ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለቅድስና በዓል ለመጡት ምዕመናን ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለቅድስና በዓል ለመጡት ምዕመናን ሰላምታቸውን ሲያቀርቡ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ምዕመናን በሙሉ ቅዱሳንን ለመምሰል እንዲጥሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተከበረው የሰባት አዳዲስ ቅዱሳን አዋጅ ላይ ለተገኙት መንፈሳዊ ነጋዲያን ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ ቅዱሳኑ የተስፋ ምልክቶች እና ለምዕመናን በሙሉ ምሳሌዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እሁድ ጥቅምት 9/2018 ዓ. ም. የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ለመካፈል ከዓለም ዙሪያ ለመጡት በርካታ መንፈሳዊ ነጋዲያን ባደረጉት ንግግር፥ “የቅድስና በዓሉ ኅብረት ባላት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየትም ሥፍራ እና ጊዜ ላይ የሚገኙት፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ እና ባሕል ያላቸው አንድ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል እና ሕያው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆናችንን ያስታውሰናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ አዲሶቹ ቅዱሳን ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለሰዎች አገልግሎት በፍቅር የሰጡ “ብሩሕ የተስፋ ምልክቶች ናቸው” ሲሉ ገልጸው፥ “ቅድስና ሁሉም የሚጋራው ጥሪ ነው” በማለት አክለዋል።

ቅዱስ ኢግናጢዮስ ማሎያን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅዱሳኑ ሕይወት ላይ በማሰላሰል፥ አርሜንያ ውስጥ በሰማዕትነት የተገደሉትን አቡነ ኢግናጢዮስ ማሎያን፥ “የኢየሱስ ክርስቶስን የሚመስል ልብ ያላቸው ሐዋርያዊ እረኛ” ናቸው ሲሉ ገልጸዋቸዋል። በስደት ጊዜ ከመንጋቸው ጋር መሆንን የመረጡ፣ ለነጻነት ለማግኘት ሲሉ እምነትን እንዲክዱ ተጠይቀ አይሆንም! ያሉ እና ደማቸውን እስከ ማፍሰስ ድረስ እግዚአብሔርን የመረጡ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

የአርመን ሕዝብ የእመነት ጽናትን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ መስቀልን የጽኑ እምነት ምልክት ማድረጉን በመግለጽ የቅዱስ ኢግናጥዮስ አማላጅነት የምዕመናንን እምነት በማደስ እርቅ እና ሰላምን እንዲያመጣ ጸሎት አቅርበዋል።

ቅዱስ ጴጥሮስ ቶ ሮት

አዲሱን የፓፑዋ ኒው ጊኒ ቅዱስ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ ቶ ሮትን ያስታወሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ ቶ ሮት የፅናት አርአያ እንደሆነው ገልጸዋል። የትምህርተ ክርስቶስ መምህር የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስ ቶ ሮት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሐዋርያዊ አገልግሎቱን በድብቅ መስጠትን ለመቀጠል ሕይወቱን አደጋ ላይ መጣሉን እና ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት የሚከለክለውን የጋብቻ ምስጢር በማክበር፥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋርም መሟገቱን አስታውሰዋል።

ቅዱስ ጴጥሮስ ቶ ሮት፥ “ጊዜው ለእኛ እጅግ ክፉ እና አስፈሪ ቢሆንም እግዚአብሔር አባታችን ከእኛ ጋር ነው” ማለቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ ቶ ሮት ምእመናን የእምነትን እውነት እንዲከላከሉ እና በፈተናዎች ሁሉ ውስጥ በእግዚአብሔር እንዲታመኑ ማሳሰቡን አስታውሰዋል።

የቬነዙዌላ ቅዱሳን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ሁለቱን የቬነዙዌላ ቅዱሳን፥ ቅዱስ ሆሴ ግሬጎሪዮ ሄርናንዴዝ እና ቅድስት ካርመን ሬንዲልስን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ የእነዚህ ቅዱሳን የእምነት፣ የተስፋ እና የበጎ አድራጎት ገድል ምዕመናን የሕይወታቸው መመሪያ እንዲያደርጓቸው አሳስበዋል። እምነት ሕይወትን ወደ ብርሃን እንደሚለውጥ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ተስፋ ለጥረቶች ጊዜያዊ መልስ ለማግኘት የሚደርግ እንዳልሆነ፥ ለጋስነት የእግዚአብሔርን ስጦታ ከመቀበል የሚገኝ፣ የታመሙትን፣ የደሄዩትን እና የተናቁትን እንድናገለግል የሚጠራን እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በዚህ መሠረት፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በርካታ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወንድሞች እና እህቶች ለተመሳሳይ ቅድስና የተጠሩት መሆናቸውን አሳስበው፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በደስታ እንዲገነቡ አበረታተዋቸዋል።

ቅድስት ማርያ ትሮንካቲ እና ቅድስት ቪንቼንዛ ማርያ ፖሎኒ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የኤኳዶር ሳሌዥያዊ ሚስዮናዊት ቅድስት ማርያ ትሮንካቲ፥ ከእምነት እና ከጸሎት በሚገኝ ፍቅር አካላትን እና ልብን መፈወሷን አስታውሰዋል። የምህረት እህቶች ማኅበር መሥራች ቅድስት ቪንቼንዛ ማርያ ፖሎኒ የኢየሱስ ክርስቶስን ርህራሄ ለሕሙማን እና ለተገለሉት ሰዎች በተጨባጭ ማሳየቷን ተናግረው፥ “የእነዚህ ቅዱሳት ሕይወት፥ ቅድስና የሚያብበው አቅመ ደካሞችን በማገልገል እንደሆነ ያሳያል” ብለዋል።

ቅዱስ ባርቶሎ ሎንጎ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፥ በአንድ ወቅት ከእምነት ርቆ የነበረው ባርቶሎ ሎንጎ የምሕረት ሥራውን ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን፣ ድሆችን እና ተስፋ የቆረጡት ሰዎች ለማገልገል ከመወሰኑ በተጨማሪ የመቁጠሪያ ጸሎትን ያበረታታ እንደ ነበር አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ምዕመናን በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ድንቅ ሥራ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓይን በማስተንተን ይህን ምሳሌ እንዲከተሉ አበረታተዋቸዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በቅድስና አዋጅ ላይ ለመገኘት ከሩቅ አገራት የመጡት ምእመናን ወደ አገራቸው ሲመለሱ አዲሶቹን ቅዱሳን ለመምሰል ባላቸው ምኞትት በምስጋና ልብ እንዲመለሱ አደራ ብለዋል።

 

21 Oct 2025, 16:33