ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ካኅናት በእግዚአብሔር ፍቅር የታነጹ እንዲሆኑ ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዓርብ ሰኔ 20/2017 ዓ. ም. በተከበረው የቅዱስ ልበ ኢየሱስ በዓል ላይ ለ32 ዲያቆናት የክኅነት ምስጢርን አድለዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ካኅናት ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ቀርበው በፍቅሩም እንዲታነጹ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ተስፋችን የተመሠረተው እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደማይተወን ባለን ዕውቀት ላይ በመሆኑ እና እግዚአብሔርም ዘወትር ከጎናችን ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ዓርብ ዕለት በተከበረው የቅዱስ ልበ ኢየሱስ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን ላይ፥ በኢትዮጵያ የሐረር ሰበካ ዲያቆን ኃይለየሱስ በላይን ጨምሮ ለ32 እጩዎች የክኅነት ማዕረግ የሰጡ ሲሆን፥ ዕለቱ ለካኅናት ቅድስና ጸሎት የሚቀርብበት ዕለት እንደነበርም ታውቋል።

ዘንድሮ የተከበረው የቅዱስ ልበ ኢየሱስ በዓል የካኅናት ኢዮቤልዩ በዓል አካል ሆኖ የሚከበር ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለዕለቱ የተለየ ትኩረት በመስጠት ወንድም ለሆኑት ካኅናት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በርን ተሻግረው በመቃብሩ ፊት ለመጸለይ፣ የጥምቀት እና የክኅነት ልብሶቻቸውን አዳኝ በሆነው በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ማስቀመጥ ለ32ቱ አዳዲስ ካኅናት የተለየ ትርጉም አለው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚህ ዐውደ ውስጥ ካኅናት ለድነት ሥራ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ላይ ከማስተንተናቸው አስቀድመው፥ የእግዚአብሔርን መገለጥ፣ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት እና ትንሳኤ ምሥጢር በዓለም ውስጥ እንዲገለጽ አደራ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውሰዋቸዋል።

እግዚአብሔር ፍቅር መታነጽ

በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከትንቢተ ሕዝቅኤል ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ እንደተጠቀሰው፥ እግዚአብሔር መንጋውን የሚጠብቅ፣ በጎቹን አንድ በአንድ የሚቆጥር፣ የጠፋውን የሚፈልግ፣ የቆሰሉትን የሚጠግን፣ የደከሙትን እና የታመሙትን የሚያበረታ እረኛ መሆኑን አስታውሰዋል።

“ነብዩ ሕዝቅኤል በትንቢቱ፥ ሰፊ እና አውዳሚ ግጭቶች ባሉበት በዚህ ዘመን የእግዚአብሔር ፍቅር ገደብ እንደሌለው ያሳስበናል” ብለው፥ “በዚህ ፍቅር ውስጥ ራሳችንን በማስገባት እንድንታነጽ፣ በእግዚአብሔር እና በራሳችንም ፊት ለማንኛውም ዓይነት መለያየት እና ጥላቻ ቦታ እንደሌለ እንድንገነዘብ ተጠርተናል” ካሉ በኋላ፥ “የእግዚአብሔር ፍቅር ወሰን የለውም፤ የተጠራነው በረሱ ፍቅር እንድንታቀፍ እና እንድንታነጽ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

ዕለታዊ የለውጥ ጎዳና

በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ በተነበበው ሁለተኛ ምንባብ ቅዱስ ጳውሎስ ለሮም ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ በምዕ. 5:8 ላይ፥ “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ደካሞች ሳለን ከራሱ ጋር አስታረቀን” ማለቱንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አስታውሰው፥ በማከልም “ሐዋርያው ይህን ማለቱ በዕለታዊው የለውጥ ጉዞ በልባችን ውስጥ ለሚገኘው የእግዚአብሔር የመለወጥ ኃይል  ራሳችንን እንድንሰጥ ይመክረናል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“ተስፋችን የተመሠረተው እግዚአብሔር ፈጽሞ እንደማይተወን ባለን ዕውቀት ላይ ነው” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን የቀጠሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እርሱ ዘወትር ከጎናችን እንደሆነ፥ እንደዚሁ እኛም ከእርሱ ጋር እንድንተባበር የተጠራን መሆናችንን፥ ከሁሉም በላይ የክርስትና ሕይወታችን ምንጭ እና ከፍተኛ ደረጃ እስከሆነ ድረስ ቅዱስ ቁርባንን የሕይወታችን ማዕከል ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህ ኃላፊነት፥ “ምስጢራትን ፍሬያማ በሆነ መንገድ መቀበል፥ በተለይም ንስሐን እና ጸሎትን ማዘውተር፥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ማስተንተን፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ማከማወን እና ልባችንን ከእግዚአብሔር ጋር ይበልጥ ማገናኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሐዋርያዊ እረኞች ደስታ

ቅዱስ ሉቃስ ከጻፈው የጌታችን የኢየሱስ ወንጌል የተነበበውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወንጌላዊው ስለ እግዚአብሔር ደስታ እንደሚናገር እና እያንዳንዱ እረኛ አንድ በግ እንኳ ቢሆን ወደ መንጋው ሲመለስ እጅግ ደስ ይለዋል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ   (@Vatican Media)

