ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከመላው የሲኖዶሳዊነት ጉዞ አስተባባሪዎች እና ተሳታፊዎች ጋር ተገናኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ሮም የመጡ ሁለት ሺህ የሚጠጉ የሲኖዶሳዊነት ጉዞ አስተባባሪ እና ተሳታፊ ነጋዲያንን በቫቲካን ተቀብለው ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከጥቅምት 14 እስከ 16/2018 ድረስ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ሮም የመጡ ብሔራዊ የሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ እና ፋይናንስ አገልግሎት ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸውል።  

የሦስት ቀናት የኢዩቢልዩ በዓላቸውን ዓርብ ጥቅምት 14/2018 ዓ. ም. ማክበር ሲጀምሩ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ ጋር የተገናኙት አባላቱ፥ በ16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የመጨረሻ ሠነድ ውስጥ በጉልህ በተጠቀሱ አቅጣጫዎች አፈፃፀም ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ በጋራ ተወያይተዋል።

አባላቱ የሚያከብሩት የኢዮቤልዩ በዓል፥ የመጨረሻው ሠነድ አፈፃፀም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶሳዊነት ጋር የሚገናኙ ሐዋርያዊ እና መዋቅራዊ ሂደቶችን በተግባር ለመተርጎም ያለመ እንደ ሆነ ተመልክቷል። እንደዚሁም አባላቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር በቫቲካን ያደረጉት ውይይት፥ ልዩ ልዩ ማኅበራት እና በውስጣቸው የሚያገለግሉ ሰዎች ለሚያበረክቱት ውድ አገልግሎት እውቅናን ለመስጠት እንደሆነ እንዲሁም በኢዮቤልዩ የተስፋ አድማስ ውስጥ የበለጠ ሲኖዳላዊት ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት ያለሙ መሆናቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በፔሩ የቺክላዮ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው ከዚያም በቅድስት መንበር የብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ዋና አስተባባሪ ሆነው ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሲኖዶሳዊነት ሂደት በመሳተፍ ከአህጉራት የመጡ ተሳታፊዎችን በትኩረት ያዳምቱ እንደ ነበር ይታወሳል።

የሲኖዶሳዊነት ጉዞ አስተባባሪ እና ተሳታፊ አባላት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት በተስፋ ላይ በማተኮር፣ በመንፈስ ቅዱስ እና እርስ በርስ የመደማመጥ መንፈሳዊ ግንዛቤ እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትን በማስቀጠል በኢዮቤልዩ ብርሃን የበለጠ ሲኖዳላዊት ቤተ ክርስቲያንን በማስተዋወቅ ላይ የተደረጉ ተከታታይ ውይይቶችን በጋራ ተመልክተዋል።

ሲኖዶሳዊ ሂደቱ ሐዋርያዊ ውሳኔዎችን ለመለየት እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ለሚያጋጥሟቸው አካባቢያዊ ችግሮች በትክክል ምላሽ የሚሰጡ መንገዶች ለማግኘት በሚረዱ መደበኛ ስብሰባዎች፣ “አብሮ መጓዝ” የሚለውን መርህ በተከተሉ ውይይቶች እና የጋራ ምክክሮች ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሲኖዳላዊ ሂደትን በማስመልከት ከአህጉራት የተሰበሰቡ የቤተ ክርስቲያን እውነታ ንግግሮችን አዳምጠዋል። የአፍሪካ አኅጉርን በተመለከተ የወንጌል ተልዕኮ ለሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን የምትመሰክር፣ በባህሎች እና በሃይማኖቶች መካከል ድልድይን የምትገነባ እና ስዎችን የምታዳምጥ ሚስዮናዊ ቤተ ክርስቲያን የመሆን አስፈላጊነትን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው የአፍሪካ ወጣቶች እና ቤተሰቦች ለሚያበረክቷቸው የህያውነት ስጦታ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያን ብዝሃነትን ተቀብላ ሰላምን እና አንድነትን እንድታሳድግ፣ ለፍጥረት እንክብካቤን እንድታደርግም አሳስበዋል። እንዲሁም እያንዳንዱን የአካባቢ እውነታ መገንዘብ እና ማክበር እንደሚገባ፣ የቤተ ክርስቲያንን ነጠላ ሞዴል ሳይጫኑ ቤተ ክርስቲያን የመሆን በርካታ መንገዶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከኦሼንያ አኅጉር የቀረበውን ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ እንደተናገሩት፥ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊነት መንፈስ በኅብረት ማደጓን እንደምትቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድህነት እና ኢ-ፍትሃዊነት ያሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለመፍታት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል፥ ቤተ ክርስቲያን ድምጿን ከፍ በማድረግ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው ውስጥ ስለ ፍጥረት እና ሰብዓዊ እንክብካቤን በማስመልከት ያቀረቡትን ጥሪ ተግባራዊ እንድታደርግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በአሜሪካ አኅጉር በአገራት እና በማኅበረሰቦች ውስጥ ያለውን ልዩነት በማስታወስ፥ በቤተ ክርስቲያን እና በማኅበረሰብ ውስጥ ሊኖር ስለሚገባ የሲኖዶሳዊነት፣ የመደማመጥ እና የውይይት አስፈላጊነትን ተናግረዋል። ለዚህ ሂደት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን መግባባት እና ኅብረት ለመጠበቅ ቀጣይነት ያለው የካህናት፣ የጳጳሳት እና የምእመናን ስልጠና አስፈላጊነት ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ክልሉ ምን ያህል ተስፋ እንደሚያስፈልገው ገልጸው፥ በትውልድ አገራቸውም ሆነ በዳያስፖራው ዓለም ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች እምነት፣ ድፍረት እና ጽናት በመካከላቸው የመንፈስ ቅዱስ መገኘት እውነተኛ ምልክቶች እንደሆኑ አስረድተዋል። በተጨማሪም በእስያ አኅጉር ለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ክርስቲያን ባልሆኑ ማኅበረሰቦች መካከል በሲኖዶሳዊነት በመኖር፥ በቋንቋ፣ በባህል እና በኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ለምትሰጠው ምስክርነት ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

25 Oct 2025, 17:08