የአረጋውያን ሐዋርያዊ እንክብካቤ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የአረጋውያን ሐዋርያዊ እንክብካቤ ዓለም አቀፍ ጉባኤ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “አረጋውያን ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ በረከት ናቸው” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለአረጋውያን የሚሰጥ ሐዋርያዊ እንክብካቤ በማስመልከት የተዘጋጀ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከተሳተፉት ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለተሳታፊዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያን በሚሲዮናዊ አገልግሎቷ መካከል ለአረጋውያን ቦታ እንድትሰጥ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ “አረጋውያኖቻችሁ ሕልምን ያልማሉ!” በሚል መሪ ጭብጥ፥ ቤተ ክርስቲያን ለአረጋውያን የምታበረክተውን ሐዋርያዊ እንክብካቤን በማስመልከት በሮም ያዘጋጀው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከመስከረም 22-24/2018 ዓ. ም. ተካሂዷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጉባኤውን ለተካፈሉት ባደረጉት ንግግር፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአረጋውያን እና በወጣቶች መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ ባላቸውን ፍላጎት፥ የሕይወት ልምድ ያላቸው የዕድሜ ባለጸጋዎች የሕይወት ጉዞን ገና የሚጀምሩትን እንዲረዷቸው በማለት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ንግገራቸውን በመቀጠል፥ “ይሁን እንጂ አረጋውያን ለወጣቶች የሥራ ዕድልን አልሰጡም ወይም ለወጣቶች ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሃብቶችን በመውሰዳቸው ምክንያት በዘመናችን ትውልዶች መካከል ጥልቅ መለያየት ይታያል” ብለዋል።

ዘመናዊ ሕክምና ብዙ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ረጅም ዕድሜ እንዲኖራቸው ማስቻሉን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “አረጋውያን ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲኖር አላደረጉም” የሚል እንዲህ ያለ አፍራሽ አስተሳሰብ ረጅም ዕድሜን እንደ ስህተት እንደሚቆጥረው ገልጸዋል።

“አረጋውያን ስጦታዎች እና ልንቀበላቸው የሚገቡ በረከት ናቸው” ብለው፥ “ረጅም ሕይወት መኖር አዎንታዊ እና በዘመናችን በየትኛውም የዓለም ክፍል ከተስፋ ምልክቶች መካከል አንዱ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “‘ኅብረተሰቡ አረጋውያንን አለመቀበል የመነጨው ‘የሰው ልጅ ምንጊዜም ከፍላጎት ጋር የተፈጠረ ነው’ የሚለውን እውነት ለመቀበል ካለመፈለግ የመነጨ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“በአረጋውያን ላይ የሚታየው አቅመ ደካማነት ይህን እውነት ያስታውሰናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህን እውነት በዓይናቸው እንዳያዩት ዓለማዊ ሽንገላን በሚያራምዱ ሰዎች ተደብቋል ወይም ተወግዷል” ብለዋል።

ከዚህ ይልቅ አረጋውያን ወጣቶች በዓለማዊ የሕይወት ለውጥ ውስጥ የሰው ልጅ መዳንን የሚያገኘው ለእግዚአብሔር እና አንዳችን ለሌላው እንደሚያስፈልገን በመገንዘብ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አስታውሰዋል።

“ስብዕናችን የሚለካው በሕይወት ውስጥ ልናሳካው በምንችለው ነገር ሳይሆን ነገር ግን እራሳችንን በሌሎች እንድንወደድ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሌሎች እንዲረዳ ማድረግ በመቻላችን ነው” ብለዋል።

“እርጅና ሳንዘጋጅ የሚመጣ ሊሆን ይችላል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ አረጋውያንን ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከቅዱሳን ሕይወት እንዲማሩ በመጋበዝ በተስፋ መቁረጥ ሳይሸነፉ በክርስቲያናዊ መንገድ መኖርን እንዲማሩ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሃሳባቸውን አረጋውያንን ወደሚያገለግሉ ሰዎች በማዞር፥ የሥራ ጊዜያቸውን በማጠናቀቅ ወደ አረጋውያንነት ደረጃ በቅርብ ጊዜ የደረሱትን አስታውሰው፥ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አጋር በመሆን የሰበካ እንቅስቃሴዎችን ለመምራት እና ለመጸለይ ነፃ ጊዜ ያላቸውን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

እነዚህን አረጋውያን በወንጌል አገልግሎት በንቃት የሚያሳትፉ ተስማሚ ቋንቋዎችን እና ዕድሎችን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ ሕይወት እና ቅዱስ ወንጌል ለሚያቀርቡልን ጥያቄዎች በጋራ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በወጣትነት ዕድሜያቸው ከእምነት የራቁ ወይም የወንጌልን የምሥራች ቃል ገና ያልሰሙ በርካታ አረጋውያን መኖራቸውን ያስተወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ነገር ግን ምንም ያህል ዕድሜ ቢኖራቸውም ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ሥራ መመስከር አለባት ብለዋል።

“አረጋውያን ብቻቸውን በሚሆኑበት እና በኅብርተሰቡ ተንቀው ወደ ጎን በሚባሉበት ወቅት፥ የብቸኝነት ጨለማን፣ የአረጋውያን ሕይወት ታላቅ ጠላት ከእነርሱ ጋር ተባብሮ ለማሸነፍ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ የሚገልጽ የምሥራች ቃል ወደ እነርሱ ዘንድ ማምጣት ይገባል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችንአረጋውያን የሕልውናን ትርጉም እንደገና እንዲያገኙ መርዳት እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው እና የተስፋ ልኡካን እንዲሆኑ ጋብዘዋል።

“ማንም ሰው ወደ ጎን ሊባል ወይም ራሱን የማይጠቅም አድርጎ ማሰብ የለበትም!”  በማለት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “በቤት ውስጥ በእምነት የሚቀርብ አጭር ጸሎት እንኳን ለእግዚአብሔር ሕዝብ መልካም አስተዋጽኦን በማድረግ በመንፈሳዊ ኅብረት ውስጥ አንድ ያደርገናል” ሲሉ አስረድተዋል።

04 Oct 2025, 16:04