ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሰላም የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት እንደሆነ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የ“ፒያሳ ሳን ፒዬሮ” መጽሔት የሐምሌ ወር እትም በሐምሌ ውስጥ የሚከበረውን የወጣቶች ኢዮቤልዩን የተመለከተ ሲሆን፥ በውስጡም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሦስት ልጆች እናት ዛይራ ሰላምን የማግኘት መብት በማስመልከት ላቀረበችላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ መያዙ ተመልክቷል።
የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት
እናት ዛይራ ለቅዱስነታቸው ባቀረበችላቸው ጥያቄ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ባላት ጥልቅ የሰላም ፍላጎት ላይ በማሰላሰል፥ የዓለም ጦርነት ቢነሳ የልጆች ህልሞች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ቤት መግዛት፣ ትምህርት ቤት መላክ ወላጆቻቸው የከፈሉት መስዋዕትነት ምን ሊሆን እንደሚችል እና የወደፊት ሕይወታቸውን ከጉዳት ማዳን” የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረቧ ታውቋል።
“ሰላም መሠረታዊ መብት ነው” የምትለው እናት ዛይራ፥ “የአንድ አገር መሪ አንድ ቀን ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ፥ የራሱ ሕዝብ ለመጥቀም በመፈልግ የራሱ ያልሆነውን መሬት በኃይል የሚነጥቅ ከሆነ የሕጻናት የወደፊት ህልም እና ዓላማ ምን ሊሆን እንደሚችል እና “ይህን ጉዳይ ለምን ረሳነው?” ስትል ጠይቃለች።
የእግዚአብሔርን ልብ የሚነካ ጥሪ ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ጉዳይ በማስመልከት ለእናት ዛይራ በሰጡ ምላሽ፥ “የእናት ዛይራ ጩሄት ወደ እግዚአብሔር ልብ የሚደርሱ ናቸው” ብለው፥ አስቸጋሪ እና ግራ በሚያጋቡ ጊዜያት ውስጥ እግዚአብሔር ሰዎች እንደሚጎበኝ አስረድተዋል።
“በዚህ ወቅት ቸልተኞች መሆን የለብንም” በማለት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ይልቅስ የእግዚአብሔር ፍቅር ለሰብዓዊ ቤተሰብ ጥቅም እና አንድነት ያለማቋረጥ መሥራት እንደሚገባን ያሳስበናል ብለዋል።
ሰላም ንቁ ስጦታ ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክታቸውን በመቀጠል፥ ቅድስት መንበር ዕውቅና ከሰጠቻቸው የዲፕሎማሲ አባላት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉትን ስብሰባ በማስታወስ፥ “ሰላም በክርስቲያናዊ ግንዛቤም ሆነ በሌሎች በርካታ ሃይማኖታዊ ወጎች ውስጥ ከሁሉ በፊት ስጦታ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የሰላም ስጦታ በጥረት የሚገኝ መሆኑንም በማስታወስ፥ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ዳራችን ምን ይሁን ምን ሁላችንንም የሚፈታትን እና የሚያሳትፍ ስጦታ መሆኑን አስረድተዋል። የሰላም ስጦታ በልብ ውስጥ የሚታነፅ እና የሚጀምር መሆኑን ያስረዱት ቅዱስነታቸው፥ ሰላምን በጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን በቃላትም ከማደፍረስ አልፎ ተርፎም ማጥፋት ስለሚቻል፥ ትምክህተኝነትን እና ቂምን ከሥሩ በመንቀል ቃላቶቻችንን በጥንቃቄ በመምረጥ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የእናት ዛይራ ጥያቄን በቅንነት ሲመልሱ፥ አንዳንድ ጊዜ ለሁኔታው ምንም መፍትሄ የሌለ እና የነገሮች መባባስ እውን ሆኖ ሊሰማን እንደሚችል ተናግረው፥ እነዚህ ሁኔታዎች ልባችንን በአስቸኳይ በማንጻት ከሰላም ጋር ዝምድናን እንድንመሠርት የሚያሳስቡን ናቸው ብለዋል።
ሰላም ውይይት እና ጸሎትን ይጠይቃል
ሰላምን ለማምጣት ሁሉም ሰው ወደ ሰላም አምላክ ጸሎቱን እንዲያቀርብ፥ እንደ ማኅበረሰቦች እና እንደ ግለሰብ በየቀኑ ለሰላም መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የተወደዱት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እንዳሳሰቡት ሁሉ፥ ከግጭት ይልቅ እውነተኛ የእርስ በርስ ግንኙነት ባሕልን ለማስፋፋት እና በስልጣን ላይ ገደብ በማበጀት በሁሉም ደረጃ የሚካሄድ ውይይት ከጸሎት ጋር አብሮ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ጸሎትን እና ተግባርን ማጣመር ፈታኝ መሆኑን ቢገነዘቡትም፣ ትናንሽ ተግባራት እንኳ ቢሆን ነገር ግን በቋሚነት ደረጃ በደረጃ ማከናወን እንደሚቻል ተናግረዋል።
“ልጆች እውነተኛ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን የማግኘት መብት አላቸው” በማለት ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ ምን ጊዜም ቢሆን ጦርነት መፍትሄ ሊሆን የማይችል መሆኑን በጥብቅ ገልጸዋል።
