ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ በቬትናም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ብቻቸውን እንዳልሆኑ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቬትናም የመጀመሪያ ሰማዕት የተባለለት የብፁዕ እንድርያስ ፉ የን 400ኛ የልደት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የቪዲዮ መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መገናኛ በኩል በላኩት መልዕክት፥ በቬትናም ውስጥ የሚገኙ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን (ካቴስቶች) ለእምነታቸው እና ለቤተሰባቸው ያላቸውን ፍቅር እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የብፁዕ እንድርያስ ፉ የን 400ኛ የልደት መታሰቢያን በማስመልከት ለቬትናም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን የቪዲዮ መልዕክት የላኩ ሲሆን፥ በሮም ከሰኞ ሐምሌ 21-25/2017 ዓ. ም. ድረስ ከሚከበረው የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ቀደም ብሎ በላኩት መልዕክት፥ በአገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ጥሪውን ለተቀበሉት ወጣቶች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በተለይም በብፁዕ እንድርያስ ፉ የን ቅዱስ አጽም ፊት ለጸሎት ለተገኙት ምስጋባቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በታላቁ የቬትናም ልጅ ሕይወት ላይ በማሰላሰል በላኩት መልዕክት፥ ብፁዕ እንድርያስ ፉ የን ወንጌልን ወደ ቬትናም ለወሰዱ ኢየሱሳውያን በዋጋ ሊተመን የማይችል እገዛ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ለእምነቱ ሲል ተገደለ

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው፥ የቬትናም ተወላጅ ብፁዕ እንድርያስ ፉ የን በእምነቱ ምክንያት መታሰሩን እና እምነቱን ለመካድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ በሰማዕትነት መገደሉን ገልጸዋል።

ካቶሊክ ሚሲዮናውያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ቬትናም ሲደርሱ
ካቶሊክ ሚሲዮናውያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ቬትናም ሲደርሱ

በ19 ዓመቱ ሕይወቱን በሰማዕትነት የተሰዋውን ብፁዕ እንድርያስ ፉ የን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ በግድያው ወቅት “ፍቅርን በፍቅር” መመለስ ለሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ ምላሽ መስጠቱን አስታውሰዋል።

ምስክርነቱ በቬትናም ውስጥ የሰማዕትነት ማዕረግ እንዳስገኘለት እና የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2000 ዓ. ም. ብጽዕናውን ይፋ ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ ብፁዕ እንድርያስ ፉ የን የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ባልደረባ እንደመሆኑ፥ መምህራኑ የወጣቱን የሰማዕትነት ምሳሌ በመከተል በፈተና መካከል እምነትን ለማስተማር የሚተጉትን በሙሉ እንዲያበረታታ በማለት ምልጃቸውን አቅርበዋል።

የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ቤተ ክርስቲያን

የቬትናምን ቤተ ክርስቲያን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በመልዕክታቸው አማካይነት የቬትናም ማኅበረሰብ ሕጻናትን እና ወጣቶችን ስለ እምነት ለማስተማር በተዘጋጁ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን የተሞላች መሆኗን ገልጸዋል። በቬትናም እና ከቬትናም ውጪ 64,000 የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን እንደሚገኙ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ መምህራኑ የቁምስና ሕይወት መሠረት ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

በዚህ መስክ የሚያገለግሉትን በማመስገን፥ በትምህርታቸው እና በአርአያነታቸው “ልጆች እና ወጣቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነትን እንዲመሠርቱ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት ይህን ስጦታቸውን ፈጽሞ አሳንሰው እንዳይመለከቱት አሳስበዋቸዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን በመቀጠል መምህራኑ “የእግዚአብሔር ፍቅር ሕያው ምልክቶች ለመሆን በቤተ ክርስቲያን የተላኩ ናቸው” ብለው፥ እንደ ብፁዕ እንድርያስ ያሉ ትሑት አገልጋዮች በሚስዮናዊነት ቅንዓት የተሞሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ብፁዕ እንድርያስ የእምነት ባልንጀሮቹ በእምነታቸው እንዲጸኑ እና በእስር ላይ በነበረበት ጊዜም ለእርሱ እንዲጸልዩ ማበረታታቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ይህ የክርስትና ሕይወት በተለይም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ሥራ “ፈጽሞ የብቸኝነት ሥራ” እንዳልሆነ በመግለጽ ሁላችንም የኢየሱስ ክርስቶስ አካል ነን” በማለት አስረድተዋል።

በቤተሰብ እና በባህል ውስጥ የተመሠረተ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቀደሙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ንግግርን በመድገም እንደተናገሩት፥ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን አገልግሎት መነሻው ቤተሰብ እና የባህል ቅርስ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ለቤተሰቦቻቸው እና ለትውልድ አገራቸው ያላቸውን ፍቅር በሥራቸው ሕያው እንዲያደርጉት አበረታተዋቸዋል።

እምነታቸው እና ባህላቸው ወደ ሌሎች የተላለፈው “በተለይም እንደ ብፁዕ እንድርያስ በመከራ ውስጥ የመሰከሩት እና በእግዚአብሔር እንዲታመኑ ያስተማሩት የወላጆች እና የአያቶች ጠንካራ እምነት ነው” ብለው፥ የእግዚአብሔር ስጦታዎች የሆኑ እነዚህን ወጎች እና የእምነት መሠረቶችን ለሌሎች የማካፈል ተልዕኳቸውን እንዲቀጥሉበት አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የቬትናም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ለወጣቶች ኢዮቤልዩ ወደ ሮም ከሚመጡት ወጣት ምዕመናን ጋር በመንፈስ እንዲቀላቀሉ እና በቬትናም ከሚገኙ ወንድሞች እና እህቶች ጋር እንዲተባበሩ ጠይቀው፥ እነርሱን እና ሥራቸውን ለእግዚአብሔር አደራ በመስጠት በጥሪው ላይ ለሚገኙት ቡራኬያቸውን በመላክ የብፁዕ እንድርያስን አማላጅነትንም በጸሎት ጠይቀዋል።

 

26 Jul 2025, 16:54