ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የሚሊተሪ ፖሊስ ጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያሳርጉ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የሚሊተሪ ፖሊስ ጸሎት ቤት ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ሲያሳርጉ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በፍትሕ መጓደል ውስጥም ቢሆን ክፋት ሊያሸንፍ እንደማይችል አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን ላይ፥ በኢዮቤልዩ ዓመት ወደ ሮም የሚመጡ ነጋዲያን ድኅንነት ለመጠበቅ የጣሊያን ፖሊስ ሠራዊት ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የዕረፍት ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ በሚገኙባት ኮረብታማ የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ማክሰኞ ሐምሌ 8/2017 ዓ. ም. በሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት ማዕከል በሚገኝ ጸሎት ቤት ውስጥ የተዘጋጀውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት መርተዋል።

በጣሊያን ውስጥ “ካራቢኒየሪ” ተብለው የሚጠሩት የሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት አባላት በጣሊያን ብሔራዊ ጦር ኃይሎች ሥር የሚገኙ እና ኃላፊነታቸው የሀገር ውስጥ ሕዝባዊ ሥርዓትን እና ደኅንነትን የሚያስከብሩ ወታደራዊ ፖሊሶች እንደሆኑ ይታወቃል።

በካስቴል ጋንዶልፎ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር አቶ ጉይዶ ክሮሴቶ እና የሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ ሳልቫቶሬ ሉዎንጎ፥ በጣሊያን የጦር ኃይሎች ሐዋርያዊ አገልግሎት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ብጹዕ አቡነ ጃን ፍራንኮ ሳባ ጋር ተገኝተዋል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች እና እህቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “ወንድም እና እህት” በሚለው ክርስቲያናዊ ሰላምታ ላይ በማትኮር ባሰሙት ስብከታቸው፥ ይህ መጠሪያ በሥርዓተ አምልኮ ውስጥ በተደጋጋሚ የመቀራረብ እና የመዋደድ ምልክት የሆነውን የእርስ በርስ ግንኙነቶችን የሚወክል መሆኑን አስረድተዋል።

“የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስንፈጽም ማለትም እግዚአብሔር እንደወደደን እኛም እርስ በርሳችን ስንዋደድ ሁላችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞችና እህቶች ነን” ብለው፥ ቀጥለውም “ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ እንዲኖር የሚልክ በመሆኑ እርስ በርሳችን ስንዋደድ እያንዳንዱ ግንኙነትታችን የእርሱ ስጦታ ይሆናል” ብለዋል።

“የእግዚአብሔር ፍቅር እጅግ ታላቅ ነው!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በነበረበት ሰዓት ማርያም የእርሱ ብቻ ሳትሆን “የሁላችን እናት እንድትሆን አደራ ማለቱን” አስታውሰው፥ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመጀመሪያዋ ደቀ መዝሙር የምትባለው የእግዚአብሔርን ቃል በፍቅር እና በታማኝነት በመጀመሪያ የተቀበለች በመሆኗ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት አባላት ጋር ሆነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት አባላት ጋር ሆነው   (@Vatican Media)

የፈተና ጊዜ ታማኝነት

የጣሊያን ሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት በቅርቡ  75ኛ የምሥረታ ዓመቱን ባከበረበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን (ቨርጂጎ ፊዴሊስ) የሠራዊቱ ጠባቂ ባልደረባ አድጎ ማክበሩን አስታውሰዋቸዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እያንዳንዱ የሚሊተሪ ፖሊስ መኰንን የማርያምን ታማኝነት ለጣሊያን ሕዝብ እና ለሀገር ያለው ታማኝነት ሞዴል አድርጎ ይመለከት እንደ ነበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ የሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊቱ ለጣሊያን ሕዝብ ላበረከተው የተከበረ አገልግሎት እንዲሁም ሮምን ለመጎብኘት ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ድኅንነትን በማረጋገጥ ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

“ማኅበራዊ ሥርዓትን የሚያቆስል ኢ-ፍትሃዊነት ሲያጋጥም ክፋት ያሸንፋል ብሎ በማሰብ በፈተና አትውደቁ” በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “በተለይ በዚህ ጦርነት እና ዓመፅ በበዛበት ዓለም ለገባችሁለት ቃል ኪዳን ታማኞች እንዲሆኑ፣ እንደ የመንግሥት አገልጋዮች ወንጀሎችን በሕግ እና በታማኝነት ልትከላከሉ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በአልባኖ የሚገኙትን የቅድስት ኪያራ ድሆች ማኅበር ገዳማውያትን ሲጎበኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በአልባኖ የሚገኙትን የቅድስት ኪያራ ድሆች ማኅበር ገዳማውያትን ሲጎበኙ   (@Vatican Media)

በአልባኖ ያደረጉት የገዳማውያት ቤት ጉብኝት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የሚሊተሪ ፖሊስ ሠራዊት ማዕከል ካቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓተ በኋላ በአልባኖ የሚገኙትን የቅድስት ኪያራ ድሆች ማኅበር ገዳማውያትን ለአጭር ጊዜ ጎብኝተው በገዳሙ ውስጥ ባለው ጸሎት ቤት ከመነኮሳቱ ጋር ጸሎት አድርሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከገዳማውያቱ ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ አብረዋቸው የተወያዩ ሲሆን፥ ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ ከመመለሳቸው በፊት ባደረጉት ንግግር፥ “ቤተ ክርስቲያን ስለ ሕይወታችሁ ማወቁ መልካም እና ውድ ምስክርነት ነው” ብለው፥ ጽዋን እና ሕብስት ማስቀመጫን በስጦታነት አቅርበውላቸዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በገዳሙ ውስጥ ከመነኮሳቱ ጋር ጸሎት ሲያደርሱ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በገዳሙ ውስጥ ከመነኮሳቱ ጋር ጸሎት ሲያደርሱ   (@Vatican Media)

 

15 Jul 2025, 17:54