳኤ ዋዜማ ብቻ ከ21,300 በላይ ሰዎች መጠመቃቸው ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለዚህ ቡድን ንግግር ሲያደርጉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ባለፈው ዓመት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከፈረንሳይ የመጡ አዲስ የተጠመቁትን እና ለጥምቀት የሚዘጋጁትን በቫቲካን ውስጥ በግል ተቀብለው አነጋግረዋቸው እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለወጣቶቹ ባደረጉት ንግግር “ጌታን በመከተል፣ እናንተ የምድር ጨውና የዓለም ብርሃን ናችሁ” ያሉ ሲሆን፥ “ቤተክርስቲያን ለማደግ እና እርዳታ ለሚያስፈልገው እያንዳንዱ ሰው ቅርብ ሆና ለመቆየት የእናንተን ውብ የእምነት ምስክርነት ትሻለች” ማለታቸው ይታወሳል።
እነዚህ ቡድኖች በአሁኑ ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ወደ ፈረንሳይ የሚያደርጉትን ጉብኝት የሚደግፈውን የበጎ ፈቃደኞች እንቅስቃሴ በማደራጀት ላይ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን፥ ምንም እንኳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀኑ መጨረሻ ስለተቀጠሩት ሠራተኞች ከተናገረው ምሳሌ ጋር በሚመሳሰል መልኩ "በመጨረሻው ሰዓት የተጠሩ" ቢሆኑም፣ ለመላው ቤተክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ በሆነ ዝግጅት ላይ መሳተፍ በመቻላቸው ደስ ሊላቸው እንደሚገባ ተነግሯል።
10,000 ተማሪዎች
በ “ስታድ ዴ ፍራንስ” የሚደረገው የምሽት ጸሎትና ዝግጅት በዋናነት ‘በዕድሜ ከፍ ላሉ ወጣቶች’ የታቀደ ቢሆንም፣ የመካከለኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ለመገናኘት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በቻምፕስ ኤሊዜስ እና በፕሌስ ዴ ላ ኮንኮርድ የሚደረገው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቅዳሴዎች ከመሄዳቸው በፊት መስከረም 16 ቀን 2019 ዓ.ም. ጠዋት በየዓመቱ በጸደይ ወቅት ለወጣቶቹ በሚዘጋጀው የጸሎት መርሃ ግብር ላይ እንደሚሳተፉ ተነግሯል።
ምዝገባው የሚጀምረው በመስከረም ወር ቢሆንም፣ አዘጋጆቹ ቢያንስ 10,000 ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የሚጠብቁ ሲሆን፥ ለታዳጊዎች የሚደረገውን ስብሰባ የማደራጀት ኃላፊነት የተሰጣቸው አባ ዣን-ሚሼል ዱፖንት እንደተናገሩት ወጣቶች የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት ላይ ለመገኘት በጉጉት እየተጠባበቁ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ፈረንሳይ የሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት ከመስከረም 15 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፥ ይህ “ዓለም ሕይወት እንዲኖራት” በሚል መሪ ቃል የሚደረገው ሃዋሪያዊ ጉብኝት ከቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 በበተለይም በቁጥር 51 ላይ የተጠቀሰውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሰማይ የወረደው ህይወትን የሚሰጥ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለት ስለ ቅዱስ ቁርባን የተናገረውን አስተምህሮ የሚያመለክት መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በእነዚህ ቀናት ፓሪስን፣ ሉርድን እና ሜትዝን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠብቅ ተገልጿል።