ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን ጋር በካስቴል ጋንዶፎ ተገናኙ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን ካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ በሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ተቀብለው ያደረጉት ውይይት ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት እና ለሰላም በሚደረግ ውይይት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው እንዳመለከተው፥ ውይይቱ በሩስያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም እና ለጦርነቱ ፍትሃዊነት ያለው ዘላቂ መፍትሄን ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ገልጾ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለጦርነቱ ሰለባዎች የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ በጸሎት ከጎናቸው መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ቅዱስነታቸው አያይዘውም፥ እስረኞችን ለመፍታት እና ከቤተሰቦቻቸው የተነጠሉ ሕፃናትን ወደ ወላጆቻቸው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት አበረታትተው፥ የሁለቱንም አገራት ማለትም የዩክሬን እና የሩሲያ ተወካዮችን ለድርድር ለመቀበል ቫቲካን ፈቃደኛ መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ከውይይታቸው በኋላ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን ለጋዜጠኞች በእንግሊዘኛ ቋንቋ በሰጡት አጭር መግለጫ፥ ቅዱስነታቸው ባደረጉላቸው መስተንግዶ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ በተለይም በጦርነቱ ወቅት ወደ ሩሲያ የተወሰዱትን የዩክሬን ልጆች ጉዳይ በተመለከተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ቫቲካን ላደረጉት ድጋፍ በማመስገን ጉዳዩ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እና ታግተው ወደ ሩስያ የተወሰዱትን ሕጻናት ወደ ወላጆቻቸው የመመለስ አስፈላጊነት አበክረው ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ዘሌንስኪ ዩክሬን ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፥ ጦርነት ቆሞ ሰላም እንዲወርድ መፈለጋቸውን በመግለጽ ቫቲካን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጦርነቱን ለማስቆም ባላቸው ምኞት ለከፍተኛ ደረጃ የመሪዎች ስብሰባ ቦታን እንደሚያመቻቹ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