በዚህም መሠረት ካኅናት በእግዚአብሔር ቸር ፍቅር በመታገዝ፥ ማንም እንዳይጠፋ በልባቸው ባለው ምኞት በቸርነት የተሞላ የእረኝነት አገልግሎታቸውን ለማበርከት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ እና በእርሱ የዘላለም ሕይወት እንዲኖራቸው የተጠሩ መሆናቸውን ተናግረው፥ “እኛ የተጠራነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን መቀራረብ እንድናጠናክር ነው” ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ያሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ያሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት   (@Vatican Media)

ማንም የተረሳ ሳይመስለው ልዩነቶችን ማስማማት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የክኅነት አገልግሎት የኢየሱስ ክርስቶስን አካል በአንድነት ለማነጽ የሚረዳ የመቀደስ እና የማስታረቅ አገልግሎት መሆኑን በማስረዳት፥ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ሠነድ በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ ካኅናት ማንም ሰው የተገለለ እንዳይመስለው ለማድረግ ልዩነቶችን በማስማማት ሁሉንም ወደ አንድነት የቸርነት መንገድ ለመምራት የተቻላቸውን እንዲያደርጉ” በማለት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን መነሻ በማድረግ፥ ሐዋርያዊ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ሥልጣን መቀበላቸውን ምክንያት በማድረግ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ የተባበረች እና የኅብረት ምልክት የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንድትኖር ታላቅ ምኞት እንዳላቸው መናገራቸውን አስታውሰው ዛሬም ቢሆን ይህን ፍላጎታቸውን እንደሚጋሩ ገልጸዋል።

“እርስ በርስ በመታረቅ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልብ በብዛት በሚፈስ ፍቅር ተዋህደን እና ተለውጠን፣ በትህትና እና በቆራጥነት፣ በእምነት ጸንተን በቸርነት ለሁሉም ክፍት ሆነን አብረን እንጓዝ” ሲሉ የተማጸኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በእግዚአብሔር አብ መላካችንን በእርሱ መወደዳችን እና መመረጣችንን ከማወቅ በተገኘ ነፃነት፥ ከሞት የተነሣውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰላም ወደ ዓለማችን እንድናመጣ አሳስበዋል።

ለአዲሶቹ ካኅናት ያቀረቡት ጠቃሚ ምክር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ አዲስ ለተቀቡት ካኅናት ባቀረቡት ምክር፥ መናገር የሚፈልጉት ቀላል ቢሆንም ነገር ግን ለወደፊት ሕይወታቸው እና እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸው በአደራ ለተሰጣችሁ ነፍሳት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

አንደኛ፥ እግዚአብሔርን እና ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ፣ እንዲሁም ራሳቸውን በልግስና እንዲሰጡ አሳስበዋል። ሁለተኛ፥ ምስጢራትን በሚያከብሩበት እና በጸሎት ጊዜ በተለይም በቅዱስ ቁርባን ስግደት እና በክኅነት አገልግሎት ትጉዎች እንዲሆኑ አሳስበዋል። ሦስተኛ፥ ለመንጋቸው ቅርብ እንዲሆኑ፣ ያለ ምንም ዓይነት አድልዎ ለሰዎች በሙሉ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን በነጻ እንዲሰጡ፥ ይህንንም ለእኛ ሲል ከተሰቀለው ከኢየሱስ ክርስቶስ የተወጋ ጎን እና ከቅዱሳን ዓርዓያነት እንዲማሩ አሳስበዋል። አራተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ሺህ ዓመታት ታሪኳ አስደናቂ የክኅነት ቅድስና ምሳሌዎች ያላት መሆኑን እና ዛሬም የቀጠለ መሆኑ እንዲያስታውሱ ጠይቀዋል።

የባለፉት ዘመናት ጠንካራ እና ቅዱሳን ካኅናት ውድ ሀብት መንከባከብ

በዚህ ዐውደ፥ ከቀደምት ማኅበረሰቦች ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕታትን፣ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ ሐዋርያትን፣ ሚስዮናውያንን እና የበጎ አድራጎት ሥራ ደጋፊዎች የነበሩ ካህናትን ማፍራቷን አስታውሰዋል። ይህን ውድ የቤተ ክርስቲያን ሃብት እንዲንከባከቡት፣ ታሪካቸውን እንዲማሩ፣ ሕይወታቸውን እና ሥራቸውን እንዲያጠኑ፣ በጎነታቸውን እንዲከተሉ፣ በቅንዓታቸው እንዲነሳሱ እና ምልጃቸውን ሳያቋርጡ እንዲያቀርቡ አደራ ብለዋል።

“የዛሬው ዓለም ብዙውን ጊዜ አጠራጣሪ እና ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ የስኬት እና የክብር ሞዴሎችን ያቀርባል” በማለት በምሬት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ካኅናቱ በእነዚህ ከመታለል ይልቅ በእምነት እና በመሰጠት ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻቸው እና ለእህቶቻቸው አገልግሎት በማዋል፥ ያሳለፉትን ጠንካራ ምሳሌነት እና ሐዋርያዊ ፍሬያማነት እንዲመለከቱ” በማለት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ አዲስ የተቀቡ ካኅናት፥ የካኅናት እና የተስፋ እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የፍቅር ጥበቃ በአደራ እንዲሰጡ በመጋበዝ፥ በእያንዳንዱ ቀን ልባቸው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ልብ የበለጠ እዲቀርብ እና ከዘላለማዊው እረኛ ጋር እንድንስማማ ለማድረግ እርምጃችንን ትመራው እና ትደግፈው ዘንድ ተማጽነዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የተፈጸመ የክኅነት ምስጢር አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት
በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የተፈጸመ የክኅነት ምስጢር አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት   (@Vatican Media)
28 Jun 2025, 17:21