ር.ሊ.ጳ ሊዮ እግዚአብሔር መስቀልን ወደ ሕይወት መንገድ ይለውጠዋል ማለታቸው ተገለጸ!

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ እሁድ መስከረም 04/2018 ዓ.ም ጌታችን ኢየሱስ ለእኛ ሲል ተሰቃይቶ፣ ተቸንክሮ የሞተበት መስቀል ከፍ ከፍ ተደርጎ የሚከበርበት እና የሚዘከርበት የመስቀል በዓል ተከብሮ ማለፉ ይታወቃል። ይህ የመስቀል በዓል በተከበረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቅዱስ መስቀል ክብረ በዓል ላይ ትኩረቱን ባደርገው አስተንትኖ በቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው ባደረጉት አስተንትኖ "የእግዚአብሔር ፍቅር" "የሞት መሣሪያን ወደ የሕይወት መንገድ" ለውጦታል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም በቅድስት እሌኒ አማካይነት የመስቀሉ እንጨት መገኘቱን እና በንጉሠ ነገሥት ሄራክሌዎስ ወደ ቅድስት ከተማ የተመለሰውን ንዋያተ ቅድሳት በማሰብ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል ክብረ በዓልን ታከብራለች።

ግን ዛሬ ይህንን በዓል ማክበር ለእኛ ምን ትርጉም አለው? በመስዋዕተ ቅዳሴ ጊዜ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ይህንን እንድንረዳ ያስችለናል (ዮሐንስ 3፡13-17 ተመልከት)። ትዕይንቱ የተከናወነው በሌሊት ነው፡ ከአይሁድ መሪዎች አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ፣ ቅን እና አእምሮ ያለው ሰው (ዮሐንስ 7፡50-51 ተመልከት)፣ ኢየሱስን ሊገናኘው መጣ። ብርሃንን ፣ ምሪትን ይፈልጋል፡ እግዚአብሔርን ፈልጎ የናዝሬትን ጌታ እርዳታ ጠየቀ፣ ምክንያቱም እርሱ አስደናቂ ምልክቶችን የሚያደርግ ነቢይ መሆኑን ያውቃልና።

ጌታ ተቀብሎታል፣ ያዳምጠዋል፣ በመጨረሻም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ” የሰው ልጅ ተሰቃይቶ ሞቶ፣ ከሞት መነሳት እንዳለበት ገለጠለት (ዮሐ. 3፡15)። አክሎም፡- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና" (ዩሐ 3፡16) በማለት ይናገራል።  ምናልባት በአሁኑ ጊዜ የእነዚህን ቃላት ትርጉም ሙሉ በሙሉ ያልተረዳው ኒቆዲሞስ፣ ከስቅለቱ በኋላ፣ የአዳኙን አካል ለመቅበር በሚረዳበት ጊዜ በእርግጠኝነት ሊረዳው ይችላል (ዮሐ. 19፡39)። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለመቤዠት ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ እንደሞተ ይረዳል።

ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ለኒቆዲሞስ የነገረው ከብሉይ ኪዳን የተነገረውን ታሪክ በማስታወስ ነው (ዘኁ. 21፡4-9)፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ በመርዛማ እባቦች ተነድፈው ሲመቱ፣ ሙሴ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመቀበል በሰራው እና በእንጨት ላይ ያስቀመጠውን የነሐስ እባብ በመመልከት ድነዋል።

እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ በመግለጥ አዳነን፣ ራሱን አጋር፣ መምህራችን፣ ሀኪም፣ ወዳጃችን አድርጎ በማቅረብ፣ ለእኛ እንኳን በቅዱስ ቁርባን የተሰበረ እንጀራ ሆነ። ይህንንም ሥራ ለመፈጸም፣ ሰው ከፈጠራቸው ጨካኝ የሞት መሣሪያዎች አንዱን ማለትም መስቀልን ተጠቅሟል።

ዛሬ “መስቀልን” ከፍ ከፍ አድርገን የምናከብረው በዚህ ምክንያት ነው፣ እግዚአብሔር ለእኛ መዳን ሲል ተሸክሞ ከሞት መንገድ ወደ ሕይወት መሣሪያነት ለወጠው፣ ከእርሱም ምንም ሊለየን እንደማይችል ያስተማረን ታላቅ ፍቅር ነውና (ሮሜ 8፡35-39) እናም የእርሱ ፍቅር ከኃጢአታችን የላቀ ነው።

እንግዲያውስ ከልጇ ጎን በቀራንዮ ያለች እናት በማርያም አማላጅነት የእርሱ የማዳን ፍቅሩ ሥር ሰዶ በውስጣችን ያድግ ዘንድ እኛም እርሱ እንዳደረገው እርስ በርሳችን እንዴት አንዳችን ለአንዳችን መሰጣጣት እንችል እናውቅ ዘንድ እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን።

15 Sep 2025, 11:53

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >