ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ "ወጣቶች በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ተስፋን የሚወክሉ ናቸው" ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ "Med 25 Bel Espoir" በተባለች መርከብ ላይ ተሳፍረው የሜዲቴራኒያን አገራት ወደቦችን በማቋረጥ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች ሰላምታ አቅርበዋል። ወጣቶቹ በባሕሎች፣ በሃይማኖቶች እና በአገራት መካከል የጋራ ውይይትን እና መግባባትን ለማጎልበት የሚያደርጉትን ጥረት በማድነቅ የተስፋ ምስክሮች በመሆናቸው አመስግነዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ዓርብ ጥቅምት 7/2018 ዓ. ም. ከቀትር በኋላ ከሮም በስተደቡብ ምሥራቅ በ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ኦስቲያ የባህር ዳርቻ ከተማ ተጉዘው፥ “ሜድ 25 ቤል ኢስፖየር” በተሰኘች መርከብ የሜዲትራኒያን አገራት ወደቦችን ለወራት ሲጎበኙ የቆዩ ከተለያዩ አገራት እና ሃይማኖቶች ከተወጣጡ 25 ወጣቶች ጋር ተገናኝተዋል።

“ቤል ኢስፖይር” በተሰኘች የወጣቶች የሰላም ትምህርት ቤት መርከብ ላይ ከተሳፈሩት መካከል፥ የሰላም ማሰልጠኛ ፕሮጀክቱ የተጀመረበት በፈረንሳይ የማርሴይ ከተማ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ማርክ አቬሊን የሚገኙ ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው በመርከቧ ላይ ለተሳፈሩት ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ በጥላቻ፣ በዓመፅ እና በመከፋፈል ውስጥ ለሚገኝ ዓለማችን የተስፋ ምልክቶችን እንድትሰጡ” በማለት አበረታተው፥ ወደ ዓመፅና ግጭት እየተጓዘ በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ ሰላም ፈጣሪዎች እና አራማጆች መሆንን እንዲማሩ አሳስበዋቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመርከቧ ላይ ከወጣቶች ጋር ሲገናኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመርከቧ ላይ ከወጣቶች ጋር ሲገናኙ   (@Vatican Media)

“ቤል ኢስፖይር”

“ቤል ኢስፖይር” የተሰኘች መርከብ ፈረንሳይ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1940ዎቹ ለመጓጓዣነት የተጠቀመቻት ስትሆን በዚህ ጊዜ የወንድማማችነትን መልዕክት ለማሰራጨት የሜዲትራኒያን አገራት ወደቦችን ማቋረጥ ከጀመረች ስምንት ወራትን ማስቆጠሯ ታውቋል። በላቫሌታ፣ ቱኒዝ፣ ቀርጤስ፣ ኢስታንቡል (ፓትርያርክ ባርቶሎሜዎስ)፣ ራቨና እና ኔፕልስ አጭር ቆይታ ይደረገች ሲሆን አስቀድሞ በስተሰሜን በኩል በሚገኝ ቺቪታቬኪያ የባሕር ዳርቻ ለማለፍ ብታቅድም ነገር ግን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ሊዮ ሃሳብ በኦስቲያ ወደብ እንድታልፍ መደረጉ ታውቋል።

የጣሊያን የወደብ ከተማ ኦስቲያ ከቅዱስ አውጉስቲን እና ከቅድስት ሞኒካ ጋር የተሳሰረች ስትሆን፥ የቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳማውያን ማኅበር አባል የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአካባቢው ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስታወስ “ኦስቲያ በዓለም እና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ጠቃሚ ቦታ የሚሰጥ ወደብ የሚገኝበት ቦታ” በማለት ተናግረዋል።

የተስፋ ምልክቶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለቡድኑ አባላት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር፥ “ከተለያዩ አገሮች፣ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች እና ሃይማኖቶች የመጣን ብንሆንም ሰዎች በመሆናችን አንድ መሆን እንችላለን ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ወጣቶቹ ያበረከቱላቸው የመርከቧ ሥዕል፣ ስለ ሜዲትራኒያን ባሕር የተጻፈ ነጭ መጽሐፍ እና በሁሉም አባላት የተፈረመ የካርታ ምስል ስጦታዎች፥ “ለሜዲትራኒያን እና ለዓለም በሙሉ የተስፋ ምልክት ናቸው” በማለት አመስግነዋቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመርከቧ ላይ ወጣቶችን ሲያገኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመርከቧ ላይ ወጣቶችን ሲያገኙ   (@Vatican Media)

ሦስት መሪ ቃላት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለወጣቶቹ የጉዟቸው መሪ እዲሆናቸው በማለት ሦስት ቃላትን እነርሱም ውይይት፣ ድልድይ እና ሰላም የሚሉትን በማቅረብ፥ "እርስ በርስ መደማመጥን፣ መከባበርን እና ችግሮችን በጋራ ማሸነፍን እንዲማሩ በማሳሰብ፥ የመገናኛ ድልድይነታቸው በሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሕዝቦች መካከል እንዲሆን አደራ ብለዋል።

“በርካታ ሰዎች በትንሽ ጀልባ ላይ አብረው እንደሚኖሩ እርግጠኛ ነኝ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ አብሮ መኖርን፣ እርስ በርስ መከባበርን እና ችግሮችን ማሸነፍን መማር እንዳለባቸው አሳስበው፥ አክለውም “ይህ ለሁሉም ወጣቶች ታላቅ ተሞክሮ እንደሆነ በመግለጽ ወጣቶቹ ይህን ልምዳቸውን ሌሎችን ማስተማር እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ከወጣቶቹ መካከል አንዳንዶቹ ፍልስጤማውያን መሆናቸው የተነገራቸው ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥በዛሬው ዓለም እጅግ አስፈላጊው የሰላም ገንቢዎች መሆንን መማር እንደሆነ በማስረዳት፥ “ሁላችንም የአንድ አምላክ ልጆች በመሆናችን በዚህ ዓለም ውስጥ አብረን እየኖርን አንድ የጋራ ኃላፊነት እንካፈላለን፤ ይህም ፍጥረትን መንከባከብ፣ እርስ በርስ መተሳሰብ እና በዓለም ዙሪያ ሰላምን ማስፈን ነው” ብለዋል።

“አመሰግናችኋለሁ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ወጣቶቹ በዚህ ዓለም ለሁሉም ሰው ተስፋን የሚሰጥ ምልክት በማበርከታቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

“የእናንተ ትውልድ እና ሌሎች እንደ እናንተ ያሉ ብዙ ወጣቶች በዓለም ዙሪያ ሰላምን የሚፈጥር የዚህን ዓይነት ተነሳሽነት ማጎልበትን ይቀጥሉ” በማለት ደጋግመው አመስግነዋቸዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ከወጣቶቹ ጋር የኅብረት ፎቶ ግራፍ ከተነሱ እና የሰላም ዜማን ካሰሙ በኋላ “ቤል ኢስፖየር”  የተሰኘች የወጣቶች የሰላም ትምህርት ቤት መርከብ ከጣሊያን የወደብ ከተማ ኦስቲያ ተነስታ የአንድነት እና የተስፋ መልዕክቷን ለስተላለፍ ወደ ፈረንሳይ ደሴት ኮርሲካ መጓዟ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመርከቧ ውስጥ ከወጣቶች ጋር ሆነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመርከቧ ውስጥ ከወጣቶች ጋር ሆነው   (@Vatican Media)

 

18 Oct 2025, 16:38