በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስወገድ በዓለም አቀፍ ቀን በማድሪድ የተካሄደ ሰልፍ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስወገድ በዓለም አቀፍ ቀን በማድሪድ የተካሄደ ሰልፍ  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እንዲያበቃ ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ለደነገገው ህዳር 15 ዓለም አቀፍ ቀን የሚሆን መልዕክት አስተላልፈዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ችግሩ ከኅብረተሰቡ መካከል መወገድ እንዳለበት አሳስበው፥ የእያንዳንዱን ሰው ክብር ማዕከል ያደረገ ትምህርታዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማለት ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም በሚል ዓላማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደነገገው ህዳር 15 ዓለም አቀፍ ቀን በተከበረበት ዕለት ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ይህን ችግር በተለይም በትምህርት እገዛ ለማስወገድ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወሰድ በማለት አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።

“መርዛማ አረም”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ህዳር 15/2016 ዓ. ም. በትዊተር የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በኩል በጻፉት መልዕክታቸው፥ “በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ኅብረተሰባችንን የሚጎዳ “መርዛማ አረም” በመሆኑ ከሥሩ መነቀል አለበት” ብለው፥ “ይህ ችግር ከጭፍን ጥላቻ እና ከፍትህ መጓደል እንደሚመነጭ ገልጸው፥ የግለሰብ ክብርን ማዕከል በማድረግ ትምህርታዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል” በማለት አክለዋል።

ጥቃቱን ለመከላከል ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1981 ዓ. ም. ጀምሮ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስወገድ በሚል ዓላማ ዓለም አቀፍ ቀን ሲከበር መቆየቱ ይታውሳል። ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ለ16 ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ፥ ግንዛቤን ለማስጨበጥ እና የጥብቅና እንቅስቃሴን ለማጎልበት፣ ጥቃቱ በሚያስከትላቸው ችግሮች ላይ ተወያይቶ መፍትሄዎችን ለማግኘት ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚጥር ታውቋል።

በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት፥ በዓለማችን ውስጥ በጣም ተስፋፍቶ ከሚገኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አንዱ ነው። ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸመው ይህ ጥቃት፥ በየ11 ደቂቃው አንዲት ሴት በባልዋ ወይም በቤተሰብ አባል እንደምትገደል ግምቶች ይናገራሉ።

በቅርብ ጊዜ የወጣው የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያመለክተው፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ700 ሚሊዮን በላይ ሴቶች መካከል፥ ከሦስቱ መካከል አንዷ ማለት ይቻላል፥ አካላዊ ወይም ፆታዊ ግንኙነት ባላቸው አጋሮች እና አጋር ባልሆኑ ወይም በሁለቱም አማካይነት በሕይወት ዘመኗ ቢያንስ አንድ ጊዜ ጥቃት እንደሚደርስባት ይገልጻል።

ክስተቱ በተለያዩ ቦታዎች፣ ማለትም በሥራ ቦታ እና በአውታረ መረብ መስመር ላይ ላይ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፥ በተለይም በወረርሽኙ፥ በጦርነቶች እና ግጭቶች እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል። ሴቶች እና ልጃገረዶች በተለይ በጦርነት ውስጥ ጾታዊ ጥቃት እንደ ጦርነት መሣሪያነት የሚያገለግል እና የስደተኞች መጠለያዎች ለዚህ ችግር በብዛት እንደሚጋለጡ ታውቋል።

የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ኃላፊነት

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋረል ዕለቱን ምክንያት በማድረግ ቅዳሜ ኅዳር 15/2016 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት መልክታቸው፥ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጾታዊ ጥቃትን ለመዋጋት እና ለመከላከል እንምዲሁም  ለጥቃቱ ተጎጂዎች ድጋፍ ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ተናግረዋል።

ብጹዕነታቸው በማከልም፥ "ቤተ ክርስቲያኗ የጥቃት እና የብዝበዛ ሰለባ ለሆኑት ሴቶች ቅርብ መሆኗንም ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያን በዚህ አገልግሎቷ የጥቃቱ ሰለባዎችን ደህንነት የሚያስጠብቅ የመኖሪያ ቤት አገልግሎት በመስጠት፣ ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ድጋፎችን በማድረግ፥ ተጎጂዎቹ ራሳቸውን በመርዳት ጉዳቱን እንዲያሸንፉ ማደረግ እና የደረሰባቸውን በደል ሪፖርት እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

ፍቅር እና አክብሮትን ማስተማር

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ፋሬል፥ መደረግ ያለበት ዋናው ተግባር፥ የሴቶችን ክብር ማዕከል ያደረገ ትምህርታዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ገልጸው፥ “ይህም የሚጀምረው በቤተሰብ እና በክርስቲያን ማኅበረሰቦች ውስጥ ያለውን ችግር በመገንዘብ ነው” ብለዋል። "ሰዎችን ስለ ፍቅር፣ ሌሎችን ስለ ማክበር እና ከሁሉም በላይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል አስፈላጊ ስለሆነው የራስ ሕይወት ማስተማር በወንጌል ውስጥ በጥብቅ የተገለጸ እና ሥር የሰደደ ነው" ብለዋል።

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋረል፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት “በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ዓላማ ያላቸው ቤተሰቦችን፣ ወጣቶችን፣ ጥንዶችን እና ማኅበረሰቦችን በትምህርት የመለወጥ እርምጃን እንዲወሰዱ አሳስበዋል።

“ይህም ቤተ ክርስቲያን የሰላም መሣሪያ የመሆኗ ጥሪ የሚገለጥበት ሐዋርያዊ ሃላፊነት ነው” በማለት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋረል መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

27 Nov 2023, 16:50