ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለዓለማችን ሰላም ምእመናን በየዕለቱ የመቁጠሪያ ጸሎት እንዲያቀርቡ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአደራ መልዕክታቸው፥ “ለመቁጠሪያ ጸሎት የተወሰነውን የጥቅምት ወር ስንጀምር በዓለማችን ሰላም እንዲወርድ በየዕለቱ የመቁጠሪያ ጸሎት እንድታደርሱ እጋብዛችኋለሁ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህን መልዕክት ያስተላላእፉት ረቡዕ መስከረም 21/2018 ዓ. ም. ረፋድ ላይ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ታዳሚዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ነው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ ግጭቶች እና ጦርነቶች መካከል ምእመናን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ታማኝ የእርቅ መሣሪያዎች በመሆን ሰላምን እንዲያበረታቱ አሳስበዋል።
ለአረብኛ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፍቅር እና ይቅርታ በሰው ልጅ ላይ ከሚወጡ የስቃይ ቁስሎች ሁሉ እንደሚበልጡ እና ከበደሎችም ሁሉ የበለጠ ጠንካራ መሆናቸውን ለመመስከር የተጠሩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከፖርቱጋል ለመጡት ምእመናን ባስተላለፉት መልዕከታቸው፥ የሰላም እና የምሕረት ልኡካን እንዲሆኑ አሳስበው፥ ከፈረንሳይ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያንም ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ከውድቀታችን እና ከልዩነታችን የሚበልጡ የሰላም እና የፍቅር ምስክሮች እንድትሆኑ” በማለት ጠይቀዋል።
