ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከመነኮሳቱ የተበረከተላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከመነኮሳቱ የተበረከተላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ   (@VATICAN MEDIA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ዓለም ለጋስ ሴቶች የሚያስፈልጉት መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤያቸውን በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የቅድስት አገር ቀርሜላውያን መነኮሳትን በቫቲካን ተቀብለዋቸዋል። ለእግዚአብሔር ጥሪ ለሰጡት ምላሽ መነኮሳቱን አወድሰው፥ በቅድስት ሀገር የሚኖሩ ቀርሜሎሳውያት ምስክርነትን እና ለሰላም የሚያቀርቡትን የዘወትር ጸሎት አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የጠቅላላ ምዕራፍ ጉባኤያቸው ለማካሄድ ወደ ሮም የመጡ የቅድስት አገር ቀርሜሎሳውያት እህቶችን፣ የቅድስት ካትሪን ማኅበር እህቶችን፣ የሳሌዢያ ሚስዮናውያን እህቶችን እና የቅዱስ ጳውሎስ ማኅበር እህቶችን ሰኞ መስከረም 12/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለገዳማውያቱ ማኅበራት የጋራ መሠረት የሆነውን “ድፍረት” የሚለውን በማስታወስ፥ በመጽሐፈ ምሳሌ ምዕ. 31:10 ላይ “ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል” የሚለውን በመጥቀስ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከክርስቶስ ዘንድ የሚገኝ ታማኝነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዓሥራ አራተኛ፥ የገዳማውያቱን ታሪክ መሠረት በማድረግ እንደተናገሩት፥ለእግዚአብሔር ጥሪ በቅድሚያ ምላሽ የሰጡት፥ “ድሆች፣ ንጹሐን እና ታዛዥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል አንዳንድ ጊዜ እስከ ሰማዕትነት ደርሰው ሥራውን የቀጠሉት፥ ለትውልዶች መንገድ የከፈቱት በርካታ ጠንካራ እና ደፋር ሴቶች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ታማኝነትን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ለምንኩስና ሕይወት መሠረቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የሚመጣ የጸሎት፣ ከቅዱሳት ምስጢራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር እና ከቃሉ ጋር መቀራረብ፣ የማሰላሰል ወይም የአገልግሎት ሕይወት እንደሆነ አስረተዋል።

“በማያምን ዓለም ውስጥ ይህ እንደ ሌላ ዓለማዊ መንፈሳዊነት የሚታይ ከሆነ፣ የልዩ ልዩ ገዳማዊ ማኅበራት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ከእግዚአብሔር በሚመጣ ብርታት የተነሳ በዓለም ላይ ያላቸውን ጠቀሜታ የሚያሳዩ ናቸው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ ገዳማውያቱ ትሕትናን እንዲላበሱ፣ ኃይላቸው እግዚአብሔር መሆኑን እንዲያውቁ እና ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እንዲቀርቡ በማበረታታት በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ መጋራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ገዳማውያትን በቫቲካን ሲቀበሉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ገዳማውያትን በቫቲካን ሲቀበሉ   (@VATICAN MEDIA)

ዓለም ለጋስ ሴቶች ያስፈልጉታል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የእግዚአብሔር ኃይል ሊገለጥ የሚችለው በማኅበራቱ መስራቾች እና ቀደምት አባላት በሆኑት፥ ሬጂና ፕሮትማን፣ የከበረ ደሙ ማሪ ገርትሩድ፣ ማሪ-አኔ ደ ቲሊ፣ የአቪላ ቅድስት ቴሬዛ እና የቀርሜሎስ ገዳም መነኮሳት በኩል እንደሆነ አስረድተው፥ እነዚህ በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ራሳቸውን የሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አክለውም፥ “ይህ ከእነርሱ የተቀበላችሁት ውርስ ዛሬ የእናንተን መኖር አስፈላጊ ያደርገዋል” ብለው፥ “በዘመናችንም ቢሆን ለጋስ ሴቶች ያስፈልጋሉ” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ገዳማውያትን በቫቲካን ሲቀበሉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ገዳማውያትን በቫቲካን ሲቀበሉ   (@VATICAN MEDIA)

የቀርሜሎሳውያት ምስክርነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ንግግራቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት፥ በቅድስት አገር የሚገኙ የቀርሜላውያን ማኅበር እህቶችን በመጥቀስ፥ “በጥላቻ እና በዓመፅ በተጠቁ ቦታዎች ሆነው በንቃት እና በጽሞና እንዲሁም እግዚአብሔርን በመታመን የሚሰጡት ምስክርነት እና ለሰላም የሚያቀርቡትን የማቋርጥ ጸሎት አስታውሰዋል።

“ሁላችንም በጸሎታችን እንተባበራችኋለን፤ በእናንተ አማካይነት እኛም መከራን ወደሚቀበሉት ሰዎች ዘንድ እንቀርባለን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከመነኮሳቱ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከመነኮሳቱ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (@VATICAN MEDIA)

 

23 Sep 2025, 16:44