ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ሠነዳቸውን ሲፈርሙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ሠነዳቸውን ሲፈርሙ  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ድነታችን የተቸገሩ ድሆችን ምልክት ያደረገ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የወንጌል ደስታ” የሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው 10ኛ ዓመት በማስመልከት መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ ድሆች በኢየሱስ ክርስቶስ የድነት ምስክነት ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ እንዳላቸው አጽንዖት ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በ2006 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት “የወንጌል ደስታ” የሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ 10ኛ ዓመት ለማክበር በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው ሲምፖዚዬም ላይ ለተገኙት አባላት ዓርብ ኅዳር 14/2016 ዓ. ም. መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቅዱስነታቸው ለሲምፖዚዬሙ ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት፥ የጥንት ክርስቲያኖች ተቃውሞ እና በደል ቢደርስባቸውም ወንጌልን በድፍረት ለመመስከር የፈጸሙትን ሚሲዮናዊነትን ቤተ ክርስቲያን እንድትደግም በማለት ያቀረቡትን ጥሪ አስታውሰዋል።

የዘመናችን ችግሮች ምናልባት የበለጠ ከባድ ቢሆኑም፥ ከዚህ ችግር ለመወጣት ፈታኝ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ተናግሯል። አንዳንድ ችግሮቻችን በግልጽ ወጥተው የሚታዩ ባለመሆናቸው ቀስ በቀስ በዝምታ የሚጎዱ ናቸው ብለዋል። "በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ድክመት፣ ራስን ማስቀደም፣ ራስ ወዳድነት እና በሁላችንም ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ምኞቶች ሁል ጊዜ አሉ” ብለዋል።

ቤዛችን ከድሆች ጋር የተያያዘ ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የወንጌል ደስታ” በሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው አማካይነት፥ የቤተ ክርስቲያንን የወንጌል ተልዕኮ እና ክርስቲያናዊ ሕይወታችን ድሆችን ችላ ማለት እንደማይችሉ ግልጽ ለማድረግ መፈለጋቸውን ተናግረዋል። “የቤዛችን መንገድ በሙሉ ድሆችን ማዕከል ያደረገ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በከብቶች በረት ውስጥ በተወለደ ጊዜ፣ በእጆቹ ሥራ ሲተዳደር፣ ድሆችን እና የተናቁትን በሙሉ በልቡ ያስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

የድነት መንገዳችን አደጋ ላይ የወደቀ በመሆኑ፥ ቤተ ክርስቲያን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚለያትን ማንኛውንም ሙከራ እና ሃሳብ መቃወም እንዳለባት፥ ግልጽ እና ቀጥተኛ በሆነ መልዕክታቸው አሳስበው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ድሆችን ማዕከላዊ ከማድረግ ሌላ ምርጫ የላቸውም" ብለዋል። “ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ ወይም ርዕዮተ ዓለም ቢሆን፥ ሁሉም ቅዱስ ወንጌልን መስፈርታቸው ያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከምንም ጋር የማይደራደር ይህ መርህ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን ተቋማት እና በክርስቲያኖች ውስጥ መታየት አለበት ብለው፥ "ማንም ሰው ሊዘነጋው ወይም እራሱን ሊያመካኝ የማይችለው አቋም ለድሆች መቅረብ ያለበት የፍቅር ዕዳ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የሁሉም ማኅበራዊ ችግሮች መነሻ የእኩልነት ጥያቄ ነው

“የወንጌል ደስታ” የሚለውን ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ ክርስቲያኖች የድህነት እና የማኅበራዊ ቀውስ መንስኤ የሆነውን የእኩልነት መጓደል እና ማኅበራዊ ችግሮችን ተባብረው እንዲፈቱ አሳስበዋል። "ፍፁም ራስ ገዝ የሆነ የገበያ ኃይሎችን እና የፋይናንስ ግምቶችን" የሚሽሩ አዲስ ማኅበራዊ መዋቅሮች እና አዲስ አስተሳሰቦች እንዲገነቡ በማለት ጥሪያቸውን አድሰዋል።

"በእነዚህ አስተሳሰቦች እና አወቃቀሮች ላይ ለውጥ ካላመጣን፥ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የጤና እና የስደት ቀውሶች፥ በተለይም ዓመጾች እና ጦርነቶች እየጨመሩ ከሄዱ መላውን የሰው ልጅ፥ ድሆችን ሆኑ ድሃ ያልሆኑትን፣ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የተካተቱም ሆነ የተገለሉትን የሰው ልጆች በሙሉ አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን መመልከት አንችልም” ብለዋል። ለሲምፖዚዬሙ ተካፋዮች በላኩት መልዕክትም፥ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ክፍል አንድ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፥ የአየር ንብረት ቀውስ ምንጩ የሰውን ልጅ ወደ ድህነት በሚወስድ የምጣኔ ሃብት አለመመጣጠን መሆኑን ከመገንዘብ የተገኘ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የድሆችን ጩኸት ማዳመጥ

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፥ ክርስቲያኖች የድሆችን እና የምድርቱን ጩኸት በማዳመጥ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ባቀረበልን ጥሪ መሠረት የወንጌል ተልዕኳችንን እንድንወጣ በማሳሰብ፥ የሲምፖዚዬሙ ተሳታፊዎች ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበው በጸሎትም አብሮአቸው እንደሚሆኑ በመግለጽ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።   

25 Nov 2023, 16:35