ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እያንዳንዱ ቁምስና በዓለም የተልዕኮ እሑድ እንዲሳተፍ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እሑድ ጥቅምት 9/2018 ዓ. ም. በሚከበረው የተልዕኮ እሑድ ቁምስናዎች በሙሉ እንዲሳተፉ አደራ ብለው፥ በዕለቱ ከምዕመናን በኩል የሚደረግ ልግስና በዓለም ዙሪያ የሚስዮናውያንን መልካም ሥራ እጅግ እንደሚደግፍ በፔሩ በነበራቸው የአገልግሎት ዓመታት ያዩትን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የዓለም ተልዕኮ እሑድ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ “በዓለም ዙሪያ የሚገኝ እያንዳንዱ ካቶሊካዊ ቁምስና በዓለም አቀፍ የተልዕኮ እሑድ ላይ እንዲሳተፍ አሳስባለሁ” ብለዋል።

የዓለም ተልዕኮ እሑድ በየዓመቱ ጥቅምት ወር ከሁለተኛ እስከ መጨረሻው እሁድ የሚከበር ሲሆን፥ ዘንድሮ “በሕዝቦች መካከል የተስፋ ሚስዮናውያን” በሚል መሪ ጭብጥ ጥቅምት 9/2018 ዓ. ም.  እንደሚከበር ታውቋል።

ቅዱስ አባታችን በቪዲዮ መልዕክታቸው፥ በየዓመቱ በሚከበረው የዓለም ተልዕኮ እሑድ መላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአንድነት በተለይም ለሚስዮናውያን እና ለሐዋርያዊ ሥራቸው ፍሬያማነት እንደምትጸልይ አስታውቀዋል።

ቅዱስነታቸው በፔሩ ሚስዮናዊ ካኅን እና ጳጳስ ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ውስጥ በዓለም የተልዕኮ እሁድ የሚታይ የምዕመናን እምነት፣ የሚቀርብ ጸሎት እና ልግስና መላውን ማኅበረሰብ ምን ያህል እንደሚለውጥ መመልከታቸውን ገልጸው፥ በመሆኑም ካቶሊካዊ ቁምስናዎች በሙሉ ተጨባጭ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

“በዓለም ዙሪያ የሚገኝ እያንዳንዱ ካቶሊካዊ ቁምስና በዓለም የተልዕኮ እሑድ ላይ እንዲሳተፍ አሳስባለሁ” በማለት አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ጸሎታችሁ እና ድጋፋችሁ ወንጌልን ለማስፋፋት፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን እና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮችን ለማዳረስ የሚወጠኑ መርሐ ግብሮችን ለማሳካት፣ አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናትን ለመገንባት፣ የሚስዮን አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የጤና እና የትምህርት ፍላጎቶችን ለማሟላት ይረዳል” ብለዋል።

“የእናንተ ጸሎት፣ የእናንተ ድጋፍ ወንጌልን ለማዳረስ፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን እና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መርሃ ግብሮችን ለማስፈጸም፥ አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናትን ለመገንባት እና በሚስዮን ግዛቶች ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የጤና እና የትምህርት ፍላጎቶችን ለማሟላት ይረዳል”

“መጭው ጥቅምት 9 በሕዝቦች መካከል የተስፋ ልኡካን እንድንሆን በተቀበልነው የጥምቀት ጥሪ ላይ በጋራ በምናሰላስልበት ወቅት፣ ተስፋችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ ለሚደረገው ድንቅ እና አስደሳች ተልዕኮ ራሳችንን እናዘጋጅ” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ሚስዮናውያንን ለመደገፍ በሚያደርጉት ጥረት ከጎናቸው ሆነው የሚረዱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቁምስናዎችን አመስግነው ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ልከውላቸዋል።

 

 

14 Oct 2025, 10:17